በአውሮጳ ኮሮና የያዛቸው ቁጥር ጨምሯል
ዓርብ፣ የካቲት 27 2012
እስካሁን ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን የገደለው የኮሮና ተህዋሲ በመላው ዓለም መሰራጨቱ ቀጥሏል። በ85 ሃገራት በተዛመተው በኮሮና ተህዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 100 ሺህ ተጠግቷል። በኔዘርላንድስ በኮሮና የመጀመሪያ ሰው መሞቱን የሀገሪቱ የጤና ባለሥልጣናት ዛሬ አስታውቀዋል። ሟቹ የ86 ዓመት አዛውንት ናቸው። በጀርመን ኮሮና የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ዛሬ 534 ደርሷል። የጀርመን የበሽታዎች መቆጣጠሪያ መሥሪያ ቤት ትናንት ምሽት የኮሮና ተህዋሲ ያለባቸው ቁጥር ከ400 በላይ ነው ሲል ነበር ያስታወቀው ። ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ተህዋሲው በ15 ቱ ተገኝቷል።እስካሁን ኮሮና ያልተገኘባት የማዕከላዊ ጀርመንዋ ፌደራል ክፍለ ግዛት ዛክሰን አንሃልት ብቻ ናት። የምዕራብ ጀርመኑ ግዛት ኖርድ ራይን ቬስት ፋለን በጀርመን ኮሮና በተገኘባቸው ሰዎች ብዛት ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘ ነው።በግዛቱ 281 ሰዎች ኮሮና ተገኝቶባቸዋል።በደቡብ ጀርመኑ በባድንቩርተምበርግ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር 81 እንዲሁም በባቫርያ ግዛት 79 በኮሮና ተህዋሲ የተያዙ ሰዎች እንዳሉም ተገልጿል። ቤልጂግ ኮሮና 109 ሰዎች ኮሮና እንዳለባቸው ማረጋገጧን ተናግራለች። ከአፍሪቃ ካሜሩን ተህዋሲው ያለበት የመጀመሪያ ሰው ማግኘቷን ተናግራለች።ቶጎም ዛሬ በተህዋሲው የተያዘ ሰው አግኝታለች። በሴኔጋል በተህዋሲው የተያዙ 4 የውጭ ዜጎች እንዳሉ ሲገለጽ ደቡብ አፍሪቃ አንድ ናይጀሪያም አንድ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ይገኙባቸዋል። 7 በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች ከተገኙ በኋላ ለአንድ ወር የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በታወጀባት በፍልስጤም ወደ ቤተልሄም ከተማ መግባትም ሆነ ከከተማዋ መውጣት ዛሬ ተከልክሏል። በርካታ ጎብኚዎች የሚጎርፉበት ቤተልሄም የሚገኘው በክርስቲያኖች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ስፍራ ነው ተብሎ የሚታመነው የልደት ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ወር ያህል ይዘጋሉ ተብለው ከሚጠበቁት ታሪካዊ ስፍራዎች አንዱ መሆኑ ተዘግቧል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ