በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተሰጡ ሰሞንኛ አስተያየቶች እና የማስተባበሪያው ምላሽ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2017ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ላብና ደም የተገነባ ከመሆኑም ባሻገር ምንም አይነት የውጪ ፋይናንስ ተዋጽኦ አይደለም ሲል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንምፕ በተደጋጋሚ በሚያሰሙት ንግግር ላይ መልስ እንዲሰጥ በጋዜጠኞች ተጠይቆ ነው መረጃውን ውድቅ ያደረገው፡፡
ግንባታው ከ14 ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ መጪው መስከረም ወር ላይ እንደሚመረቅ የተነገረለት ግድቡ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ አቅም ብቻ የተገነባ ነው ሲል ጽህፈት ቤቱ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
የተደጋገመው የተፈጥሮ አደጋ፣ የህዳሴው ግድብ የማመንጨት ኃይል፤ ግብጽ በሶማሊያ
ዛሬ በጽህፈት ቤቱ ጋዜጠኞችን ጠርቶ መግለጫ የሰጠው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ያለው ግድቡን በገንዘብ መደገፉ እስካሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ም/ዋ/ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር በዚህን ወቅት እንዳሉት በዚህ ዓመት ብቻ ለግድቡ ግንባታ ከ1.7 ቢሊየን ብር የላቀ ገንዘብ ተሰባስቧል፡፡
“በያዝነው 2017 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ብቻ በቦንድ እና በስጦታ በሀገር ውስጥ 1.6 ቢሊየን ብር ከዲያስፖራ 95 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከልዩ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች ታክሎበት በዓመቱ ከህብረተሰቡ 1.6 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 1.7 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል” ብለዋል፡፡ ይህም ከእቅዱ የሰባት በመቶ ብልጫ ያለውና ከአምና አንጻር የወ1 በመቶ ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የጦር የሠራዊቱ ሚና
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ በጠቅላላው በቦንድ ግዢና በስጦታ በሀገር ውስጥ 20.1 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከዳያስፖራ 1.6 ቢሊየን ብር ብሎም ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች 1.7 ሚሊየን ብር በአጠቃላይም እስከ ዘንድሮ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 23.6 ቢሊየን ብር ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ መዋሉነም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል፡፡
ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ሲሰናበቱ ዶናልድ ትራምፕ ተፎካካሪያቸውን እየጠበቁ ነው
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጓን በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸውን ተከትሎ በዚህ ላይ ማብራሪያውን እንዲሰጥ በጋዜጠኞች ተጠይቆም፤ ግዙፉ የአፍሪካ ግድብ መቶ በመቶ የተገነባው “ያለምንም የውጭ እርዳታም ሆነ ብድር በራስ አቅም” ነው በማለት የትራምፕን ንግግር አስተባብሏል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ማንም አካል ተነስቶ እኔ ነኝ የሰራሁት ቢል ያለማስረጃ ምንም ማድረግ አይችልም ያሉት የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር ለግድቡ ግንባታ ምንም አይነት የውጪ ገንዘብ ድጋፍም ሆነ ብድር አልገባበትም ብለዋል፡፡ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መንግስት በራሱ መንገድ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መልስ ልሰጥበት እንደሚችልም ጠቁመው “አፍራሽ” ያሉት መረጃ ላይ በሰጡት ምላሽ ግን እውነታው ግድቡ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ የስራ ውጤት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምሀርና የጂኦፖሊቲክስ ተመራማሪ፣ የህዳሴ ግድብና ሌሎች ውሃነክ የሆኑ ካባቢዊ ላይ በአማካሪነት የሚሰሩ ዶ/ር ያዕቆም አርሳኖ፤ “እኛ እንግዲህ ይሄንን ግድብ ከመነሻው ጀምሮ እንደ ተከታተልነው እንደምናውቀውም ግድቡ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ትብብር መንግስት ተባብረው የገነቡትና አሁን ማጠቃለያ ላይ የደረሰ ግድብ መሆኑን ነው” ብለዋል፡፡ “አሜሪካኖች ወይም ሌሎች ወገኖች ግድቡ በኛ ገንዘብ ነው የተሰራው ሲሉ ወይ ስለሌላው ህዳሴ ግድብ እያወሩን መሆን አለበት አለበለዚያም ከሉላ ወገን ጋር ማስተላለፍ የፈለጉት መልእክት አለ ማለት ነው” ያሉት ዶ/ር ያዕቆም ይህ ሁሉ ግን እውነታውን ልቀይር እንደማይችል ገልጸው ግድቡ በኢትዮጵያውን ርብርብ ብቻ እንጂ በሌላ ወገን በተበረከተ ገንዘብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባሁኑ ወቅት ግድቡ መጠናቀቁ ከተገለጸ በኋላ የሚሰበሰበው ገንዘብን በተመለከተ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ይህ የፕሮጀክቱ ግንባታ ገንዘብ አሰባሰቢ በአዋጅ እስኪዘጋ እንደሚቀጥልና ከፕሮጀክቱ ግንባታ ባሻገር ለተፋሰስ ስራዎችም ተጨማሪ የገንዘብ አቅብ እንደሚስፈልግ ጠቁሟል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ