በትግራይ ደቡባዊ ዞን እየበረታ የመጣዉ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት
ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2017በትግራይ ደቡባዊ ዞን ያለው ሁኔታ ተከትሎ፥ አለመረጋጋት ቀጥሏል። በአከባቢው መንግስታዊ አገልግሎት ተቋርጧል። የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በአካባቢው 'የሽብር ጥቃቶች' እየተፈፀሙ ናቸው፥ በእነዚህ ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብሏል።
የህወሓት ክፍፍል ተከትሎ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የተፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታ፥ የዞኑ አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲወርዱ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መወሰኑ ተከትሎ ወደ ተካረረ ሁኔታ ተሸጋግሯል። በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎች በሚካሄድባቸው የደቡባዊ ዞን ከተሞች እና ሌሎች ወረዳዎች በአብዛኛው መንግስታዊ አገልግሎቶች ተስተጓጉሎ እንደሚገኝ ከነዋሪዎች ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ሐይሎች እና የአካባቢ ሚሊሻዎች ግጭት እንዳይከሰትም በነዋሪዎች ዘንድ ስጋት አለ። የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር ተደርገው የተሾሙት አቶ ዝናቡ ገብረመድህን ነባር የዞኑ የፀጥታ ሐላፊዎች ከስልጣናቸው ያወረዱ ሲሆን ሁሉም የወረዳ እና ከተማ አመራሮች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ይህ የማያደርጉ ከሆነ ግን እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል። በደቡባዊ ትግራይ የተፈጠረዉ ዉጥረት እንደቀጠለ ነዉ
በሌላ በኩል አዲሱ የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር አቶ ዝናቡ ገብረመድህን በሳምንቱ መጨረሻ በአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፥ በከተማዋም አቀባበል እንደተደረገላቸው የህወሓት የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አላማጣ ከተማ እና ነዋሪው በአስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፥ ከተማዋ ከየአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የእንቅስቃሴ እግድ ልትወጣ ይገባል ያሉት እኚሁ ባለስልጣን፥ ይህ ለማመቻቸት ከአላማጣ በተጨማሪ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ከተሞች የሁከት ማእከል ለማድረግ እየሰሩ ናቸው ያሏቸው ሐይሎች ማሸነፍ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
የዞኑ አስተዳደር አቶ ዝናቡ "በኮማንድ ፓስት መመራት ማለት በእስርቤት መኖር ማለት ነው። ያውም አላማጣ፥ መምሸቱ ወይም መንጋቱ የማይታወቅ የደራ ከተማ። አሁን መንቀሳቀስ የማይቻልበት፣ ለሊት ታምመህ እንኳን ሆስፒታል መሄድ የማይቻልበት ሁኔታ እንዳለ አውቃለሁ። ከዚህ ነፃ መውጣት የምንችለው፥ ከአላማጣ በተጨማሪ ሌሎች አካባቢዎች ወደኮማንድ ፖስት ማስገባት የሚፈልግ ሐይል በመታገል ነው" ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ትላንት ባሰራጨው መልአክም በማይጨው ከተማ የጥፋት ሐይሎች ባላቸው አካላት ቦምብ መወርወሩ፣ ይሁንና በሰው ጉዳት አለማድረሱ አስታውቋል። ይህ የሽብር ተግባር ፈፀሙ ባላቸው ላይም እርምጃ እንደሚወስድ በጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ የሚመራው የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገልጿል። በደቡባዊ ትግራይ የስልጣን ሹም ሽሩ ያስከተለው ውዝግብ
ከዚህ በተጨማሪ ከአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በነበረ ውይይት የተናገሩት የዞኑ አስተዳደር አቶ ዝናቡ ገብረመድህን፥ ከትግራይ ደቡብ ዞን አለ ያሉት ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲያብራሩ "አሁን እያደረግነው ያለው ትግል ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ነው። ከግለሰብ አልያም ከሌላ ጋር አይገናኝም። የሆነ ሰው በሌላ ለመቀየር አይደለም። በትግላችን እና መስዋእትነታችን ያገኘነው አካባቢ መልሰህ በጠላት እጅ እንዲወድቅ እየተሰራ ስለሆነ፥ እኛም ከእጃችን እንዳይወጣ እያደረግነው ያለ ትግል መሆኑ ሁሉ ሊረዳው ይገባል" ብለዋል። ይህ በእንዲህ እያለ በትግራይ ደቡብ ዞን ያለው ሁኔታ አስመልክቶ የህወሓት መግለጫ ያሰራጨ ሲሆን፥ ከህወሓት የተነጠሉ ሐይሎች ወደ አካባቢ የውጭ ሐይል እጁ እንድያስገባ ጥሪ እያቀረቡ ነው ብልዋል። ነባሮቹ የትግራይ ደቡባዊ ዞን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ