በአገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ኦነግ ያወጣው መግለጫ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 26 2017በአገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ኦነግ ያወጣው መግለጫ
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሚያሰባስባቸው የምክክር አጀንዳዎች ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ባወጣዉ መግለጫ በአገሪቱ ለሚስተዋሉ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ችግሮች መድሃኒት ይሆናል ባለዉ በምክክር አስፈላጊነት እንደሚያም እና፤ ሂደቱ ግን አካታች እና አሳታፊ ሊሆን እንደሚገባ ጠይቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገ የኮሚሽኑ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ አሰባሰብ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፈሰር መስፍን አርዓያ እስካሁን በምክክር ሂደቱ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸውን በመጠቆም በሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የኦሮሞ ልሒቃንን ያስቆጣው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ንግግር
በመግለጫው የአገሪቱን ችግሮች ከመሰረቱ የሚፈታ ምክክር አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም ለው የኦነግ መግለጫ፤ ተሳታፊ ባልሆነበት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት ላይ ቅሬታውን አሰምቷል፡፡«በበረታው የግጭት ዳፋ» የኦነግ መግለጫ
ኮሚሽኑ አጀንዳ እያሰባሰበ ከመሆኑ ባሻገር እየተሰበሰቡ ያሉትን ለምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በይፋ ባላሳወቅበት በአሁን ወቅት ኦነግ “በትግል የመጣ” ያለውን “የህዝቦች መብት” “በአገራዊ ምክክር ስም እንዳይደናቀፍ እሰጋለሁ” በማለት ይህም አደጋ እንዳያስከትል ሲል ነዉ የጠየቀው፡፡
የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ በዚሁ ላይ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየታቸው፤ “በዘመናት ትግል የተገኘውን ህዝቦች የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው የሚወስኑበትና ለህዝቦች መብት ዋስትና የሆኑ ህግጋት እንዳይናዱ ነው የጠየቅነው” ያሉት አቶ ለሚ ከባለፈው ምርጫ ወዲህ በአገሪቱ ይስተዋላል ያሉት የጸጥታ ችግሮች እንዳይባባስም ስጋት አለን ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ይህንን መግለጫ ያወጣነውም ከምክክር ሂደቱ አጀንዳ አሰባሰብ ላይ “ከተነሱ አንዳንድ ሃሳቦች በመነሳት ስጋት ገብቶን ነው” ሲሉም የመግለጫው አወጣጡንም መንስኤ አብራርተዋል፡፡``በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግስት ይመስረት`` ምክረ ሃሳብ ያስኬዳል ?
አቶ ለሚ ፓርቲያቸው ተሳታፊ ባልሆነበት በሂደቱ ስለምን ከውጪ ሆነው ሂደቱን ተቃወመው በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም፤ ፓርቲያቸው በሂደቱ እንዳሳተፍ ስላደረገው ጉዳይ ይህን ብለዋል፡፡ “እኛ እንደ ድርጅት ለግለሰቦቹ ክብር አለን ነገር ግን ለኮሚሽኑ እውቅና አንሰጥም በማለት” የኮሚሽኑ አወቃቀር እና የኮሚሽነሮች አመራረጥ ላይ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ጥያቄ በማንሳት ኦነግ በተለይም የህገመንግስት ማሻሻያን ከማይስማሙባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የተከናወነውን የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የምክክር አጀንዳን ከተረከቡ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፈሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ የቀረቡትን አጀንዳዎች በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበው በመገባደድ ላይ ባለው የአገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ በሂደቱ ተሳታፊ ያልሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የታጠቁ አካላትን ተሳታፊ የማድረጉ ጉዳይ መሆኑንና በዚህም ላይ እንደሚሰራበት አስታውቀዋል፡፡ በዚህም “እነሱም ወደዚህ አጀንዳቸውን በማምጣት በቀጣይ በሚደረገው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ እነሱም ተሳታፊ ሆነው ሁሉም አሸናፊ ሆነው የሚወጣበትን እንደሆን ነው ጥሪ የምናቀርበው” ብለዋል፡፡
ስለሚቀርበው ጥሪው ጥያቄ የቀረበላቸው የኦነግ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ለሚ ግን መሰል ጥሪዎች መልስ ሚገኙት በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ኮከስ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ