በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተዳሰሱ ዋና ዋና ጉዳዮች
ሰኞ፣ የካቲት 10 2017በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተዳሰሱ ዋና ዋና ጉዳዮች
ቅዳሜ እና እሑድ አዲስ አበባ ውስጥ የተከናወነው 38 ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአህጉሩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭት እና ጦርነቶች በውይይት፣ በድርድር እና እርቅ እንዲፈቱ አቋም የተያዘበት ነው ተብሏል። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ የሕብረቱ አባል መሪዎች በሶማሊያ ያለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚሻ መሆኑን፣ በምስራቅ ዴሞክራሲያዊ ኮንጎ የተከሰተው ግጭት በውይይት እና በእርቅ ሊፈታ እንደሚገባ፣ ለሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ብቸኛ መፍትሔ አስቸኳይ ተኩስ አቁም ማድረግ መሆኑን እንደመከሩበት አስታውቋል። የፕሪቶሪያውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ዘገባ ያቀረበው ሕብረቱ ስምምነቱ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካው መፍትሔ በማስገኘት ረገድ ጥሩ ማሳያ መሆኑ ተመላክቷል። የሚቀሩ እርምጃዎች ቢኖሩም ስምምነቱ ተፈጻሚ እየሆነ ነውም ተብሏል።
የጉባኤው ዋነኛ የምክክር ማጠንጠኛ ፍትሕን መሻት ነበር
አፍሪካ እና ሕዝቦቿ በአስከፊው የባሪያ ፍንገላ እና የባሪያ ንግድ እንዲሁም ጠባሳው ዛሬም ጎልቶ በሚታየው የቅኝ ግዛት ዘመን፣ ብሎም በከፋፋዩ የአፓርታይድ ሥርዓተ ትድድር ለደረሰባቸው ግፍ እና በደል ማካካሻ ይገባቸዋል የሚለው ሀሳብ ጎልቶ የተስተናገደበት 38 ኛው የአሕጉሩ የመሪዎች ጉባኤ፣ ለሕብረቱ ኮሚሽን የጅቡቲውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍን ሊቀመንበር አድርጎ በመሾም ተጠናቋል። በድህረ ቅኝ ግዛት እና የነጻነት ዘመን ላይ አፍሪካዊያን መሪዎች በሕዝባቸው ላይ የፈፀሙት በደል፣ ግፍ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዴት ይቁም የሚለው ግን የውይይታቸው አካል ስለመሆኑ አልተሰማም።የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሱዳን
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ባንኮሌ አዶዬ የሕብረቱ አባል መሪዎች በሶማሊያ ያለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚሻ መሆኑን፣ በምስራቅ ዴሞክራሲያዊ ኮንጎ የተከሰተው ግጭት በውይይት እና በእርቅ ሊፈታ እንደሚገባ፣ ለሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ብቸኛ መፍትሔ ወታደራዊ ሳይሆን አስቸኳይ ተኩስ አቁም ማድረግ መሆኑን መሪዎቹ መምከራቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በጉባኤው መጠናቀቂያ ትናንት ምሽት የፕሪቶሪያው ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነትን የተመለከተ ዘገባም ቀርቧል። ስምምነቱ በአፍሪካ ሰላምን ለማስፈን ለሚደረግ ጥረት መማሪያ መሆን የቻለ እና ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለማመንጨት ጉልህ ማሳያ ተደርጎ ተጠቅሷል።
የስምምነቱ ፈራሚዎች የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የሕወሓት መሪዎች እንዲሁም አደራዳሪዎቻቸው በተገኙበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ስምምነቱ የሚቀሩት አፈጻጸሞች ቢኖሩም እየተተገበረ መሆኑን የሕብረቱ ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ባንኮሌ አዶዬ ትናንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
"በመጀመሪያ [ስምምነቱ] ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች ሙሉ አክብሮት ሰጥቷል። ሁለተኛ በዚህ ሂደት ከሁሉም የስምምነቱ ተዋናዮች ጋር ሁሉን ያሳተፈ ውይይት መኖሩን ታዝበናል። ሶስት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች፣ በመጨረሻም ሁሉንም የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳዮችን በተመሳሳይ ጊዜ ለመፍታት መድረኩን ተጠቅመዋል። የፕሪቶሪያ ስምምነት እየሰራ ነው? አዎ፣ በእርግጠኝነት። እስካሁን በክልሉ የተመለሰ የፀጥታ ችግር የለም። ሆኖም ግን በእርግጥም አሁንም መፈፀም የሚገባቸው የሚቀሩ ጉዳዮች አሉ"የአፍሪቃ ኅብረት እንደ ስሙ አሕጉሩን በሕብረት ያስተሳስር ይሆን?
በሕብረቱ አቋም የተያዘባቸው ዋና ዋና የግጭት ቀጣናዎች
በምስራቅ ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ የተከሰተው ግጭት ሕብረቱን በእጅጉ ማሳሰቡ እና ችግሩ በውይይት እና እርቅ እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጧል ተብሏል። ኤም 23 እና ደጋፊዎቻቸው የጎማ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በሁሉም ከተያዙ ከተሞች በአስቸኳይ እንዲወጡም ተጠይቀዋል። የሀገራት መሪዎችም ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገር መሰረታዊ የሆነውን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ አንድነት እና የግዛት አንድነት መጠበቅ እንዳለባቸው አቋም ይዘዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች በሶማሊያ በቀጣይ የሚሰማራው የአፍሪካ ሕብረት የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ሽግግር በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ስለመሆኑ ባንኮሌ አዶዬ ገልፀዋል። "አለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካን እንዲደግፍ እንጠይቃለን። በአፍሪካ ቀንድ እየሠራን ያለነው የሶማሊያ ችግር ብቻ አይደለም። የጋራ የደህንነት አካሄድ የሚፈልግ የአፍሪካ ችግር ነው።"
ከአፍሪካ ሕብረት አባልነቷ የታገደችው እና ላለፉት ሁለት ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን ችግሯ በወታደራዊ ኃይል ሳይሆን በአስቸኳይ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲፈታ በመሪዎች ውሳኔ ስለመተላለፉ በሕብረቱ ጉባኤ መጨረሻ ላይ ተጠቅሷል።ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ጉልህ ጥሪ የቀረበበት የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ
የጉባኤው ድምቀት የነበሩት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር
በዚህ ጉባኤ ላይ የተጋበዙት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ ስለ አፍሪካ አንድነት እና ሕብረት አስፈላጊነት ቻይና በሰራችው የተንጣለለ አዳራሽ፣ በዋናነት አውሮፓ ሕብረት አብዛኛውን በጀቱን በሚሸፍንለት የሕብረቱ የጉባኤ ስፍራ መሪዎቹን እና የጉባኤዎን ታዛቢዎች ያስደሰተ ሞቅ ያለ ንግግር አድርገዋል።
አፍሪካን ከአውዳሚ ግጭት፣ ከእርስ በርስ ጦርነት፣ ከመንግሥት ግልበጣ ልማድ፣ ከድህነት፣ ከተረጂነት፣ ከኋላ ቀርነት እና በሽታ መታደግ የቸገራቸው የአሕጉሩ መሪዎች ግን ከ 54 ዓመታት በፊት የወቅቱ የጋናው ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንኩርማህ ስለ አፍሩካ አንድነት፣ ስለ የጋራ ገበያ፣ መገበያያ ገንዘብ፣ የጋራ ባንክ እና መሰለ ብርቱ ሥራ የሚጠይቁ ጥሪዎችን ያስተጋቡበትን ሀቀኛ ንግግር የዘነጉት አልያም ችላ ያሉት ይመስላሉ።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ