በኢትዮጵያ የከተማ ወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር ያለመው አዲስ ምርምር
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2017በኢትዮጵያ የከተማ ወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር ያለመው አዲስ ምርምር
በኢትዮጵያ አደገኛ የከተማ ወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችል፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ የምርምር ፕሮጀክት ተጀመረ። ይኸው የሦስት ዓመት የጥናት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ሶስት ከተሞች ጅጅጋ፣ሰመራና ሎጊያ ላይ የተኮረ ነው። ከሰሜን አሜሪካ ኤምሪ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር ምርምሩን በዋናነት የሚያካሂዱት፣ አዲስ አበባ እና ጅጅጋ ዩንቨርስቲዎች ናቸው። ከጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘው የሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ይኸው የምርምር ፕሮጀክት፣ በኢትዮጵያ አደገኛ የሆኑ የከተማ ወባ አማጪ ትንኞችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ቴክኖሎጂና ርካሽ የሆነ ዘዴን ለመጠቀም የሚያስችል ነው።የወባ ስርጭት በአማራ ክልል
ዶቼ ቬለ፤በጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ የዚሁ ፕሮጀክት ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑትን ዶክተር ሰሎሞን ያሬድን አነጋግሯቸዋል። "ባለው ነባራዊ የቁጥጥር ዘይቤ፣ የትንኝ ዕጭ ቁጥጥር የነበረው፣ የብዙ የሰው ኃይል የሚያስፈልገው በመሆኑ እንዲሁም ወጪውም ከፍተኛ በመሆኑ ሌላም፣ በተለምዶ የትንኞች ርጭንትም በመላመዷ፣አዲስ የአሰራር ዘይቤ፣ አዲስ ኬሚካልና አዲስ የአሰራር ዘዴ ይህንን ችግር ለመፍታት ነው።
አዲሱ ምርምር ምንድ ነው?
አዲሱ የምርምር ፕሮጀክት እንዴት እንደሚካሄድ የጠየቅናቸው ዶክተር ለሎሞን ሲያስረዱ፤
"አሠራሩ ቴክኖሎጂን በታገዘ፣የትንኟን መራቢያ ቦታዎችን መለየት፣ በሳተላይት ምስሎች በመጠቀም፣የወባ ትንኝ የምትረባባቸው ዕቃዎች፣ የኮንስትራክሽን ቦታዎች ውኃ ያቆሩበት በአጠቃላይ ያን ምስል ወስዶ፣የሰው ሰራሽ ክህሎትን በመጠቀም፣ ያንን ምስል አስጠንቶ "ላዛፕ "የተባለ መተግበሪያ አለ።እሱን በማበልጸግ የሞባይል መተግበሪያ ይሰራል።ያንን መተግበሪያ ደግሞ በቀጥታ እነዚህ የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ያመላክትልናል ማለት ነው።ይህ ቴክኖሎጂ በጣም ቀልጣፋና ትክክለኛ የሆነ መረጃን ይሰጠናልና በርቀትም ሆኖ መቆጣጠር ይቻላል።ለሃገሪቱም በጣም ጠቃሚ ይሆናል።"በአፍሪካ የወባ በሽታን የመከላከል ጥረቶች
"ኢኖሬሌስ ስቴፌንሲ"
የዚህ የጥናት ፕሮጀከት ዋና ዓላማው፣"ኢኖሬሌስ ስቴፈንሲ "የተባለችውን ወራሪ የወባ ትንኝ መቆጣጠር ሲሆን፣ይህም በበጋ ወቅት የትንኝ ዕጪዎችን ሊይዙ የሚችሉትን የውኃ ምንጮችን በመለየት ነው።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የዚህ ፕሮጀክት ሌላኛው ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አርአያ ገብረሥላሴ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል። "ይህቺ ትንኝ በከፍተኛ ሁኔታ በተለይ ከምስራቁ የሃገራችን ክፍል ይዛ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል መንገድ፣ ከተሞች ላይ በብዛት ከመስፋፋቷ አንፃር፣እንደሚታወቀው ሀገራችንንም ጨምሮ በአፍሪቃ ውስጥ ወባ በብዛት ገጠራማ አካባቢ የጤና ችግር ነው ፤አልፎ አልፎ ከተሞችንም ቢያጠቃ ማለት ነው።እናም ይኼ የወባ ስርጭቱ ወደ ከተማ መስፋፋት በቅርቡ የተደረገ ጥናት ድሬዳዋ ላይ አመላክቷል፣ ምን ዓይነት አበርክቶ እንደነበራት።" የወባ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋፍቷል
ተመራማሪዎቹ፣አደገኛና ወራሪ የሆነችውን የወባ በሽታ አማጪ ትንኝ፣ በትክክለኛ ጊዜና በትክክለኛው ቦታ መቆጣጠር ከቻሉ፣ ከኢትዮጵያ እና ከአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገሮች ጭምር የማስወገድ ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ ይናገራሉ። "እነዚህ በይበልጥ ዋና የመራቢያ ጉድጓዶች ወይም ለግንባታ የተቆፈሩ ጉድጓዶችን እነዚህን ቦታዎች እያንዳንዱን ቤት ሄዶ ማድረግ ስለማይቻል፣ዋና የመራቢያ አስተዋጽኦ አላቸው ተብሎ የሚታሰቡትን ቦታዎች በኬሚካል በማከም በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል የጥናት ዘዴ ነው ብለን ነው የምናምነው።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ