ስልኮቻችን በመረጃ መንታፊዎች እጅ መውደቃቸውን እንዴት እናውቃለን?
እሑድ፣ ኅዳር 11 2015
ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ቪዲየዎች፣ የጽሁፍ መልእክቶች፣ የይለፍ ቃሎች እና ሚስጥራዊ እና ለሌሎች ማካፈል የማንፈልጋቸው አድራሻዎች የመሳሰሉ ስለእኛ በርካታ ግላዊ መረጃዎችን ይይዛሉ። ነገር ግን እነዚህ የግል መረጃዎቻችን በመረጃ መንታፊዎች ዕጅ ሊወድቁ የሚችሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው።ለመሆኑ ይህ መሰሉ የመረጃ ስርቆት አደጋ ሲያጋጥም ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ላይ ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶቹ ምንምን ናቸው? ችግሩ ከተፈጠረስ መፍትሄው ምንድነው? የትኞቹ እንቅስቃሴዎችስ ለችግሩ ሊያጋልጡን ይችላሉ?።የዛሬው የሳይንስ አና ቴክኖሎጅ ትኩረት ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍም ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።በተለይ የስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን በርካታ ስራዎችን በመከወን ከዕለት ተዕለት ኑሯችን ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ሆነዋል።ከዚህ የተነሳ በርካታ ግላዊ መረጃዎቻችን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ይቀመጣሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በስልኮች ላይ የሚደረገው መረጃ የመመንተፍ አደጋ እየጨመረ መጥቷል።
የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ባለፈው ጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሳይበር ጥቃቶች በ2022 ሶስተኛ ሩብ ዓመት ከ2021 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ28 በመቶ ጨምሯል።የሞባይል ስልክ ተጋላጭነት ደግሞ በ 2022 ከ 10 የሳይበር ደህንነት ስጋቶች አንዱ ሆኗል። በወሎ ዩንቨርሲቲ መምህር እና የሶፍት ዌር ማሀንዲስ የሆኑት አቶ ሶሎሞን አይዳኝ እንደሚሉት ከአጠቃቀም መጨመር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያም ችግሩ እየጨመረ መጥቷል።
«አንድ የሞባይል ስልክ በብዙ መንገዶች ሊጠቃ ይችላል።ልክ ያልሆኖ የኔትወርክ አጠቃቀሞችን ጨምሮ እና፤የተገኙትን ዋይፋዮች አክሰስ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ስልኮች ለጥቃት ይጋለጣሉ።በመሰረቱ አሁን ላይ ሞባይል ስልካችን ባንካችን ነው «የሶሻል ኔትወርክ» መጠቀሚያችን ነው።ብዙ ስራዎችን ለመስራት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ለማከናወን የምንጠቀመው ስልካችንን ነው።ምናልባት እንደ ኢትዮጵያ እንደሀገር ብናወራ በቅርቡ እንደ መብራት ውሃ የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በስልክ እንዲገኙ ሆነዋል።ከዚህ ጋር ተያይዞ መንታፊዎች ወይም ሀከር ብለን የምንጠራቸው ሰዎች እነዚህን መረጃዎች አላግባብ ለመጠቀም ብዙ ጊዜ ወደ ስልኮች ጥቃት ይሰነዝራሉ።» በማለት እያጋጠመ ያለውን ችግር ገልፀዋል።
ስልኮቻችን በመረጃ መንታፊዎች ዕጅ ሲወድቁ የሚያሳዩአቸው ምልክቶች
በመሆኑም ይህ መሰሉ ችግር ሲያጋጥም ቪዲየዎች፣ የጽሁፍ መልዕክቶች፣ የይለፍ ቃሎች እና ሚስጥራዊ የሆኑ እና ለሌሎች ማካፈል የማንፈልጋቸው የግል መረጃዎቻችን በመረጃ መንታፊዎች ዕጅ ሙሉ በሙሉ ከመውደቃቸው በፊት ጉዳቱን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተጠቃሚዎች ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በዚህ አደጋ ላይ መሆናቸውን እንኳን ላያውቁ ይችላሉ።አቶ ሶሎሞን እንደሚሉት እንደ መረጃ መንታፊው ፍላጎት እና አቅም ስልኮቻችን የተለያዩ የአደጋ ምልክቶች የሚያሳዩ ቢሆንም የተለመዱ እና የጋራ ምልክቶች ግን አሉ። በመሆኑም አንድ ተጠቃሚ የሚከተከተሉትን ምልክቶች በስልኮቹ ላይ ካስተዋለ የግል መረጃው አደጋ ላይ መሆኑን መገንዘብ አለበት።
«ስልካችን በመንታፊዎች እጅ ሲወድቅ «ኮመንሊ»ያሳያል ተብሎ የሚጠበቁ ባህሪዎች አሉ።አንደኛው ልክ ያልሆኑ ማስታወቂያዎችን ቶሎቶሎ ማምጣት ነው።ምናልባትም በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ማስታወቂያዎች ይሆናሉ።እነሱን ማስታወቂያዎች ያሳያል።ሁለተኛው እኛ «ሜሴጅ» ሳንልክ እንዲሁ በራሱ ሊፅፍ እናሊልክ ይችላል።ሊደውል ይችላል። ተመሳሳይ የሆኑ «ሩቲኖችን» ተከትሎ የሆነ ቦታ ስንነካ ወዲያው ሜሴጅ ውስጥ ገብቶ መልዕክት መላክ መጀመር ሁለተኛው ባህሪ ነው።ሌላኛው «ሀይ ዳታ ዩዜጅ» ይኖረዋል።ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በቀን ሰፋ ያለ የዳታ አጠቃቀም ይኖረዋል።ከተለመደው በዛ ያለ ቶሎቶሎ «አክቲቪቲዎች» ውስጥ የመግባት ምልክት ያሳያል ማለት ነው።ከዚያ ውጭ ከባትሪ ጋር ይገናኛል።በተለምዶ ከነበረው ባትሪ በፍጥነት ማለቅ።»ካሉ በኋላ ስልኩ ሊሞቅ እንደሚችልም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ከተለመደው ፍጥነት መቀነስ እና ጊዜ የመውሰድ ወይም ጭርሱኑ ለሚታዘዘው ነገር ምላሽ አለመስጠት፣ባልተለመደ ሁኔታ ስልካችን መጥፋት እና ዳግም መጀመር ፣ከእኛ ያልሆኑ የፍለጋ ታሪኮች በስልኮቻችን ላይ መታየት /Browser History Mismatch. / ከመጠን በላይ የሆነ የዳራ ውሂብ አጠቃቀም/Excessive Background Data Usage/፣እንዲሁም እኛ ያልጫናቸው እና የማይታወቁ መተግበሪያዎች በስልኮቻችን ላይ መገኘትም ሌላው ምልክት መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ።
«አፕሊኬሽኖችን እኛ እስካልጫናቸው ድረስ ከየት መጡ ብሎ አለመጠየቅ አንድ ለችግር ተጋላጭነትን ያሳያል።እነዚያ አፕሊኬሽኖች ምናልባትም ለሶስተኛ አካል መረጃ ሊያቀብሉ የሚችሉ ስለሚሆኑ በተቻለ መጠን ስላካችን ላይ ያሉ «አፕሊኬሽኖችን» ማወቅ ።ስለዚህ አንድ ችግር ተደርጎ የሚወሰደው እኛ ያልጫናቸው መተግበሪያዎች ወይም ከየት እንደመጡ የማይታወቁ «አፕሊኬሽኖች» ስልካችን ላይ መገኘት ጭምር ነው።ሌላው በሶሻል ሚዲያ «አካዉንቶቻችን« ያልተለመዱ «አክትቪቲዎቻችን» ማየት እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።ከዚያ ውጭ ሜሴጅ አለመላክ ስልክ አለመደወል እንደ ችግር ይጠቀሳሉ።»ካሉ በኋላ እንደ መረጃ መንታፊው የእውቀት መጠን ከዚህ የበለጠ የተወሳሰበ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።
ችግሩን ለመፍታት መደረግ ያለባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች
አቶ ሰለሎምን እንደሚሉት ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች በስልኮቻችን ላይ ሲታዩ የይለፍ ቃል መቀየርን ጨምሮ የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
«አንደኛው ከእኛ እውቅና ውጭ የተጫነ አፕሌኬሽን ካለ ማረጋገጥ እና ተጭኖ ከተገኘ ከስልካችን ላይ ማጥፋት።ሁለተኛው ስልኮቻችንን «ፕሮቴክት« የሚያደርጉ አንቲ ማልዌር/Anti-Malware / አፕሊኬሽኖችን አሉ እነሱን መጠቀም ነው።ሶስተኛው ስልካችንን ወደ ነበረበት ወደ ኋላ ለመመለስ «ሪሴት» ማድረግ ነው።በፋብሪካ ደረጃ የተሰራበት «ሌብል» እስኪያገኝ ድረስ።ስልኩን «ሪሴት» አድርጎ ወደ «ኦርጂናል» ቦታው መመለስ ነው።ሌላኛው«ፓስ ወርድ» መቀየር ነው።ከዚያ ውጭ አንድ «ሀከር» ወይም መንታፊ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ሌሎችንም በስልኩ ውስጥ ያሉ «ኮንታክቶችን»የተሳሳተ መረጃ በመላክ ማጥቃት ስለሚሆን ስልካቸው በመንታፊ ስር መሆኑን ስልኮቻቸው ለሚገኙ ሰዎች ደውሎ ማሳወቅ ።በዚያ ስልክ ምንም አይነት ነገር ቢላክ ከሱ ቁጥጥር ወጭ መሆኑንም ማሳወቅ ነው።ሌላኛው ለ«ኮንታክት ሰርቪስ ፕሮቫይደር» ማሳወቅ ነው።» ማለትም አገልግሎት ለሚሰጡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ላሉ ተቋማት ማሳወቅ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመረዳት የስልኮቻችንን ባህሪ በአግባቡ ማወቅ
የመተግበሪያ አጠቃቀምን በተመለከተም ስልኮቻችን ላይ የምንጭናቸውን መተግበሪያዎች ከሚሰጡት አገልግሎት ጋር የማይገናኝ የግል መረጃ ፈቃድ በሚጠይቁበት ወቅት በአግባቡ ማጤን፣ እንዲሁም የግል መረጃዎቻችንን በተለዬ የመለያ እና የይለፍ ቃል በአግባቡ እና በጥንቃቄ ማስቀመጥ ተመሳስለው ከተሰሩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ከመጠቀም መቆጠብ እና የማይታወቅ እና ነፃ «ዋይፋይ»ን ከመጠቀም መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑንም ባለሙያው መክረዋል።ከሁሉም በላይ ግን የምንጠቀመውን ስልክ በአግባቡ ማወቅ እንደ አቶ ሰለሞን ችግሩን ለመከላከል የበለጠ ይረዳል።
«እኔ በድጋሚ አሁንም አፅንኦት ሰጥቼ መናገር የምፈልገው ማንኛውም ሰው የተለየ ባህሪ እንዳለው የሚያስተውለው ስልኩን የሚያውቅ ሰው ብቻ ነው።የማያቅ ሰው የስልኩ ባህሪ መስሎት ችግሩን ይዞ ይቀጥላል።መረጃን ሰብስበው መላክ የሚችሉ ሮቦቶች አሉ።እነዚህ «አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ» የሆኑ «አፕሊኬሽኖች»በቀላሉ የኛን መረጃ እየላኩ በዕለት ተዕለት የምንሰራውን ምስልም ሆነ የስልክ ኮንቨርሴሽኖች የሜሴጅ አገልግሎት ለሰው አሳልፈው የሚሰጡ መተግበሪያዎች እየመጡ ነው።ስለዚህ በዚህ ዘመን እኛ ልንጠነቀቅ የሚገባን ነገር የምንጭነውን አፕሊኬሽን ማወቅ፣የማናቃቸው ከሆኑ ከባለሙያ ጋር በመነጋገር ማስወገድ፣ስልካችንን ልክ የሰው ልጅ የጤና ምርመራ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ዛሬ መረጃ ከዚያ በላይ እያገለገለ ነው ያለው። ስለዚህ ስልካችንን እና ባለሙያ ካልሆን በጣም ለምናምናቸው ባለሙያዎች ስልካችንን «ቸክ» እንዲያደርጉልን ማድረግ። በተለይ ለታዋቂ ሰውች መረጃቸው አደጋ ለሚያስከትል የመንግስት ባለስልጣናት ይህንን ምክር አብሬ መለገስ እፈልጋለሁ።» በማለት ገልፀዋል።
ሙሉ ዝገጀቱነ የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ