በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረገው ዘላቂ የከተማ ልማት ለተፈናቃዮች
ቅዳሜ፣ የካቲት 15 2017በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ፕሮጀክቱን የሚተገብረው ኦውዳ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ሙህየዲን ጀማል የአውሮፓ ህብረት በለገሰው ድጋፍ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ቦታዎች የሚከናወኑ ተግባራትን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል ።
ጅግጅጋ እና አሶሳን ጨምሮ ፕሮጀክቱ በአምስት አፍሪካ ሀገራት በዘጠኝ ከተሞች የሚተገበር መሆኑንም አቶ ሙህየዲን አብራርተዋል።
ከጎረቤት አካባቢዎች ተፈናቅለው በጅግጅጋ ከሚገኙት መካከል አንዷ ወይዘሮ ከድራ አብዶሽ ለዶይቼ ቬለ በመጠለያ አሉ ያሏቸውን ችግሮች ጠቁመዋል።
"በጀመሪያ እንዲሟላልን የምንፈልገው የመብራት የውኃ እና የትምህርት ቤት አገልግሎት ነው። ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው ያለብን። በተለይ መንገድ የለም ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም ተቸግረናል።" ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወደ ቄያቸው ይመለሳሉ ተባለ
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሌላ አስተያየት ሰጭ “በአካባቢያችን በርካታ ተፈናቃዮች ይኖራሉ። የሚሰጡ አገልግሎቶችም ካለው ፍላጎት ጋር አልተመጣጠነም” በማለት ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል።
“ያለው ማህበረሰብ ላይ በየጊዜው ተፈናቃዮች ይጨመራሉ” ያሉት አስተያየት ሰጪ የውኃ ጉዳይን በምሳሌነት በማንሳት ያለውን ችግር አብራርተዋል። “አሁን እዚህ ጋር ውኃ ለመቅዳት ብዙ ሰዓት መጠበቅ ይኖርብናል። ውኃ በሳምንት አንዴ ነው የሚመጣው በአንድ ጀሪካን አምስት ብር መክፈል ይጠይቃል” የሚሉት አስተያየት ሰጪ “ለነዚህ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋል” በማለት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ርዳታ ማቋረጥ እና የትግራይ ክልል ስጋት
በፕሮጀክቱ ማስጀመርያ መድረክ መንግስት ተፈናቅለው የሚመጡ ሰዎችን ለማቋቋም ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስትር ዲኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ፕሮጀክቱ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል ።
ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት የጅግጅጋ ውይይት መድረክ ላይ ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው የአፍሪካ ሀገራት እና የለጋሽ ተወካዮች ተገኝተዋል።
መሳይ ተክሉ
እሸቴ በቀለ