በትግራይ ክልል የሰፈሩ ተፈናቃዮች በሥነ ልቡና ችግር ይሰቃያሉ-ጥናት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 8 2017በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቃሉት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በዚህ ዝናብ ወቅት ለከፋ ችግር መጋለጣቸዉ ተነገረ። ተፈናቃዮች በረሃብ፣ በሽታ እና በመጠልያ እጦት ከመቸገራቸዉ በተጨማሪ፥ ከፍተኛ የስነልቦና ችግር እየገጠማቸው መሆኑን አንድ ጥናት አመላክቷል። በትግራይ ክልል በ92 መጠልያ ጣብያዎች የተደረገ ጥናት 81 በመቶ ተፈናቃዮች ለስነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል ይላል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና ሌሎች በተፈናቃዮች ዙርያ የሚሰሩ ተቋማት ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፥ በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአየው የተፈናቀሉ እና አሁንም ድረስ ወደቀዬአቸው ያልተመለሱ 1 ሚልዮን ገደማ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በትግራይ የተለያዩ መጠልያዎች እንደሚኖሩ ይገለፃል። እነዚህ ተፈናቃዮች በተለይም በያዝነው የክረምት ወቅት ከነበረው የከፋ ሁኔታ እያስተናገዱ፣ በጎርፍ እና ዝናብ መጠልያዎቻቸው እየወደሙ አስቸጋሪ ኑሮ እየገፉ ሲሆን እነዚህ እና ሌሎች የተወሳሰቡ ችግሮች በርካቶች ለሞትና በሽታና እየዳረጉ እንዳሉም ተመልክቷል። በትግራይ በጦርነቱ ወቅት የደረሱ በደሎች የሚያጣራው መንግስታዊ ተቋም የትግራይ የጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን እንደሚለው በክልሉ በ92 የተፈናቃዮች መጠልያ ጣብያዎች የተደረገው ጥናት 81 በመቶ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለስነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል ይላል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይሁን ዓለምአቀፍ ተቋማት የተፈናቃዮች መብት የሚያስጠብቁ እርምጃ አለመውሰዳቸው የሚገልፁ ጥናቱ ያደረጉት ምሁራን በዚህም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለአደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ ብለዋል። ከአጥኚዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት የሕግ ምሁሩ አቶ ብርሃነ ገብረእግዚአብሔር፥ በተፈናቃዮቹ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት የፈረመው የካምፓላ ስምምነት እያከበረ አይደለም ይላሉ።
በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀለ ዜጋ ከጦርነቱ መቆም በኃላ በአስቸኳይ ወደቀዬው ካለመመለሳቸው በተጨማሪ መሰረታዊ አቅርቦቶች ጭምር እያገኙ እንዳልሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ሌላው የጥናቱ አዘጋጅ አቶ ገብረመስቀል ሐይሉ ያስረዳሉ።
አቶ ገብረመስቀል"በተለያዩ አቅርቦት ዘርፎች ስንመለከት የተተገበረ መብት የለም። የምግብ አቅርቦት፣ መጠልያ፣ የተፈናቃዮች ዋስትና ይሁን ነፃነት በሁሉም ዘርፍ ተፈናቃዮች መብታቸው ተጥሶ ነው እየኖሩ ያሉት" ይላሉ።
በተፈናቃዮች ላይ እየደረሰ ያለው በተደል ጀምሮ በትግራይ በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙት በደሎች ፍትህ ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው መሆኑ የሚገልፀው የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን በበኩሉ፥ ተጠያቂነት በማረጋገጥ ላይ ያሉ ክፍተቶች ለመሙላት ስራው አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመለክቷል። የኮምሽኑ ምክትል ኮምሽነር ዶክተር አለምፀሓይ ፀጋይ "ፍትህ እና ተጠያቂነት በማረጋገጥ ላይ ያሉ መቀዛቀዞች እንዳይቀጥሉ" ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ላለመመለስ ተጠያቂው በትግራይ ያሉ ፖለቲከኞች ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ይገልፃል። ህወሓት ጨምሮ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አመራሮች ደግሞ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚወቅሱ ሲሆን በዚህ ውዝግብ መሃል በሚልዮን የሚቆጠሩት ተፈናቃዮች አምስተኛ ክረምት በመጠልያ ለማሳለፍ ተገደው ይገኛሉ።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ