በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ምን ያህል ተፈትቷል?
ሐሙስ፣ ግንቦት 7 2017የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ በማድረግ ሥርዐቱ በገበያ እንዲመራ ካደረገ በኋላ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ማደጉን በተደጋጋሚ እየገለፀ ነው። አምራቾች፣ ላኪዎችና አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የነበረባቸው ፈተና እየቀነሰ፣ በተሻለ ሁኔታ ማግኘት መጀመራቸውንም የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሰሞኑን ተናግረዋል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አምራችና ላኪዎች የውጭ ምንዛሪአቅርቦት በጉልህ መሻሻሉን ገልፀዋል። ይሁንና የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲሁም የባንኮች ብድር የመስጠት ገደብ ሥራቸው ላይ እክል መፍጠሩን አስታውቀዋል። አንድ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ በበኩላቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የወሰደው ርምጃ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳሉት የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ "በ2011 ዓ.ም ከነበረው አሁን ከእጥፍ በላይ" አድጓል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱም መንግሥት የኢኮኖሚ ሥርዐት ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪመጠባበቂያ በሦስት እጥፍ ማደጉን፣ የምንዛሪ አቅርቦቱም መሻሻሉን ተናግረዋል። ይህንን በተመለከተ አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው አምራች ድርጅቶች አንዱ የበላይ አብ ኬብል ሥራ አሥፈፃሚ የሆኑት አቶ ወንደሰን በላይ ሥራን ለማስፋፋት ብድር ወስዶ ያንንብ ብር ወደ ውጭ ምንዛሪ ለውጦ ለመንቀሳቀስ ካለው ችግር በቀር የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ ነው ብለዋል።
"አወዳድረው ካልከኝ እኔ እንደ አምራች የተሻለ ነገር አለ። የሀገር ውስጥ ገንዘብ ቢኖረው አንድ አምራች ያንን ወስዶ ወር ሁለት ወር ወረፋ ጠብቆ ተቸግሮ ካልሆነ በስተቀር LC (Letter of Credit) መክፈት አይችልም ነበር። አሁን ግን የሀገር ውስጥ ገንዘብ እስካለው ድረስ ብዙ ባንኮች ላይ ሄዶ በሦስት በአራት ቀን ሳምንት ባልሞላ ጊዜ LC መክፈት ይችላል"
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው የግብርና ምርቶች ቡና ቀዳሚው ነው። ላኪዎች የውጭ ምንዛሪ አመንጪም ፈላጊም ናቸው። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁን ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።
"የውጭ ንግዱ ጨምሯል የቡና፣ መጠኑን ጨምሯል። ይህ በዚህ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ በመደረጉ የመጣ ነው ብትለኝ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ነው የምልህ" የበላይ አብ ኬብል ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ወንደሰን በላይ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እና የባንኮች ብድር የመስጠት ገደብ ግን በሌላ መልኩ ሥራቸው ላይ እክል መፍጠሩን አልሸሸጉም።
"የውጭ ምንዛሪ ችግሩ ለቀቅ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም በዚያ የተገኘውን ዕድል በበቂ ለመጠቀም ደግሞ አፀፋዊ ችግር ነው የሚታየው" የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በዚህ ደረጃ ከተሻሻለ፣ የጥሬ ብር/ ገንዘብ እጥረት እንዴት ተከሰተ የሚለውን የኢኮኖሚ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ አብራርተዋል።
"የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ፣ ለማርገብ ወደ አንድ ዲጂት ለማውረድ ወደ ገበያ የሚመጣው የገንዘብ መጠን መቀነስ ስላለበር በዛ ምክንያት ባንኮች የሚያበድሩትን የገንዘብ መጠን ገደብ ተደርጎበታል ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት መንግሥት ሊያነሳው ይችላል። »
መንግሥት ሐምሌ 2016 ዓ.ም በገበያ የሚመራየውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዐት ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በባንኮች ይስተዋል የነበረው ወረፉ ስለመቀነሱ ታዝበናል።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም ችግሩን በማቅለል ረገድ አማራጭ ሆነው ብቅ ብለዋል። ብሔራዊ ባንክ አምስት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ በማደረግ ባንኮች ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ እያደረገ ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ