በአማራ ክልል መማር ያልቻሉ ልጃገረዶች እያገቡ ነዉ
ማክሰኞ፣ የካቲት 4 2017በአማራ ክልል በሚደረገዉ ግጭት ምክንያት ትምሕርት መከታተል ያልቻሉ ልጃገረዶች እያገቡ መሆኑን ወላጆችና መምሕራን አስታወቁ።ወላጆችና መምሕራን እንደሚሉት በክልሉ ትምሕርት ለማቋረጥ የሚገደዱ ተማሪዎች በተለይም የልጃገረዶች ቁጥር እየጨመረ ነዉ። የአማራ ክልል የሴቶችና ህፃናት ቢሮም ችግር ያለዉን የልጃገረዶች ትምሕርት ማቋረጥ ሊኖር እንደሚችል ገልጧል።ይሁንና በክልሉ ባለው የፀጥታ መታወክ ምክን ያት ቢሮዉ የተጣራ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ አመልክቷል።
አስትያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት በክልሉ ባለው የሠላም እጦት ምክንያት ብዙዎቹ ተማሪዎች ትምህርት በማቋረጥ የተለያዩ አማራጮችን እየወሰዱ ነው። አንዳንዶቹ ስደትን ሲመርጡ ሌሎች ደግሞ ትዳርን መርጠዋል።በምስራቅ ጎጃም ዞን የእነማይ ወረዳ ነዋሪ ለዶይቼቬሌ እንደገለጡት በርካታ ልጃገረዶች በትምህርት ተስፋ በመቁረጥ አማራጭ ያሉትን እርምጃ እየወሰዱ ነው።
ትምህርት ያቋረጡ ልጃገረዶች ጋብቻን ምርጫ አድርገዋል
ትምህርት በመቋረጡ ተስፋ መቁረጥ በተማሪዎች ዘንድ መኖሩን የሚናገሩት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ ልጃገረዶች ትዳርን እየመረጡ እንደሆነ ተናግረዋል፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ከአገር መውጣት የሚያስችላቸውን ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ናቸው ነው ያሉት። ለሁለት ዓመት ከትምህርት በማቋረታቸው ወላጆች ልጅ መዳርን አማራጭ እንዳደረጉ ነው ያብራሩት።
በዚሁ ዞን እናርጅ እናውጋ ወረዳ መምህር እንደሆኑ የገለጡልን አስተያየት ሰጪ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአብዛኛው ወደ ትዳር እየገቡ ነው። በተልይ ችግሩ በገጠር አካባቢ የባሰ እንደሆነም አብራርተዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን የይልማና ዴንሳ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው በትምህርት ተስፋ የቆረጡ ወንዶችም ሴቶችም በገፍ ወደ ትዳር መግባታቸውን ጠቁመው፣ ለቀጣዩ የፋሲካ በዓል ለመገባትም ብዙዎቹ ቀጠሮ እንደያዙ ነው የገለፁልን።
ተማሪዎች “ሆ” ብለው ወደ ትዳር እየገቡ ነው
“... ሆ ብሎ ነው የተጋባ፣ ትምህርት ተስፋ አስቆርጦታል አሁን ህፃናት ነው እንጂ የሚማሩት የደረሱት እያገቡ ነው፣ በቀጣዩ ፋሲካ “መንጋ” (ብዙ ለማለት ነው) ነው ያለው፣ ተማሪ የነበሩ ወንዱሚስት፣ ሴቷም ባል እያገቡ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ አስተያየት የሰጡን ነዋሪም ችግሩ በአካባቢው እንዳለ ጠቁመው፣ ይህ የትምህርት መስተጓጎል ዓመታት ወደ ኋላ 50 ዓመታት የሚጎትት ነው ብለውታል።
የመረጃ እጥረት ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አላስቻለም
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የእነማይ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሐይማኖት አወቀ በወረዳው ካሉ 29 ቀበሌዎች በሁለቱ ብቻ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጠው፣ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መረጃ ማግኜት ባለመቻሉ የቸገሩን ጥልቀት ማወቅ አይቻልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ዝና ጌታቸውበክልሉ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንደራቁ መረጃ እንዳለ ጠቅሰው፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለጃገረዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
አሁን ባለው ሁኔት የመረጃ ልውውጥ አለ ለማለት እንደማይቻል አመልክተው የሴት ተማሪዎችን ሁኔታ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጠዋል።
“7 ሚሊዮን ተማሪዎች ለመመዝግብ ታቅዶ፣ 2.7 ሚሊዮን ብቻ ተመዝግበዋል” የአማራ ትምህርት ቢሮ
ዶይቼ ቬሌ ያነጋገራት አንድ የሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ የሠላም በር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ትምህርት በመቋረጡ በጣም እንዳዘነች ገልጣ ገጠር ከበኢተሰቦቿ ጋር የትምህርት ቤት መከፈትን እየጠበቀች እንደሆን አመልክታለች::
የአማራ ክልል በያዝነው ዓመት 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መመዝገብ የቻሉት ግን 2 ሚሊዮን 700 ሺህ ያክል ብቻ እንደሆኑ የአማራ ክልል ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግሥቱ በቀርቡ ኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ገልጠዋል።
ዓለምነዉ መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ