በሞያቸው ተፈላጊ የሆኑ የውጭ ዜጎች ለምን ከጀርመን ወደ ሌሎች ሀገራት ይሄዳሉ?
ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2017የጀርመን ምጣኔ ሀብት እየተዳከመ ነው። ያም ሆኖ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሰለጠነ የሰው ኃይል በእጅጉ ያስፈልጋታል። የህክምና ባለሞያዎች በተለይም የነርሶች ፣የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በግንባታው እና በንግድ ዘርፍም የባለሞያዎች እጥረት አለ። የአፀደ ህጻናት መምህራን፣ ምግብ አብሳዮችና እና የከባድ ተሽከርካሪዎችና የአውቶብስ ሾፌሮችም እንዲሁ ይፈለጋሉ። በዶቼቬለዋ የዛቢነ ኪንካርትስ ዘገባ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ኩባንያዎች 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ የስራ ቦታዎች ሠራተኛ አልተገኘላቸውም ነበር። ያም ሆኖ ከቀድሞው አሁን ቁጥሩ ከፍ ያለ የውጭ ዜጋ ጀርመን ውስጥ በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርቷል። በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም. ብቻ በሥራው ዓለም የውጭ ዜጎች ስምሬት ከ16 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህም በ2010 ዓም ከነበረው ከእጥፍ በላይ ያደገ መሆኑ ነው የተነገረው። ከሁሉም በላይ በህክምናው ዘርፍ እጅግ ብዙ የውጭ ዜጎች ይሰራሉ።በጀርመን ከ6 ሐኪሞች፣ ከአንድ በላይ የሚሆኑት የውጭ ዜጎች ነው። ከ2022 ዓም ወዲህ በተለይ የውጭ ሀገር ዜጋ ነርሶች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው።በአጠቃልይ በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ከአምስት ሠራተኞች አንዱ የውጭ ዜጋ ነው።
ከጀርመን የመወጣት ሀሳብ
ግን እነዚህ የውጭ ዜጎች ጀርመን ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየት ይፈልጋሉን?
በፌደራል ጀርመን የቅጥር ጉዳዮች የሚመለከተው መስሪያ ቤት የቅጥር ጥናትና ምርምር ተቋም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ጥናት አካሂዷል። ጥናቱም እድሜያቸው ከ18 እስከ 65 ዓመት በሚደርስ የተለያዩ የሞያ ዘርፎችን በሚወክሉ 50 ሺህ የውጭ ዜጎች ላይ በበይነ መረብ ነበር የተካሄደው ። ከጎርጎሮሳዊው 2024 እስከ ጥር 2025 ዓ.ም. በተካሄደው በዚህ ጥናት በጀርመን የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ በርካታ ተገን ጠያቂዎች አልተካተቱም። ፕሮፌሰር ዩልያ ኮስያኮቫ በጀርመን የስራ ገበያና የሞያ ምርምር ተቋም የፍልሰት፣ የውህደት እና የዓለም አቀፍ የስራ ገበያ ተመራማሪ ናቸው። ተቋማቸው ባካሄደው ጥናት መሠረት በርካታ የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ጀርመን ለቀው የመውጣት እቅድ አላቸው ።በጀርመን የውጭ ዜጎች ጥላቻ መባባሱ
«26 በመቶ ወይም 2.6 ሚሊዮን ሰዎች, በእርግጥ ባለፈው ዓመት ጀርመንን ትተን ለመሄድ አስበን ነበር ይላሉ። ይህም ማለት አገሩን ለመልቀቅ አስበው ነበር።ወደ ሦስት በመቶ ገደማ, ወይም 300,000 ሰዎች, አስቀድሞ ከዚህ ሀገር ለመውጣት ተጨባጭ ዕቅድ አላቸው። ግማሽ ያህሉ ወደ ትውልድ አገራቸው, ሌሎች ግማሽ የሚሆኑ ወደ ሌላ አገር መሄድ ይፈልጋሉ. እና እነዚህ አሃዞች በግልጽ እንደሚያሳዩት ይህ ፍልሰት ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የፈላስያን ቁልፍ ፈተና ነው።»አዲሱ የጀርመን ረቂቅ የፍልሰት ሕግ
ጀርመን መሸጋገሪያ ናት
ወደ ሀገራቸው መመለስ ከሚፈልጉት መካከል አባዛኛዎቹ ፖላንዳውያንና ሮማንያውያን ናቸው። ጀርመንን ለቀው መውጣት የሚፈልጉት ፤ የሚመርጡት ስዊዘርላንድ ዩናይትድ ስቴትስ ወይም ስፔን መሄድ ነው። በንጽጽር ሲታይ ከፍተኛ የትምሕርትና የኑሮ ደረጃም ካላቸውና ከተሳካላቸው ይልቅ ከቤተሰባቸው ጋር ለመቀላቀል ጀርመን የመጡት ከጀርመን ከመውጣት ይልቅ እዚሁ መቆየትን ይመርጣሉ፤ ይላሉ ሌላዋ የተቋሙ ተመራማሪ ካትያ ጋሌጎስ ቶሬስ ። ጋሌጎስ ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ ለስራ የምትፈልጋቸው የውጭ ዜጎች እንዳይሄዱ መላ መፈለግ አለባት ሲሉ አሳስበዋል።
«የእኛ የዳሰሳ ጥናት ቁልፍ ግኝት ጀርመን ለስራ ወይም ለመማር የመጡ፣ የተማሩ፣ በኢኮኖሚ የበለጠ ስኬታማ እና በጀርመን ቋንቋ የተሻለ እውቀት ያላቸው፣ ከአማካይ በላይ የሚሆኑት ጀርመንን ለቀው መውጣት እንደሚያስቡ ወይም በተጨባጭ የመሰደድ እቅዳቸው እንዳላቸው የሚገልጹ ናቸው። በአጭሩ እነዚህ በትክክል ጀርመን በአፋጣኝ እንዳይወጡ ማስጠበቅ ያለባት የሰለጠነ የሰው ኃይሏ ናቸው። ይህ የተለየ ስደት ለጀርመን የወደፊት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራል።»
የሚፈለግ የሠራተኛ ኃይል ስደት ለጀርመን አደጋ ነው
ባለፉት 12 ወራት የማስተርስ ወይም የዶክትሬት ዲግሪ እና ከዚያም በላይ ያላቸው ጀርመንን ለቀው ለመውጣት አስበዋል። ከፍተኛ እውቀት ከሚያስፈልጋቸው የአገልግሎት ዘርፎች እንደ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፋይናንስ እና ከቢዝነስ ጋር የተያያዙ አገልግሎት ውስጥ የተሰማሩ ከ30 እስከ 39 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከጀርመን ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ እያሰቡ መሆናቸውን እንደተናገሩ ጋሌጎስ ቶሬስ ተናግረዋል። በጤናው በማምረቻ እና በሎጂስቲክስም ዘርፎች ከተሰማሩት ሀገሪቱን ለቀቆ የመውጣት ፍላጎት ያላቸው እንዳሉም ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ የስራ ግብር እና አድልዎ
ታዲያ እነዚህ ተፈላጊ ባለሞያዎች ለምንድን ነው ከጀርመን ወደ ሌላ ሀገር መውጣት የሚፈልጉት?
ባለሞያዎቹ ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሰደድ የሚፈልጉት በዋነኛነት የተሻለ የስራ እድል እና ከፍተኛ ገቢን ተስፋ በማድረግ ነው። እጅግ ቡዙ የስራ ግብር እና የማኅበራዊ ደኅንነት ጫናዎች እንዲሁም ቢሮክራሲ ከጀርመን መውጣት እንፈልጋለን የሚሉት ከሚያነሷቸው ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የምጣኔ ሀብት ምሁርና የአስተዳደር ባለሞያ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እነዚህን ምክንያቶች አብርተዋልአጥኚዋ ጋሌጎስ ቶረስ እንደሚሉት አድልዎም ከዚሁ ጋር ይደመራል።
«ከፍልሰተኞች ሁለት ሶስተኛው በአንድ የሕይወታቸው ክፍል ለምሳሌ በስራ ቦታ ፣በቤት ፍለጋ ፣በህዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች፣ ወይም ከፖሊስ ጋ በሚኖራቸው ግንኙነት ቢያንስ አንዴ አድልዎ እንደደረሰባቸው ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሦስተኛውበያሉሉበት ፍጹም ተቀባይነት እንዳላገኙ ወይም ደግሞ በመጠኑ ተቀባይነት እንዳገኑ ሆኖ ነው የሚሰማቸው። ይህም የስደት ዝንባሌን በእጅጉ ከሚጨምሩ ምክንያቶች ውስጥ ነው። »በጀርመን የውጭ ዝርያ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትና መከላከያው
የሀገሪቱ የፖለቲካ ዝንብሌም አሉታዊ ተጽእኖ አለው
ከጀርመን ህዝብ አንድ አራተኛው መሠረቱ የውጭ ዝርያ አለው። ከጎርጎሮሳዊው 1950 በኋላ 21 ሚሊዮን የውጭ ዜጎች ጀርመን መጥተዋል። አመጣጣቸውም በራሳቸው ወይም በወላጆቻቸው ምክንያት ነው። ከ2015 ወዲህ ብቻ 6.5 ሚሊዮን የውጭ ዜጎች ጀርመን ገብተዋል። ከነዚህም አብዛኛዎቹ ሶሪያውያንና ዩክሬኖች ናቸው። በዚህ ዓመት በየካቲት ወር በተካሄደው ምርጫ የፍልሰተኞች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነበር ።ይኽው ርዕስ የምርጫ ዘመቻው ማድመቂያም ነበር ።በዚህ ጉዳይ ላይ በመገናኛ ብዙሀንም ብዙ ክርክሮች እና ውይይቶች ተካሂደዋል። ይህም በውጭ ዜጎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደነበረው ፈላስያንን በጥሩ ሁኔታ የመቀበሉ ባህል እያሽቆለቆለ መሄዱን ተመራማሪዋ ዩልያ ኮስያቮካ ተናግረዋል። ዶክተር ፀጋዬም ይህ የውጭ ዜጎች ጀርመን የመቆየት ፍላጎታቸውን ከቀነሱት ውስጥ የሚጠቀስ ነው ይላሉ።
«በጎርጎሮሳዊው 2024 የፍልሰት ጉዳይ በጣም ትኩረት የሳበና አነጋጋሪም ነበረ። ማኅበራዊ ተቀባይነት ግን ያን ያህል ጎልቶ የወጣ አልነበረም። እነዚህ ስለ ፍልሰትና የፍልሰት ፖሊሲ ሲካሄዱ የነበሩ ክርክሮች በሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ነበራቸው። የሀገሩ ህዝብ አቀባበል የሚያስከትለው ስሜት ፣ የመገለል ልምዶች እነዚህ ሁሉ የግል ልምዶች ተደማምረው ነው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የመጡበትን ለቀው ለመሰደድ እንደሚያስቡ የሚናገሩትወይም ጀርመንን ትተው ለመሄድ የሚያቅዱት።» ዶክተር ፀጋዬ ጀርመን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ፈጣን እርምጃዎችን ካልወሰደች ተፈላጊ የሆኑ የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ