በአፍሪካ የወባ በሽታን የመከላከል ጥረቶች
ቅዳሜ፣ የካቲት 15 2017አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ እና የቀድሞ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስሮች፣ አምባሳደሮች በተገኙበት በአፍሪካ መሪዎች የወባ ጥምረት የቀረበው የአሕጉሩ የወባ በሽታ ስርጭት፣ የመከላከል ጥረቶች እና ችግሮች ላይ የወባ በሽታ የሚሊዮኖችን ጤና ከማውደሙ በተጨማሪ በአባል ሀገራት ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል። በወባ በሽታ በተያዙ አካባቢዎች በሽታው በዓመት እስከ 1.3 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገትን የሚቀንስ ሲሆን በአፍሪካ በየዓመቱ እስከ ግማሽ ቢሊዮን የሚደርሱ የሥራ ቀናትን የሚቀንስ ነው ተብሏል።
በተለይ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በዋናነት የበሽታው ሰለባዎች ቢሆኑም ድምጻቸው ግን ብዙም አይደመጥም የሚለው መልእክት በዚሁ ጊዜ ተመላክቷል።
በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳይ እና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሱማቲ ይህ ሁኔታ መፍትሔ እንዲሰጠው አሳስበዋል።
ተመራማሪዎች አዲስ የወባ መከላከያ ማግኘታቸውን ገለፁ
"የወባ በሽታን ለመከላከል የሚደረገው ትግል የተቀናጀ የገንዘብ እጥረት እያጋጠመው ነው። በዚህ ወቅት እየጨመረ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰብአዊ ቀውስ፣ እና እንደ ፀረ ተባይ እና አደንዛዥ እጽ የመቋቋም ያሉ ተፈጥሯዊ ሥጋቶ ችግር እየፈጠረብን ነው። ይህ ሁኔታ መፍትሔ ካልተበጀለት ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተገኘውን ጥንካራ ግኝት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።"
የአሕጉሩ መሪዎች የፖለቲካ ፈቃደኝነት እንዲኖራቸው እና በሽታውን ለመከላከል ሀብት ፈሰስ እንዲያደርጉም ውትወታ ተደርጓል። የአፍሪካ ሕብረት ብዙውን ጊዜ ሲሳኩ የማይስተዋሉ እና የተለጡጡ እቅዶችን ይፋ በማድረግ ይታወቃል። ለዚህ ማሳያው በ2030 - ከአምስት ዓመታት በኋላ በአሕጉሩ ወባን አጠፋለሁ የሚል ትልም ነድፎ ነበር።
የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ መሪዎች የወባ ጥምረትን ከአሥር ዓመታት በፊት በሊ ቀመንበርነት የመሩት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ይልቁንም ወባን በመከላከል ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች እንዳይቀለበሱ በዚሁ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
የወባ በሽታን ሙሉ በሙሉ ለመግታት በየዓመቱ 5.2 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ማሰባሰብ እንደሚጠይቅ እና ለዚህም በመሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
"እየቀጠለ ያለው የገንዘብ እጥረት ችግር፣ እየጨመሩ የሚሄዱትን የተፈጥሮ ሥጋቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰብአዊ ቀውሶች አሉታዊ ተፅእኖዎችን ለመቀነስ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን።
እነዚህ ሥጋቶች በ 20 ዓመታት ውስጥ ለወባ የተጋለጡትን በጣም ከባድ የሆነውን ድንገተኛ ሁኔታዎች ያመለክታሉ። እናም ምላሽ ካልተሰጣቸው ወደ ወባ መጨመር እና ወረርሽኝነት ያመራሉ።"
የአፍሪካ መሪዎች የወባ ጥምረት ሊቀመንበርነትን አሁን የተረከቡት የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ዱማ ቦኮ ከዚህ በፊት የተጀመሩ የፀረ ወባ ጥረቶችን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል። ለዚህ ይረዳ ዘንድ ሁሉም የሕብረቱ አባል ሀገራት የአፍሪካ የመድኃኒት ኤጀንሲ የሕግ ማእቀፍ ስምምነትን እንዲያፀድቁ ጥሪ አድርገዋል።
"መጪው ዓለም አቀፍ የገንዘብ አቅርቦት በሥራችን ሂደት የጀመርነውን በጎ እድገት እንድንቀጥል ወይም የበለጠ ወደ ኋላ እንድንመለስ ይወስናል። የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ዕርዳታን ለማገድ ያሳለፈው ውሳኔ በተለይ እራሳችንን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ ያላገኘንበት በመሆኑ ያለምንም ጥርጥር የበለጠ ከሥራችን እንድንርቅ አድርጎናል።
በትግራይ በየሳምንቱ 17 ሺህ ሰዎች በወባ እየተያዙ ነው
በመሰል አደጋ ጊዜ የሀብት አጠቃቀማችንን በመቀነስ እና ለጤና የበጀት ድልድልን በመጨመር፣ የሀገር ውስጥ ሀብቶችን በማሰባሰብ አፍሪካ በአስቸኳይ ለችግሩ መነሳት አለባት።"
የአለም ጤና ድርጅት አፍሪካ ውስጥ በ2024 ግብጽ ከወባ በሽታ ነጻ የሆነች ሀገር መሆኗን አውጇል። በዚሁ አዲስ አበባ ላይ ከአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጎን ለጎን በተደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ ግብጽ ለዚህ ስኬቷ ከተቋሙ ሽልማት ተበርክቶላታል። ይህ ጥረት ለሌሎች ሀገራት የፀረ ወባ ትግል መነሳሳት የሚፈጥር ስለመሆኑም ተነግሯል።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ2023 ብቻ አለም ላይ 263 ሚሊዮን ሰዎችን የወባ በሽታ ይዟቸው የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 600 ሺህ ያህሉ በዚሁ በሽታ ሞተዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ