በአማራ ክልል ወደ 4 ሚሊዮን ታዳጊዎች ት/ቤት አይሄዱም ተባለ
ሐሙስ፣ ጥር 22 2017በአማራ ክልል እድሜያቸዉ ለትምህርት ከደረሱ እና ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረዉ 7 ሚልየን ተማሪዎች ዉስጥ 2.3 ሚልየን ተማሪዎች ናቸዉ 2017 ዓ.ም ወደ ትምህርት ገበታቸዉ የመጡት ለአብነትም በክልሉ በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 142 የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ተግባሩን ይቀጥላሉ ተብሎ ቢታሰብም በማስተማር ላይ ያሉት ግን 17 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸዉ ይላሉ የወረዳዉ ትምህርት ፅህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ አዘዘ።
«እንግዲህ ባለፍት ስድስት ወራት በወረዳችን የትምህርት እንቅስቃሴ ባጋጠመዉ የፀጥታ ችግር ምክንያት የኛም ወረዳ ጉዳት ደርሶበታል 133 አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 14 ብቻ ናቸዉ 9 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉን እያስተማሩ ያሉት ሦስት ብቻ ናቸዉ።»
በበጀት አመቱ መመዝገብ የነበረብን በአንደኛ ደረጃ ከ48 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ነዉ የመዘገብነዉ ግን 9ሺህ አይበልጡም በሁለተኛ ደረጃ 14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መመዝገብ ይጠበቅብናል የመዘገብናቸዉ ወደ አምስት ሺህ አካባቢ ነዉ ስለዚህ ይህ በጣም ዝቅተኛ ነዉ።»
በክልሉ ያለዉ የፀጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረዉ ተፅኖ የጎላ እንደሆነ የሚናገሩት የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍትህ ታደሰ የመማር ማስተማሩ የተቋረጠባቸዉን አካባቢዎች ዳግም ወደ ትምህርት ለማስገባት እየተሰራ ነዉ ነገር ግን በዞኑ የማንነት ጥያቄ ያለባቸዉ አካባቢዎች አሁንም ከመማር ማስተማር ዉጭ ናቸዉ ይላሉ
«ብግና ላስታ ቆላማዉ አካባቢዎች መቄት ከወሰድን ጉባላፍቶም በመስመር ላይ ያሉትን የመማር ማስተማር እንዲቀጥሉ ምክክር እየተደረገ እየተሰራ ነዉ ያለዉ 100 ፐርሰንት ትምህርት ቤት ከፍተዉ እያስተማሩ ያሉ 7 ወረዳዎች አሉ በከፊል የሚያስተምሩ ወደ አራት ወረዳዎች ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ የመማር ማስተማር የተቋረጠባቸዉ የማንነት ጥያቄ ያለባቸዉ ሦስት ወረዳዎችና ዳዉንት ወረዳ በአሁኑ ሰአት ሙሉበሙሉ መማር ማስተማሩ የተቋረጠባቸዉ ናቸዉ።»
400ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በትምህርት አመቱ ከመዘገባቸዉ 2.7 ሚልየን ተማሪዎች መካከልም ከስድስት ወራት በኃላም 400 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸዉ ላይ አለመሆናቸዉን ወይዘሮ እየሩስ መንግስቱ የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይናገራሉ።
«በአመቱ በገጠመን የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ 7 ሚልየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ እቅድ ይዘን ነበር የተንቀሳቀስነዉ መመዝገብ የቻልነዉ ግን 2.7 ሚልየን ተማሪ ብቻ ነዉ ከመዘገብናቸዉ ተማሪዎች ዉስጥም አሁን በመማር ማስተማር ላይ የሚገኙት ወደ 2.3 ሚልየን ተማሪዎች ናቸዉ ስለዚህ ከመዘገብናቸዉ እንኳን 400 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ዉጭ መሆናቸዉን ያሳየናል።»
በሀገር አቀፍ ፈተና የክልሉ ተማሪዎች ዉጤት ዝቅ ማለት
የአማራ ክልል በግጭት ዉስጥ በቆየባቸዉ ግዚያት የክልሉ ተማሪዎች አጠቃላይ ዉጤት ዝቅ ማለቱን ተከትሎ ዘንድሮ ለ12ተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ የተሻለ ዉጤት እንዲገኝ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ይገልፃል።
«ያለፈዉ አመት የ12ተኛ ክፍል ዉጤታችን በክልል ደረጃ ወደ6.6 ነዉ 50 ፐርሰንትና ከዚያ በላይ አግኝተዉ ወደ ዮንቨርስቲ የገቡት ስለዚህ የባለፈዉን አመት ጉድለታችንን በምን መልኩ እንሙላዉ ብለን እየሰራን ነዉ ይላሉ።»
ሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ
አሁንም በክልሉ ወደ ትምህርት ቤት ይመጣሉ ተብለዉ ታስበዉ የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸዉ ለመመለስ እስከ ቀጣዮ የካቲት 30 ድረስ የሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ይካሄዳል ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይናገራሉ።
«የመጀመሪዉ ዙር ምዝገባችን በሚፈለገዉ መልኩ ባለመሄዱ ሁለተኛ ዙር ምዝገባ ንቅናቄ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል በዚህም ቢሆን 200 ሺህ ተማሪ ብቻ ነዉ መምጣት የቻለዉ ስለዚህ ድጋሜ የንቅናቄ መድረክ ያስፈልገናል ቀሪተማሪዎችን ወደትምህርት ቤት ለማምጣትም እስከ የካቲት 30ድረስ ተማሪዎችን በልዮ ሁኔታ እንመዘግባለን።»
ኢሳያስ ገላዉ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ