በኢትዮጵያ የተደጋገመው ርዕደ መሬት እና ስጋቱ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017በኢትዮጵያም ከመስከረም 2017 ዓ/ም ጀምሮ በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት ርዕደ መሬቶች መከሰታቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ/ም በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ በተለይም በአዋሽ ፈንታሌ እና አካባቢው ንዝረቱ እስከ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የደረሰ እና በሬክተር ስኬል እስከ 5.8 የተመዘገበ ርዕደ መሬት መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ አመልክቷል።
በክስተቱ የሰው ህይወት አልጠፋም
ክስተቱ በአካባቢው የመሬት መሰንጠቅ ያስከተለ ሲሆን፤ ዶፈን የተባለው ተራራም ድንጋይ የቀላቀለ ጋዝ ሲተፋ እና በበርካታ ሥፍራዎችም ፍል ውሀ ሲፈልቅ ማየታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች በስጋት ይገልፃሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የመሬት መንቀጥቀጥ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ እንደገለጹት ርዕደ መሬቱ ከመካከለኛ ያለፈ ቢሆንም፤ እስካሁን በክስተቱ የሰው ህይወት አልጠፋም።ነገር ግን ርዕደ መሬቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ።
ይህንን ተከትሎ መንግስት ርዕደ መሬቱ በሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎችን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን አስታውቋል።
ድህረ ርዕደ መሬት የበለጠ ጉዳት ያደርሳልባለሙያዎቹ እንደሚገልፁት ርዕደ መሬት ከተከሰተ በኋላ ድህረ ርዕደ መሬት ወይም / After shocks/ ይከሰታል። በሬክተር ስኬል ሲለካ ከዋናው ያነሰ ቢሆንም ቀድሞውኑ በዋናው ርዕደ መሬት የተመቱ እና ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች በቀላሉ ሊያወድም ስለሚችል የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ከዚህ አንፃር በተደጋጋሚ ንዝረት ያጋጠማቸው መሰረተ ልማቶች ሊፈርሱ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይህንን በመገንዘብ ይመስላል መንግስት በአግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመልክቷል።ክስተቱ በዋና ዋና ከተሞች የጎላ ተጽዕኖ ባያደርስም ፤ዜጎች በባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልእክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩም አሳስቧል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ድህረ ርዕደ መሬት ለሳምንታት፣ለወራት ወይም ለዓመታት ሊቀጥል ይችላል።የሰሞኑ ርዕደ መሬት በመጠኑ ረግቧል የሚሉት ፕሮፌሰር አታላይም መዘናጋት እንደማያስፈልግ ገልፀዋል።
ርዕደ መሬት እንዴት ይፈጠራል?
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዘመናዊ የሳይንስ ምርምሮች ከመስፋፋታቸው በፊት በጥንት ዘመን ርዕደ መሬት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳይሆኑ በተለያዩ እምነቶች እና ባህሎች የእግዚአብሔር ቁጣ ምልክቶች እና ለሰው ልጆች ኃጢአት ቅጣት ተደርገው ይቆጠሩ ነበር።
የሥነ-ምድር ተመራማሪዎች እንደሚገልፁት ርዕደ መሬት በምድር ውስጣዊ እንቅስቃሴ የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ክስተት ነው።
የምንኖርባት ምድር ሶስት የተደራረቡ አካላት ያሏት ሲሆን፤የውስጠኛው ክፍል ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር /core/ የመካከለኛው ክፍል / mantle/ እንዲሁም የላይኛው ክፍል /crust/ በመባል ይጠራሉ። የምድር የላይኛው ክፍል ጠንካራ እና ከ50 እስከ 70 ኬሜ ውፍረት ያለው ቢሆንም ቀጫጥን ቅርፊቶችም አሉት።ይህ የምድር ቅርፊት «ፕሌትስ» በሚባሉ ብዙ ቁርጥራጮችም የተከፋፈለ ነው። እነዚህ የምድር ቅርፊቶች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ናቸው። እንቅስቃሴው ብዙውን ጊዜ ያለምንም ችግር የሚካሄድ ቢሆንም ፤አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚተሻሹበት እና የሚጋጩበት ጊዜ አለ።ይህ ድንተኛ ግጭት የሚፈጥረው ንዝረት እና ሞገድም ምድርን በመሰንጠቅ ርዕደ መሬት እንደፈጠር ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ ሀገር ነች
ይህ የመሬት ውስጣዊ እንቅስቃሴ ደግሞ በታላቁ የሰምጥ ሸለቆበተደጋጋሚ የሚታይ ክስተት ነው። የሰምጥ ሸለቆ ከሚያልፍባቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ለዚሁ ተፈጥሯዊ ክስተት ተጋላጭ ሀገር ነች።ያም ሆኖ በሀገሪቱ ይህ ግንዛቤ የለም ይላሉ።
በመሆኑም የሰሞኑን ክስተት እንደ ማንቂያ ደወል በመውሰድ ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባ ያስረዳሉ።ስለ አደጋው ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር በመንግስት በኩል የአደጋን መቋቋም የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የህንፃ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድም ሌላው ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ለመሆኑ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዚህ አደጋ ተጋላጭ ሊሆን ይችላልን?
«የህዳሴው ግድብ የተሰራበት ቦታ ተጋነነ ባይባል ህዳሴው ግድብ አሁን ያለበት ቦታ ላይ ካልተሰራ የትኛውም ዓለም ላይ ሊሰራ አይችልም ማለት ነው።ምክንያቱም በጣም አክቲቭ ከምንለው ሰምጥ ሸለቆ በወፍ በረር አሁን ፈንታሌ ካለበት ምናልባት ወደ 700 ኪሎ ሜትር የሚርቅ ይመስለኛል። እና የሰምጥ ሸለቆ ተፅዕኖ በህዳሴው ግድቡ የሚያደርሰው ተፅዕኖ በጣም በጣም እዚህ ግባ የማይባል ነው።ማለቴ ተፅዕኖው ዜሮ ነው።»በማለት ገልፀዋል።
ርዕደ መሬትን ማስቀረት ባይቻልም ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል
የሥነምድር ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት ርዕደ መሬት ተፈጥሯዊ ክስተት በመሆኑ መከላከል ወይም ማስቀረት አይቻልም።ነገር ግን የሚያደርሰውን ጉዳት ግን መቀነስ ይቻላል። ከዚህ አኳያ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ በመነሳት የተማከለ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አሰጣጥ ስርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።በህብረተሰቡ ዘንድም መደረግ ያለባቸውን የጥንቃቄ ርምጃዎች ጠቁመዋል።
ርዕደ መሬት ሲከሰት የጥንቃቄ ርምጃዎች
የሌላው ዓለም የሚጠቀምባቸውን መሰረታዊ የጥንቃቄ መንገዶች በሀገር ውስጥ ቋንቋ ተርጉሞ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ ጠቃሚ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አታላይ፤ሜዳ ላይ እያሉ ርዕደ መሬት ከተከሰተ ዛፍ እና የመብራት ፖል አካባቢ አለመሆን፣ቤት ውስጥ ከሆነ ደግሞ ከመደርደሪያ ፣የተሰቀለ ነገር ካለበት እና ከመስኮት አካባቢ መራቅ እንዲሁም ጠረጴዛ ስር መሆን ፣ራስን እና አንገትን ከጉዳት በሚከላከል ነገር መሸፈን እና በህንፃዎች ውስጥ ማዕዘን አካባቢ መሆን ይመከራል ብለዋል።ተቀጣጣይ ነገር እና ክብሪት የመሳሰሉ ነገሮችን አለመጠቀምም ሌላው የጥንቃቄ ዘዴ ነው።
በኢትዮጵያ የከፋ ችግር ያደረሱ ርዕደ መሬቶች ተመዝግበዋል
እንደ ፕሮፌሰር አታላይ ገለፃ በኢትዮጵያ በታሪክ ተመዝግበው የተቀመጡ የከፋ ችግር ያደረሱከፍተኛ የርዕደ መሬት ክስተቶች አጋጥመዋል።ለአብነትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፣ትልቁ እና በሬክተር ስኬል 6 .8 የተመዘገበው ርዕደመሬት በአፄ ሚኒልክ ዘመን በአዲስ አበባ አቅራቢያ ተከስቷል። በ1969 ዓ/ም አፋር ውስጥ ከአሁኗ የሰመራ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ትገኝ የነበረች ሰርዶ የተባለች ከተማ ሙሉ ለሙሉ መውደሟን እንዲሁም በካራቆሬ ከፍ ያለ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ እንደነበር ተመዝግቧል።
ስለሆነም የአሁኑን ክስተት እንደ ማንቂያ ደወል በመውሰድ በመንግስትም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሻለ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።በሀገሪቱ በዘርፉ የሚደረገውን ሳይንሳዊ የምርምር አቅምን በሰው ሀይል እና በቁሳቁስ ማሳደግም ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ