“በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ዝግጅት የለም” – ህወሓት
ቅዳሜ፣ ሰኔ 28 2017ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) “በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ዝግጅት” እንደሌለ አስታወቀ። ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት ህወሓት እና የትግራይ ጸጥታ አካላት “ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ምንም ዓይነት ዝግጅት እንደሌላቸው” የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወደ ትግራይ በማቅናት “እውነታውን ማየትና መታዘብ” እንደሚችሉ ገልጿል።
ህወሓት ጉዳዩን የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና ባለሐብቶች ጭምር ማረጋገጥ እንደሚችሉ የገለጸው ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ነው።
የህወሓት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 26 ቀን 2017 የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነትን እና የትግራይ ክልልን በተመለከተ ላቀረቡት ማብራሪያ የተሠጠ ምላሽ ነው። ዐቢይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት ቢነሳ ሊኖረው የሚችለውን ጉዳት እየጠቀሱ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለአንዳንዶች ስለ ውጊያ እያነሱ መናገር ምንም ጉዳት የሌለው ሊሆን ይችላል-ስለማይሞቱ። ለወጣት ግን ጉዳት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። “የትግራይ ሕዝብ 100 ፐርሰንት ጦርነት አይፈልግም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ ጦርነት ቢቀሰቀስ ብዙ “ውጊያ እያስተናገደ ነው” ያሉት ዓለም “ደንታው አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከትግራይ ወገን በሥም የጠቀሱት ወገን ባይኖርም ጦርነት ቢቀሰቀስ “የሚያግዙን ሰዎች አሉ፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ” የሚል ስሌት መኖሩን ሲናገሩ ተደምጧል። “እነዚያ ሀገራት እንኳን እናንተን ራሳቸውን ማገዝ አይችሉም። ሞራል፣ ቲፎዞ እና ማገዝ ለየብቻ ነው። ስታዲየም ተቀምጦ ማጨብጨብ እና ኳስ ሜዳ ገብቶ መጫወት ለየብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ህወሓት በዛሬው መግለጫው “የትግራይ ሕዝብ ካሳ እና መልሶ ግንባታ እንጂ በደል እና የጦርነት ማስፈራሪያ የሚገባው አይደለም” ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመሩትን የፌድራል መንግሥት “በአፋር እና በምዕራብ ትግራይ በኩል ታጣቂዎችን በማሰልጠን እና በመደገፍ” ከሶታል። ከዚህ በተጨማሪ “ወደ ትግራይ የሚገባ ነዳጅ በከፍተኛ መጠን ገደብ በማድረግ የክልሉ ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ በመጉዳት” ህወሓት የፌድራል መንግሥቱን ወንጅሎታል።
“በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በብሔራዊ ማንነታቸው ተለይተው እንዲታሰሩ እና እንዲሳደዱ” አድርጓል የሚለው በዛሬው የህወሓት መግለጫ የተካተተ ተጨማሪ ክስ ነው። ፌድራል መንግሥት “በትግራይ ተቋማት እና አመራሮች ላይ የተቀናጀ ጥላሸት የመቀባት ዘመቻ በማካሄድ ለሰላም ሂደቱ ዕንቅፋት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ተጠምዷል” በማለት ህወሓት ወንጅሏል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ፌድራል መንግሥት በጥቅምት 2013 ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የገቡት ለረዥም ጊዜ ከተካሔደ ውዝግብ በኋላ ነበር።
ሁለቱን ተፋላሚ ኃይላት ካሸማገሉ አደራዳሪዎች አንዱ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እንዳሉት በጦርነቱ 600,000 ሰዎች ተገድለዋል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና ፋብሪካዎች የወደሙ ሲሆን ሀገሪቱ የ28.7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶባታል።
የፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ዳግም ወደ አሳሳቢ ውዝግብ ውስጥ የገቡት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ግንኙነት በኃይል በሻከረበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ትግራይ ወደ ግጭት እንዳይገባ፤ ወደ ጦርነት እንዳይገባ በፍጥነት ሥራችሁን አሁን ጀምሩ” የሚል ጥሪ ለሐይማኖት አባቶች አቅርበዋል። ጦርነት “ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም” ያሉት ዐቢይ ኤምባሲዎች፣ ባለሐብቶች እና ምሁራን ጭምር ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዐቢይ ውጊያ “ከተጀመረ ከዚህ በፊት እንደምናውቀው አይደለም። ነገር ይበላሻል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “በእኛ በኩል በትግራይ ክልል አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ህወሓት በበኩሉ “የትግራይ ህዝብም ሆነ አመራሩ የቆዩም ሆኑ አዳዲስ ችግሮች እና ልዩነቶች ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀራረብ በውይይት መፈታት የሚችሉ ናቸው” ብለው እንደሚያምኑ ገልጿል። ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ያቀረቡላቸው “አካላት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ” ጠይቋል።
የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች “የሰላም ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ ገምግሞ ወደ ፊት ለመራመድ የሚያስችል አስቸኳይ ስብሰባ” እንዲጠሩ ህወሓት በድጋሚ ጠይቋል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ