በአማራ ክልል ሆስፒታሎች የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄዎች የደገፉ ሰልፎች ተካሔዱ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 2 2017በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባልሙያዎች ከደመወዝና ሌሎች ጥቅማጥቅም ክፍያዎች አለመመጣጠን ጋር በተያያዘ የማህበራዊ ንቅናቄ ዘመቻዎችን ካደረጉ አንድ ወር እየሞላቸው ነው፡፡ 12 ጥያቄዎቻቸውንም እንዲመለሱላቸው ለጤና ሚኒስቴር ማስገባታቸውን ንቅናቄውን የሚመሩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄውን በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፎችን እያካሄዱ ነው፡፡ በአማራ ክልል ዛሬ ሰልፍ ካካሄዱ ተቋማት መካክል የደብረታቦር ሆስፒታል አንዱ ሲሆን የሰልፉን ዓላማ በተመለከተ የአንድ፣ “ሠልፉ በግቢ ውስጥ ተካሂዷል፣ በዋናነት ሰልፉ ለአገር አቀፉ የጤና ባሙያዎች ንቅናቄ ድጋፍ መስጠት ነው “ ብለዋል፡፡
በደብረማርቆስ ሆስፒታል ገቢ ውስጥ በተመሳሳይ ባልሙያዎቹ ሠልፍ ያካሄዱ ሲሆን ባልሙያዎቹ በሰልፋቸው “እየራበን አንሰራም፣ ተገቢው ክፍያ ይከፈለን” የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል ነው ያሉት፡፡
በህክምና ሙያ ተመርቃ ተሰዳ ለመስራት የተገደደች ወጣት
በባሕር ዳር ጥበበ ጊዮን ሆስፒታል በተደረግው የጤና ባለሙያዎች ሠልፍ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እስከ 4 ወራት እንደማይከፈላቸው ተግልጧል፣ ለአግራዊ የጤና ባለሙያዎች ያላቸውን አጋርነትም የገለፁበት ሠልፍ እንደነበረም አንድ አስተያየት ሰጪ አመልክተዋል፡፡
ትናንት በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሆስፒታል ግቢ የተደርገውን ሠላማዊ ሰልፍ በማስመልከት ደግሞ አንድ የህክምና ባለሙያን ጠይቀን የሚከተለውን ምላሽ ስጥተዋል፡፡
“እኛም እንደሀገር የተነሳው የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ እኛንም ይመለከታል በሚል መሰረታዊ ጥያቄ የጠየቅን መሆኑን፣ የመኖር አለመኖር ጥያቄ የጠየቅን መሆኑና እኛም እንደሀገር ለመጣው የጤና ባለሙያው ንቅናቄ አካል መሆናችንን በይፋ ለመግለፅ ነው” ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭት በጤና ባለሙያዎች ስራ ላይ ያደረሰዉ ጫና
የጎንደር ሆስፒታል ሠራተኞች በተመሳሳይ ንቅናቄውን በመደገፍ ሠላማዊ ሰልፍ ሰሞኑን ያካሄዱ ሲሆን የሆስፒታሉና የከተማዋ ጤና መምሪያ ኃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ከሰራተናወ ጋር ውይይት ቢያደርጉም ንቅናቄው አገር አቀፍ መሆኑን ባልሙያዎቹ ለባለስልጣናቱ ማስረዳታቸውን አንድ ባልሙያ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የጤና ኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ሰሞኑን እንደገለፁልን ለባልሙያው ጥያቄዎች እውቅና እንደሚሰጡና የጤና ባልሙያዎቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የጤና ባልሙያዎች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸው ከሚያዝያ 3/2017 ዓ ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ንቅናቄ የጀመሩ ሲሆን ጥያቄዎቻቸው በተጥቀሰው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካላገኙ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፣ የጤና ባለሙያዎች የሰጡት “የሥራ እናቆማለን” የማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ ነገ ይጠናቀቃል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ