በአማራ ክልል አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሆነዋል
ረቡዕ፣ ጥር 28 2017በክልሉ ከ85 በመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች የመሆናቸው አንድምታ
በአማራ ክልል 86.5 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸዉ ተነገረ ። በክልሉ የተካሄዱና እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች ለትምህርት ተቋማት መጎዳት ምክንያት ናቸዉም ተብሏል።
መምህር መብራት ካሳየ በአማራ ክልል የዋግ ህምራ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር በፃግብጂ ወረዳ የፃድቃ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ናቸዉ ። እርሳቸዉ የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ከዳስ የተሠራና ደረጃዉን የጠበቀ ባለመሆኑ ለማስተማር መቸገራቸውን ተናግረዋል።
``የሚማሩት ዳስ ላይ ነዉ፤ ዳሱም የሚችል ዳስ አይደለም ፤ ቅንጭብት ጋር የተያያዘ ነዉ፤ ጧት ሲመጡ ተማሪ መስለዉ ይመጣሉ ፤ ስድሰት ሰዓት ወደ ቤት ሲባሉ ግን አቧራ ለብሰዉ ተማሪ አይመስሉም ። በመጋቢት ፣ ሚያዝያ ፣ ግንቦት አልፎአፎ ዝናብ ስለሚጥል ትምህርታቸዉን በትክክል አይማሩም ። ምክንያቱም ዝናብ በመጣ ቁጥር ወደ ቤት ነዉ የሚሄዱት ፤ ይታመማሉ፤ በታመሙ ቁጥር ደግሞ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ።``
በአማራ ክልል ወደ 4 ሚሊዮን ታዳጊዎች ት/ቤት አይሄዱም ተባለ
በዋግ ህምራ ብሄረሰብ ዞን 12ትምህርት ቤቶች የዳስ ትምህርት ቤት ሲሆኑ 271 መማሪያ ክፍሎች አሏቸዉ። ተማሪዎች በየዕለቱ ትምህርታቸዉን የሚከታተሉት ለፀሀይና ዝናብ ክፍት በሆኑ መማሪያ ክፍሎች ነዉ ይላሉ በዋግ ህምራ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ፍታለሽ ምህረቴ።
``12 የዳስ ትምህርት ቤቶች አሉን ፤ 271 የዳስ ክፍሎች አሉን ፤ ከተመቻቸ የመማሪያ ክፍል የሚማር ተማሪና በዳስ የሚማሩ ተማሪዎች በጣም ልዮነት አላቸዉ ። በትምህርት ጥራቱ ላይ ማለት ነዉ በዳስ የሚማሩት አቧራ ንፋስ ፀሀይ አለ ፤ ይህ እየተፈራረቀ ነዉ የሚማሩት ፤ ትምህርቱን በአግባብና በትክክል ለመከታተል እጅግ ፈተና እየሆነባቸዉ ነዉ ``
«በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምሕርት ቤት አይሄዱም»
በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ምክንያት ብርቱ ጉዳት አስተናግደዋል
በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች በትምህርት ተቋማት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚሉት የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሠጠ ታደሰ በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በርካታ ትምህርት ቤቶች ወደ ዳስ ትምህርትቤትነት ተቀይረዋል ይላሉ።
``ዳስ ትምርት ቤቶች የተፈጠሩት ከሠሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ መልሶ ግንባታዉ በተገቢዉ መንገድ ባለመሰራቱ ያመጡት ችግር የሚታወቅ ነዉ፤ ምቹ አይደሉም ፤ ለመማር ማስተማር እንደ ዞን ስምንት ናቸዉ፤ ትምህርት ቤቱቹ አሁን እየሰበሰብን ባለዉ መረጃ ከዳስ ያልተናነሱ ጣሪያቸዉ ቆርቆሮ ቢሆንም የወላለቁ ሌሎችም እንዳሉ አሁን እየመጡ ነዉ መረጃዎች።``
የመማር ማስተማሩን ፈታኝ የሚያደርጉ የዳስ ትምህርት ቤቶች ምርጫ ስለታጣ ብቻ ተማሪዎች እንዲማሩባቸዉ ተደርገዋል ይላሉ ወይዘሮ ፍታለሽ ምህረቴ።
`` የዳስ ትምህርት ቤትና የዳስ ክፍል ተብሎ ምቹ የሚባል ነገር የለም። አማራጭ ሲጠፋና ሜዳ ላይ ሆነዉ ከሚማሩ ዳስ ክፍል ላይና ዳስ ትምህርት ቤት ይማሩ ከሚል የመጨረሻ አማራጭ እንጂ ይሄ የተሻለ አማራጭ አይደለም።``
አማራ ክልል የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው ተባለ
በክልሉ በርካታ የዳስ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ
በአማራ ክልል 86.5 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሲሆኑ ሰሜን ወሎ ዋግ ህምራ ፣ ደቡብ ጎንደር ሌሎች አካባቢዎች የዳስ ትምህርት ቤቶች በብዛት ይገኙባቸዋል ። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኢየሩሳሌም መንግስቱ አሁን በክልሉ ያለዉ ግጭት በርካታ ትምህርት ቤቶችን እንዲወድሙና ደረጃቸዉ ዝቅ እንዲል እያደረገ ነዉ ይላሉ።
``የክልላችን የትምህርት ቤቶች ደረጃ ከዚህ በፊትም በዝቅተኛ ደረጃ እየተገመገመ የመጣ ነዉ ፤ አሁን ደግሞ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ወደ ኋላ የሚመልሱ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ነዉ። ምክንያቱም አሁን ባለዉ የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል የወደሙ አሉ።``
በአማራ ክልል ያለዉ ችግር የክልሉን ትምህርት እየጎዳዉ እንደሆነና በትምህርት ዘርፉ ታይቶ የነበረዉን ተስፋ ስጋት ዉስጥ ያስገባ ነዉ የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ በመንግስትም ይሁን በማህበረሰቡ በጋራ የትምህርት ተቋማትን የማደራጀት ተግባር ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
``የትምህርት ቤት ደረጃ ግብዓት ብቻ ማለት አይደለም ግብአት አለ፤ ሂደት አለ፤ ዉጤት አለ ፤ሦስቱንም ያማከለ ነዉ። ስለዚህ ግብዓትን ከማሟላት አኳያ መንግስት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ አጠቃላይ ማህበረሰቡ በንቅናቄ ትምህርት ቤቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስና መልሶ ግንባታ የሚሰራ ይሆናል።``
ኢሳያስ ገላው
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ