በሴቶች ላይ በበይነመረብ የሚፈፀም ጥቃት፤ እያደገ የመጣው የዲጂታል ዘመን ስጋት
ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2017
በፍጥነት እያደገ የመጣው የዘመናችን የዲጂታል ቴክኖሎጅ የሰዎችን መስተጋብር ቀላል እና የተፋጠነ በማድረግ ፣ የትምህርት እና ኢኮኖሚያዊ እድሎችን በመፍጠር ረገድ እጅግ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝቷል።በዚያው ልክ ደግሞ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲጨምሩም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል በሚል ይተቻል። የተባበሩት መንግስታት በዓለም ላይ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሶ በጎርጎሪያኑ ታህሳስ 2024 ዓ/ም ባወጣው መረጃ ከ16 እስከ 58 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች በበይነመረብ ጥቃት ይደርስባቸዋል።
በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በበይነመረብ ሚፈጸም ጥቃት ሰፊ ጉዳይ ሲሆን፤ ስማቸውን ሳይገልፁ የዲጂታል መድረኮችን ተደራሽነት ያለአግባብ የሚጠቀሙ በርካታ ጎጂ ይዘቶችን ያጠቃልላል።
በጎርጎሪያኑ ያለፈው መጋቢት 8 ቀን የተከበረውን የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ተከትሎ የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱትም በሴቶች ላይ በበይነመረብ የሚደርስ ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁንም እየጨመረ መጥቷል።ጥቃቱ በተለይ በማኅበረሰብ ውስጥ ድምፃቸውን በሚያሰሙ አንቂዎች እና ፖለቲከኛ ሴቶች ላይ ይበረታል።በተለይ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እነዚህ ሴቶች ላይ ስድብ እና ዘለፋ እንዲሁም የጥላቻ እና የጥቃት ማስፈራሪያ ያጋጥማቸዋል።
ዶክተር ማህሌት ሽመልስ ከመደበኛ ስራዋ በተጨማሪ በፆታ እኩልነት ላይ በግሏ የማንቃት ስራ የምትሰራ ወጣት የጤና ባለሙያ ነች።በአንድ ወቅት እርሷም በምታነሳቸው ሀሳቦች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ ጥቃት አጋጥሟታል።ዶክተር ማህሌት እንደምትለው ይህ መሰሉ የበይነመረብ ጥቃት ህብረተሰቡ ለሴቶች ካለው አመለካከት የሚመጣ ነው።
ከኅብረተሰቡ ነባር አመለካከት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችም ለሴቶች የበይነመረብ ጥቃት መጨመር ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውንም ታስረዳለች።
ለጥቃቱ መጨመር የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሚና
ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በዓለማችን አዲስ ክስተት ባይሆንም፤ ጥቃቱ ወደ ዲጂታሉ ዓለም መዛመቱ ግን መጠኑን እና ተፅእኖውን ከፍ አድርጎታል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢሜል እና የቻት ሩም መምጣትን ተከትሎ፤ሴቶች በሳይበሩ ዓለም የክትትል እና የትንኮሳ ኢላማዎች ሆነዋል። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መበራከት ደግሞ እነዚህ ስጋቶች እንዲስፋፉ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶችን ለማዋከብ፣ለመተንኮስ እና ለማዋረድ ለጥቃት አድራሾቹ አጋዥ መሳሪያዎች ሆነዋል።እነዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ በሴቶች ላይ የሚንጸባረቁ የተዛቡ አመለካከቶችን ደግመው በማንፀባረቅ ጥቃቱ እንዲባባስ ያደርጋሉ።
ለዚህም እንደ ዶክተር ማህሌት ገለፃ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎቹ በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የይዘት ክትትል አነስተኛ መሆን ችግሩን የበለጠ እንዲሰፋ አድርጓል።
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የበይነመረብ ጥቃቶች ገፅታ
የበይነመረብ ጥቃት ሴቶችን ዝም በማሰኘት ወይም በማስፈራራት ላይ ያነጣጠሩ ስድብ እና ዛቻዎችን በመፃፍ በሰዎች ዘንድ ሞገስ ማሳጣት እና ማስጠላትን፣ ሴቶችን ለማዋረድ ወይም ለመቆጣጠር የግል ምስሎችን አላግባብ መጠቀምን (የበቀል ፖርኖን)፡ ያለፈቃድ ማጋራትን፣ እንደ አድራሻዎች እና ስልክ ቁጥሮች ያሉ የግል መረጃዎችን በይፋ በመልቀቅ በገሃዱ ዓለም አደጋ እንዲፈጠር ማድረግን ያጠቃልላል።በተጨማሪም የሴቶችን ምስሎች መያዣ በማድረግ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደድ፣ፍርሃት እና ጭንቀት የሚፈጥር የማያቋርጥ የበይነመረብ መስተጋብር፣ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግም ከጥቃቱ ገፅታዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
የሰውሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሴቶችን ፎቶ እና ቪዲዮዎች በሀሰት ባልተገባ መንገድ ማቀናበር፣ በስርዓተ-ፆታ ላይ የተመሰረተ የጥላቻ ንግግር፡ ሴቶችን ለማዋረድ ያለመ የተሳሳቱ ወይም አድሎአዊ ይዘቶችን መስፋፋት።የሴቶችን እርቃን ፎቶዎች በመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ወይም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማሰራጨትን ይጨምራል።ያም ሆኖ ይህ መሰሉ በሴቶች ላይ የሚደርስ የበይነመረብ ጥቃት በኢትዮጵያ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ብዙም ትኩረት ሲሰጠው አይታይም።ዶክተር ማኅሌት ችግሩን አቅልሎ ከማየት የመጣ ነው ትላለች።
የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ጥቃቱን በማባባስ
የቴክኖሎጂ በተለይም የሰውሰራሽ አስተውሎት (AI) እድገት የበይነመረብ ጥቃት ውስብስብነትን እንዲጨምር አድርጓል። ወንጀለኞች በሰውሰራሽ አስተውሎት ታግዘው ከሞራል ውጭ የሆኑ ምዕናባዊ የምስል እና የቪዲዮ ይዘቶችን ለመስራት ዲጅታል መሳሪያዎች ቀላል አድርገውላቸዋል። ይህም በእውነት እና በሐሰት መካከል ያለውን ድንበር የሚያደበዝዝ ይሆናል። የዚህ ዓይነት በደል ታዲያ የጥቃቱ ሰለባዎች ብዙውን ጊዜ እነዚህን ትክክለኛ የሚመስሉ የሀሰት ይዘቶች ለማስተባበል ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል።ይህም ጭንቀታቸውን የበለጠ ያባብሰዋል።
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችም ጎጂ ይዘቶችን በፍጥነት ለማሰራጨት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው።ለተጠቃሚዎች ለተሳትፎ ቅድሚያ የሚሰጡት የእነዚህ ዲጅታል መድረኮች ስልተ ቀመሮችም ሳያውቁት ጎጂ መልዕክቶችን ጭምር በማጉላት፤ በሰፊው እንዲሰራጩ ያደርጋሉ።
በአንፃሩ እነዚህ ዲጅታል መድረኮች የመልዕክቶቹን ምስጢራዊነትን በመጠበቅ እና የበይነመረብ ጥቃት አድራሾች ማንነታቸውን ሳይገልፁ እንዲጠቀሙ በመፍቀድ ከህጋዊ ተጠያቂነት እንዲያመልጡ ያደርጋሉ።
በዚህ ሁኔታ አጥፊዎች ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦችን ለመጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተራቀቁ መንገዶችን እያገኙ ነው። ከዚህ አንፃር በሴቶች ላይ የሚደርሰው የበይነመረብ ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አሳሳቢ ሆኗል።
በተጨማሪም የበይነመረብ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ድንበር አልፎ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ ያደርገዋል። ደካማ ወይም ወጥነት የሌላቸው የህግ ማዕቀፎች ችግሩን በማድበስበስ፤ብዙ ተጎጂዎች ፍትህ ሳያገኙ እንዲቀሩ ያደርጋሉ።
ዶክተር ማኅሌት ችግሩን ለማቃለል ይረዳሉ የምትላቸውን አንድአንድ አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ጠቁማለት።
ጥቃቱ ተፅዕኖ በሴቶች እና በማህበረሰቡ
የበይነመረብ ጥቃት በተጠቂዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፣ ብዙዎችን ጭንቀት፣ እና ድብርትን ለመሳሰሉ የሥነልቡና ጉዳት ይዳርጋቸዋል።በኢኮኖሚ ረገድም አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በተለይ የወጣቶች ለእንደዚህ አይነት ጥቃት መጋለጥ ትምህርታቸውን እና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ይጎዳል። ይህም በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ጉዳት ያስከትላል።
በበይነመረብ የሚደርስ ጥቃት ከተጎጅዎች አልፎ ወደ ማህበረሰቡ እሴት ይዘልቃል። የተባበሩት መንግስታት መረጃ እንደሚያሳየው በአውሮፓ ህብረት ውስጥ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በበይነመረብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ኢኮኖሚያዊ ወጪ በዓመት 49-89 ቢሊዮን ዩሮ ይገመታል ፣ይህም የሀብት ብክነትን ያስከትላል።የሴቶች የእኩልነት መብትም ይጥሳል።
የበይነመረብ ጥቃት የሴቶች ድምፅ እንዳይሰማ በማፈን ረገድም እንዲሁ አሳሳቢ ነው።እንደ ድርጅቱ ዘገባ 30% የሚሆኑ ሴት ጋዜጠኞች በዚሁ ጥቃት ሳቢያ እራሳቸውን ሳንሱር ያደርጋሉ።በርካታ ወጣት ሴቶችም ተመሳሳይ ትንኮሳን በመፍራት በፖለቲካ ወይም በአንቂነት እና በጋዜጠኝነት ሙያ ለመሰማራት ስጋት እንዳላቸው የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል።
እነዚህ አዝማሚያዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የሴቶችን ድምጽ በመቀነስ፤ለጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ሂደቶች አስፈላጊ የሆነውን የብዝሃነት ድምፅ ያፍናል።
በበይነመረብ የበሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለማስቀረት የተቀናጀ እና ስልታዊ ጥረቶችን እንዲሁም ድንበር ዘለል የሆነ ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ይፈልጋል።ችግሩን የሚመለከት አዳዲስ ህጎችን ማውጣትም ሌላው ጉዳይ ነው።
በአውሮፓ ህብረት በሴቶች ላይ የሚደርሱ የበይነመረብ ጥቃቶችን ለመዋጋት በጎርጎሪያኑ ግንቦት 7 ቀን 2024 አዲስ ህግ ፀድቋል። ህጉ ሰኔ 2027 መጨረሻ ላይ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፤ በአውሮፓ ህብረት ደረጃ በበይነመረብ እና ከበይነመረብ ውጭ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ወንጀል የሚያደርግ ነው።
ይህ ህግ አባል ሀገራቱ ጠንካራ የመከላከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ የተጎጂዎችን ጥበቃእና ድጋፍ እንዲያጎለብቱ፣ተጎጅዎች ፍትህ እንዲያገኙ የሚያመቻቹ እና በባለስልጣናት መካከል ቅንጅት እና ትብብር በማጠናከር እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይጠይቃል።
የዲጅታል መድረኮች የይዘት ክትትል እንደ መፍትሄ
ከአዳዲስ ህጎች በተጨማሪ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መድረኮች የይዘት ክትትልን ማሳደግ፣ ጎጂ ይዘትን ለመቀነስ ስልተ ቀመሮችን መተግበር እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ከህግ አስከባሪዎች ጋር መተባበር አለባቸው። ዶክተር ማኅሌት በበኩሏ የይዘት ፈጣሪዎችም መድረኩን በሀላፊነት ሊጠቀሙ ይገባል ትላለች።
የህብረተሰቡን የዲጂታል እውቀት እና ግንዛቤዎች ማሳደግም ሴቶች እራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት እንዲጠብቁ ለመርዳት ወሳኝ ናቸው። የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችም የሥነ-ምግባር ማሻሻያ እና ቁጥጥር በማድረግ ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የጉዳት መሳሪያ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።
በአጠቃላይ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው የሳይበር ጥቃት ደህንነታቸውን፣ ክብራቸውን እና በዲጂታል አለም ውስጥ ተሳትፎን የሚጎዳ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።እነዚህን የመብት ጥሰቶች በመዋጋት ረገድ በአካባቢው የሚታዩ አንቂዎች እና የመብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ አስተዋፅኦ ቢያደርግም፤ ባለሙያዎች እንደሚሉት የችግሩ ስፋት እና ውስብስብነት ሥርዓታዊ መፍትሄዎችን ይፈልጋል። ስለሆነም የሳይበር ጥቃትን ለመዋጋት ህጋዊ፣ቴክኖሎጂያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ያስገባ መፍትሄ ሊኖር ይገባል። ያ ከሆነ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከፍርሃት እና ጉዳት ነፃ ሆነው የሚኖሩበት ዲጂታል አካባቢ መፍጠር ያስችላል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ