በትግራይ ደቡባዊ ዞን የቀጠለዉ ተቃዉሞ
ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2017የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የደቡባዊ ዞን መሪዎች ለመቀየር ያደረገው እንቅሰቃሴ ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ትላንት በትግራይ ደቡብ ምስራቅ ዞን ዓዲጉደም ከተማ 'የህዝብ መድረክ' ለመከልከል ተብሎ የፀጥታ ሐይሎች ወሰዱት በተባለ እርምጃ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር አካላት ለመቀየር የወሰደው እርምጃ ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ተከስቶ የሰነበተ ሲሆን ይህ የሚቃወም ሰልፎችም በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ናቸው። በሌላ በኩል ትላንት እሁድ በክልሉ ደቡብ ምስራቅ ዞን ወጀራት ወረዳ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ መድረክ ለመከልከል እንዲሁም የሚድያ ሽፋን እንዳያገኝ ለማድረግ በማቀድ በተባለ ታጣቂዎች እርምጃዎች መውሰዳቸው ተገልጿል። የወጀራት ወረዳ ፀጥታ ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሐጎስ ለዶቼቬለ እንዳሉት የተደረገው ክልከላ የተቃወመ ህዝብ ህዝብ ላይ በተከፈተ ተኩስ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ገልፀዋል።የትግራይ ክልል ሹም ሽር ያስከተለዉ ተቃዉሞ
አቶ ረዳኢ "ህዝቡ መድረኩን ለመከታተል የሚመጡ አካላት ለምን ይከለከላሉ ብሎ ቦታው ድረስ በመሄድ ተቃወመ። በቦታው ደግሞ ታጣቂዎች ቶክስ ከፈቱ። ወያናይ ደስታ ገብረእዝጊ የተባለ ጓዳችን ተገደለ። ይህ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ፈጥሮ ይገኛል። ዛሬ የቀብር ስነስርዓቱ ተፈፅሟል" ብለዋል።
ማእከላቸው ትግራይ አድርገው የሚሰሩ የግል ሚድያ የሆኑት ቲቢኤስ ቴሌቭዥን እና ቲፒኤም ባልደረቦቻቸው ወደ አካባቢ በመጓዘ ላይ እያሉ መታገታቸው፥ በግፈት ከተፈቱ በኃላም የነዋሪዎች ሰልፍ በመከታተል ላይ እያሉ እስር እና እንግልት እንደደረሳቸው ሚድያዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ስለትላንቱ ሁነት መግለጫ ያወጣው ቃንጪ ሓቂ ፓርቲ አሁን ላይ በትግራይ እየተስተዋለ ያለው ውጥረት፥ አስቀድሞ የነበረው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በሐይል የማስወገድ ተቀጥያ ነው ብሎታል። የቃንጪ ሓቂ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ደጋፊ ጎደፋይ "አስቀድሞ የነበረው ግዚያዊ አስተዳደር በሐይል ካፈረሱት በኃላ፥ እሱ አስቀምጧቸው የነበሩ ባለስልጣናት ለማውረድ ነው በሐይል ለመቀየር ነው እየተሞከረ ያለው" ብለዋል።
ከዚህ በዘለለም ህዝቡ በህወሓት ላይ ያለው ተቃውሞ በግልፅ እየታየ መሆኑ አቶ ደጋፊ ጨምረው ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች ለትግራይ ህዝብ ፍትሃዊ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አዋኪ አጀንዳዎች በመፍጠር ላይ ተጠምደዋል ሲል ህወሓት በሳምንታዊ መግለጫው አስታውቋል። ህወሓት በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና ወታደራዊ መሪዎች የትግራይ ህዝብን በማስፈራራት ላይ ናቸው፣ እየቀረበ ያለው ዛቻ ትግራይን ለቀጣይ ጥፋት ሰበብ ለመፍጠር ያለመ ነው ብሏል። ህወሓት ጨምሮም የትግራይ ጥቅም ለማስከበር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንደሚቀጥል እና የፕሪቶርያ ውል በሙሉእነት እንዲተገበር ዓለማቀፉ በማሕበረሰብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል ብሏል።ትግራይ ክልል የፖለቲካ አለመረጋጋትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በህወሓት እና የፌደራል መንግስት መካከል ያለው መካረር ለማስታረቅ የተለያዩ አካላት ጥረት እያደረጉ ያሉ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተወከሉ የተባሉ የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ዛሬ ከክልሉ መሪዎች ጋር ሲወያዩ ውለዋል።
በዚሁ የትላንቱ ሁነት ዙርያ እንዲሁም ሰሞኑን በትግራይ ደቡባዊ ዞን በነበረው ሁኔታ ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ