በተፈጥሮ መንገድ ደንን የመመለሱ ጥረት የጋና ተሞክሮ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2017
የተራቆቁ አካባቢዎችን በተፈጥሮ መንገድ ዳግም በዛፎችና ቁጥቋጦዎች እንዲሸፈኑ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣቱ ትኩረትን ስቧል። በተለይም የምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጋና ተሞክሮ ለሌሎችም ምሳሌነቱ እየተነገረለት ነው። በሰሜናዊ ጋና የአየር ንብረት ለውጥ፤ የደን ጭፍጨፋ እና ሰደድ እሳት ተረባብረው ለምለሙን አካባቢ ጠፍ ሜዳ አድርገውት ቆይተዋል። አሁንስ? የዶቼ ቬለዎቹ ቮልፍ ጉብሃርድ እና ማክስዌል ሱኩ በቦታው ተገኝተው በፊልም ደግፈው ያቀረቡትን እናካፍላችሁ።
ተቆርጠው ጉቷቸው ብቻ የቀረ ትናንሽም ሆኑ ትላልቅ ዛፎች ሁሉ ፈጽመው ሞተዋል፤ ወይም ዳግም አያንሰራሩም ብሎ መወሰን አይቻልም። አንደኛውን ሥራቸው ተመንግሎ ካልተወገዱ በቀር ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው አንዳንዶቹ እንደገና የመብቀል እድላቸው ሰፊ ነው። እናም የጥቂት ዓመታት ጊዜ ካገኘ ጠፍ መሬት እንደገና በጤናማ ዛፎች ሊሞላ እንደሚችል ሰሜናዊ ጋና ውስጥ የሆነው ዓይነተኛ ማሳያ ይሆናል።
እንዴት? ጋና ውስጥ የተሠራውን ለምሳሌነት የሚበቃ ተሞክሮ እናካፍላችሁ።
የተራቆተው አካባቢ ገጽታ
በሰሜናዊ ጋና ነዋሪ የሆኑት የያመሪጋ ማኅበረሰብ ሴቶች በተንተን ብለው የሚገኙትን የዛፎች ትናንሽ ቅርንጫፎች ሆነ ብለው ይቆርጣሉ፤ ይህን በማድረጋቸው ታዲያ ጠንካሮቹ ቅርንጫፎች የተሻለ የጸሐይ ብርሐን፤ አየር እና ጠቃሚ ንጥረነገሮችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል። እንዲህ ያለው ተፈጥሯዊ የዛፎች እንክብካቤ ዘዴ ዛፎቹ ያለምንም ተጨማሪ ነገር በጤናማ መንገድ እንዲያድጉ እና አካባቢውን እንዲሞሉ እድሉን ያመቻቻል። በዚህ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን የመሸፈን ጥረት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ሴቶች አንዷ ይናማያ ማጋዚ የያመሪጋ ማኅበረሰብ ሴቶች ቡድን አባል ናቸው።
«አስቸጋሪ ነበር። ምን ወንጀል መጽመን ነው አካባቢው እንዲህ እንዲራቆት የሆነው በማለት እናስብ ነበር። ሰፋፊ እርሻዎችን ናቸው ያሉን ነገር ግን ምርቱ ሁሌም በጣም ትንሽ ነበር። በርካታ ሰዎች ከዚህ አካባቢ ተሰደዋል፤ እኔም እንደዚያ ለማድረግ አስብ ነበር።»
እውነትም የቀድሞው የአካባቢው ገጽታ ከአሁኑ ጋር በምን አይመሳሰልም። ጋና ውስጥ በርካታ አካባቢዎች ከዛፍ ተራቁተው እልም ያለ ሜዳ እስከ መሆን ደርሰው ነበር። የደን ጭፍጨፋ በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ተጽዕኖውን አሳርፏል። የሀገሪቱ ሦስት አራተኛ ግዛት በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች ሰዎች በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ በሚያደርሷቸው ጉዳቶች ማለትም ከመጠን በላይ ለማገዶ ዛፎችን የመቁረጥ፤ እንዲሁም አዳኞች ሆን ብለው እንስሳትን ለማስደንበር ጫካ ውስጥ በሚያስነሱት ሰደድ እሳት ምክንያት ለምለም የነበረው አካባቢ ለበረሃማነት እንዲጋለጥ ሆነ።
የደን ሀብት እንዴት ይመለሳል?
በተመድ ድጋፍ ጋና እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ.ም. ድረስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የተራቆተውን መሬት ዳግም እንዲያገግም ለማድረግ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ለመትከል አቅዳለች። አንዳንዶች ግን ተነሳሽነቱን እምብዛም አይቀበሉትም። ከእነዚህ አንዷ የጋና የደን ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ግሎሪያ ኩኩርጂ አደይጋ በደፈናው ችግኞችን በተገኘው ስፍራ ሁሉ እየተከሉ ደን እናለማለን የሚባለውን ለምን እንደማይቀበሉት እንዲህ ያስረዳሉ።
«ትናንሾቹን ችግኞች አፍልተዋል። መልካም፤ ግን እነዚህን ችግኞች ከፍተኛ የሙቀት መጠን ባለበት ስፍራ እንዲሁም ድርቅ በሚጠናበት አካባቢ እንደው በተገኘበት ሁሉ ይተክላሉ። በዚያ ላይ ደግሞ የከብቶች መንጋ ይግጣቸዋል። ይህ ማለት ጨቅላ ሕጻንን ወስዶ ከተማ መካከል እንደመጣል እና እዚያው ኑሮህን በራስህ ኑር እንደማለት ነው። ወደዚች ምድር አምጥቼሀለሁ፤ አንተ ደግሞ እራስህን ችለህ ኑሮህን ግፋ እንደማለት። እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሕይወት መኖር በራሱ ቀላል አይሆንም።»
ጋና ውስጥ ብቻም አይደለም ኢትዮጵያን ጨምሮ በየጊዜው ወቅት እየተጠበቀ በሚሊየኖች የሚቀጠር ችግኝ ስለመትከል ይወራል። የአንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ዜናም ሲሆን ይታያል። ግን በየዓመቱ የተተከሉት ችግኞች ከወራት በኋላ የደረሰበት አይነገርም። ዜናው ግን በየዓመቱ ይደጋገማል።
የሰሜናዊ ጋና አካባቢ ነዋሪዎቹ የያመሪጋ ማኅበረሰብ ሴቶች የተከተሉት ስልት ከሌሎች ይለያል። ከዓመታት በፊት አካባቢያቸው ተራቁቶ መሬቱም አፈሩ ተሸርሽሮ ድንጋዮች ገጥጠው ይታዩበት ነበር። አሁን የአካባቢው ማኅበረሰብ ባደረገው ተፈጥሮን የተከተለ የደን ክብካሄ ሂደት ከ10 ዓመታት በፊት የነበረው ገጽታ ተለውጦ አረንጓዴ ለብሷል። ሁኔታውም የተራቆቱ አካባቢዎች ዳግም እንደሚያንሰራሩ ጥሩ ማሳያ ሆኗል።
የጋና ተሞክሮ
መጀመሪያ ላይ ሴቶቹ ሕያው የሆኑትን የዛፍ ጉቶዎች ቆረጡ። አሁን ግን በተፈጥሮ መንገድ ዘራቸው በአእዋፍም ሆነ በእንስሳት በያ,በት ተበትኖ የበቀሉትን የትናንሾቹን ዛፎች ቅርንጫፎች በጥንቃቄ ይቆርጣሉ። አላማው ዛፎቹ በጤናማ እና ፍሬ በሚያፈሩበት መንገድ ማደጋቸውን ማረጋገጥ ነው። ጠፉ መሬት ዳግም በደን እንዲሸፈን ማድረግ ለአየር ንብረት በመጠኑም ቢሆን አዎንታዊ ሚና የመጫወት እድል አለው፤ አካባቢው እርጥበታማ አየር እንዲኖረው፤ አፈሩን ለማቀዝቀዝ እንዲሁም ዝናብ በተደጋጋሚ እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
ሂደቱም አርሶ አደሮች አካባቢን በተፈጥሮ መንገድ የሚያድሱበት ስልት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ FMNR በመባል ይታወቃል። በጎርጎሪዮሳዊው 2010 ዓለም መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ዎርልድ ቪዥን ጋና ውስጥ ያስተዋወቀው ፕሪጀክት ነው። ሳሙኤል አባሲብ የዎርሊድ ቪዥን ጋና ባልደረባ ናቸው።
«በFMNR ጋና እሳቤ አማካኝነት ማኅበረሰቡ ይህ ስፍራ ዳግም አንሰራርቶ ደን እንዲለብስ ማድረግ ችሏል። ምንድነው ያደረጉት? በዋናነት ያደረጉት እራሳቸን ለሥራው አነሳሱ፤ ወጡናም ብቅ ብቅ ያሉትን ቁጥቋጦዎች በመጠኑ ቆረጡ፤ በዚያም ላይ በሰደድ እሳት እንዳይጋዩ ጥበቃን ሲያደርጉላቸው ከረሙ። ከዚያም በጥቂት ዓመት ውስጥ ያ ቁጥቋጦ የነበረበት ቦታ በደን ተሸፈነ። ስለዚህ የFMNR ሃሳብ ነው። እዚህ የምትመለከተው ሁሉ በተፈጥሮ መንገድ ክብካቤ ያገኘ እንጂ የተተከለ ዛፍ አይደለም።»
እንዲያም ሆኖ ይህንን ስልትም የሚተቹ አልጠፉም። በአካባቢው የበቆሎ እርሻ ባለቤት የሆነው አርሶ አደር ሞሰስ አያምጋ ከተቺዎቹ አንዱ ነው። በቆሎ አምራቹ አያምጋ ከዚህ በጣም የተለየ የእርሻ ስልት እንዳለው ነው የሚናገረው።
«በሥራችን ጣልቃ እየገቡ ነው በእርሻችን ቦታ ዛፎችን መቁረጥ አትችሉም እያሉን ነው። ኬሚካሎችና ትራክተርም ሳትጠቀም፤ የእርሻ መሬትህንም ሳትመነጥር እንዴት ነው እርሻ ማረስ የምትችለው? ዛፎችን ሳትቆርጥ እንዴት ነው እህልም ማምረት የምትችለው?»
ሲልም ይጠይቃል። ሆኖም ግን ለያመሪጋ ሴቶች ፕሮጀክቱ ኑሯቸውን መግፋት የሚችሉበት ፍራፍሬና የኦቾሎኒ ዘሮችን ማምረት አስችሏቸዋል። ከኗሪዎቹ አንዷ ቴንዳማ ዱዉሪ፤
«FMNR ወደ ማኅበረሰባችን ከመምጣቱ በፊት እነዚህ በእጄ የያዝኳቸውን የመሰሉ ፍራፍሬዎች በዚህ አካባቢ አልነበሩም። የሺያ ለውዝ አልነበረም። ስቃይና ረሀብ ነበር፤ ሕይወታችን አሳዛኝ ነበር። ልጆቻችን በርካታ ችግርን ይጋፈጡ ነበር። ሌላው ቀርቶ የማገዶ እንጨት ማግኘት ሁሉ ችግር ነበር። አሁን ግን ሁሉም ተመልሶ በቅሏል፤ እኛንም እያስደሰተን ነው።»
የሴቶቹን የልፋት ውጤት ለመቋደስ ወንዶቹም ቢሆኑ ዛፎቹን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። ዛፎችን ሊጎዳ ሲሞክር የተያዘ ሁሉ ቅጣት ይጠብቀዋል፤ አንዳንዴ በገንዘብ አንዳንዴም በዓይነት ቅጣቱን ይከፍላል። የጋናዋ ያመሪጋ ማኅበረብ ሴቶች አሁን በርካቶችን የሚያነቃቁ ምሳሌዎች ሆነዋል። እንደ እነሱ የተሰባሰቡ ሴቶች በሰሜናዊ ጋና አካባቢ በ90 ቡድኖች ተዋቅረዋል። በእነሱ አማካኝነትም በየጊዜው ከ45 ስኩየር ኪሎሜትር በላይ የተራቆተ አካባቢ መልሶ ማገገም አረንጓዴ እንዲለብስ እየተደረገ ነው። ሰሜናዊ ጋና ውስጥ በተፈጥሮ መንገድ የተራቆተ አካባቢ እንዲያገግም የሚደረግበትን ስልት ያስቃኘን የዕለቱ ጥንቅር በዚሁ አበቃ። በየአካባቢያችሁ የሚደረግ ተመሳሳይ ጥረት ይኖር ይሆን? መረጃው አጋሩን ።
ሸዋዬ ለገሠ /ቮልፍ ጉብሃርድና ማክስዌል ሱኩ
አዜብ ታደሰ