በትግራይ ማንኛዉም አይነት የማዕድን ማውጣት ስራ ታገደ
ሰኞ፣ የካቲት 3 2017በትግራይ ማንኛዉም አይነት የማዓድን ማውጣት ስራ እንዲቆም መወሰኑ
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ የሚከናወን ማንኛዉም አይነት የማዕድን ማውጣት ስራ እንዲቆም ወሰነ። ይህ ሕገወጥ የማዕድናትን ምዝበራ ለመከላከል ያለመ የተባለ ውሳኔ፥ በፌደራል መንግስት እና የክልል አስተዳደር ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወርቅ እና ኮፐር ጨምሮ ሌሎች ማዕድናት የሚያመርቱ አካላት ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ ስራ እንዲያቆሙ የሚያደርግ ነው። በትግራይ የተበራከተው በሕገወጥ መንገድ ማዕድናት የማውጣት ተግባር ለሃብት ብክነት እና ለአካባቢ ብክለት ምክንያት እየሆነ ነው ተብሎ በበርካቶች ሲገለፅ ቆይቷል።
በተለይም በትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላዊ ዞን በስፋት የሚካሄደው የወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት የማውጣት ስራ፥ ከጦርነቱ በኃላ ባለው ግዜ ስፋቱ እየጨመረ፣ ሕገወጥ ተግባራት እየተበራከቱበት፣ ይበልጥ ደግሞ ለአካባቢ ብክለት ምክንያት እየሆነ ስለመምጣቱ በነዋሪዎች እና በሌሎች አካላት ሲገለፅ ቆይቷል። በቅርቡ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር ጥናት በማድረግ ያለው ሁኔታ ይፋ አድርገው የነበሩት በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፥ ማለትም ዓረና ትግራይ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እና ባይቶና፥ በክልሉ የወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናት ምዝበራ መበራከቱ፥ በዚህም የመንግስት ባለስልጣናት እና የጦር መሪዎች እጅ ጭምር አለበት ብለው ነበረ።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ውሳኔ ያስተላለፈው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ፥ በክልሉ የሚደረግ የማዕድናት ማውጣት ስራ ሙሉበሙሉ እንዲቆም መወሰኑ አስታውቋል። ጥር 30 ቀን 2017 ዓመተምህረትለትግራይ መሬት እና ማዕድን ቢሮ ተብሎ፥ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ እንደሚያሳየው በፌደራል መንግስት ይሁን በክልሉ አስተዳደር ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወርቅ እና ኮፐር ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት የማውጣት ስራ የሚከውኑ አካላት ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ ሙሉበሙሉ ስራቸው እንዲቆም ያዟል። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ ማዕድን የማውጣት የስራ ፍቃድ መስጠትም ጭምር እንዲቆም ውሳኔ ተላልፏል።
ይህ ለሕገወጥ ተግባራት የተጋለጠ ማዕድናት የማውጣት ስራ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀርቡ የነበሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ ውሳኔው በአዎንታ ይቀበሉታል። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ ዘግይቶም ቢሆን የማዕድን ማውጣት ስራው እንዲቆም መወሰኑ የሃብት ምዝበራ ለመከላከል ያግዛል ብለዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች በተደጋጋሚ ተፈፃሚ እንደማይሆኑ በማንሳት፥ የዚህ ውሳኔ ተፈፃሚነትም በቀጣይነት እንደሚታይ የሚገልፁት አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ ይሁንና ውሳኔው የሃብት ዝርፍያው ህዝቡ በራሱ እንዲታገለው እንደሚያግዝም ጨምረው ገልፀዋል። በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመርያ አራት ወራት ውስጥ ብቻ 28 ኩንታል ወርቅ ከትግራይ የተለያዩ ወረዳዎች ወጥቶ፥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታውቆ የነበረ ሲሆን፥ ከዚህ ውጭ ደግሞ መጠኑ የማይታወቅ ወርቅ መነሻው ትግራይ አድርጎ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚወጣም ይገለፃል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ