በምሥራቅ አፍሪቃ ምን እየተካሄደ ነው?
ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በተለይ በወደብ ጉዳይ የተነሳ ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ «የቃላት ጦርነት ውስጥ» መግባታቸው ይስተዋላል ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ግን ሐሙስ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር፦ «ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባችም» ብለዋል ። «ከኤርትራ መንግሥት ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባም።
እንዲያም ሆኖ ከኤርትራ በኩል «የማይመቹ እና የሚጎረብጡ» ነገሮች መኖራቸውን ግን ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል ። ኢትዮጵያ የሁለቱን ሃገራት «የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላለመጉዳት» ስትል ጉዳዩን በትዕግስት እያለፈችው መሆኑንም ገልጠዋል ። የምሥራቅ አፍሪቃ ተንታኙ አብዱርሃማን ሠይድ ግን ጉዳዩን በተለየ ነው የሚመለከቱት ።
አቶ አብዱርሃማን አክለው ሲናገሩ፦ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ አሁን ባሉበት ውስጣዊ ሁኔታ የተነሳ ወደ ጦርነት መግባት ላይፈልጉ ይችሉ ይሆናል ይላሉ። ግን ደግሞ ሁለቱም በጎረቤት ሃገራት በተለይም በሱዳን እና በሶማሊያ በኩል ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ይቀጥል ይሆናል ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ ።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ኃላፊ በሆኑት ሬድዋን ሁሴን የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ሱዳንን ጎብኝቷል ። ልዑካን ቡድኑ እሑድ ግንቦት 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ፖርት ሱዳን ውስጥ በሱዳን አጠቃላይ የደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ አህመድ ኢብራሂም ሙፋዳል አቀባበል እንደተደረገለትም የሱዳን ጋዜጦች ዘግበዋል። የልዑካን ቡድኑ ዓላማ የቃጣናውን ፀጥታ በተመለከተ ለመወያየት እና ኢትዮጵያ ለሱዳን የምታደርገውን ድጋፍም ለመግለፅ ነው ተብሏል ።
ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን በኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አስመራ ውስጥ ይፋዊ አቀባበል ተደርጎላቸው ስለ ቀጣናዊ ጉዳዮች መወያየታቸው ተገልጧል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው እንደቀድሞው አይደለም። ለመሆኑ በአካባቢው ምን እየተካሄደ ነው? አቶ አብዱርሃማን ሁለት ጉዳዮችን በዐበይትነት መመልከት ይገባል ይላሉ ።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወዳጅ የሆነችው የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ሱዳን ግንኙነት እጅግ ሻክሯል ። ሬድዋን ሁሴን የመሩት የሱዳን ጉብኝት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ለጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ያስተላለፉትን መልእክት ያካተተም እንደነበር ተዘግቧል ። በአካባቢው የአሰላለፍ ለውጥ ያስከተለውን ሁለተኛውን ዋና ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያሉትን አቶ አብድርሃማን ይጠቅሳሉ ።
ከሦስት ሳምንታት ግድም በፊት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የፖርት ሱዳን ላይ የድሮን ድብደባ ሲያካሂድ የኤርትራ ባሕር ኃይል ፖርት ሱዳን በመገኘት ከሱዳን ጦር ጋር የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፉን ተንታኙ ተናግረዋል። የኤርትራ ባሕር ኃይል በሱዳን መገናኛ አውታሮች ላይ ሱዳንን ለመደገፍ እና የባሕሩን ቀጣና ለማስተማመን ፖርት ሱዳን መገኘታቸውን ገልጠው ነበረም ብለዋል ።
ከቀጣናው የፀጥታ ጉዳይ ጋር በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው ግብፅም በራሷ እየተንቀሳቀሰች ነው ። በዚሁ ሳምንት የግብጽ ፕሬዚደንት ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ሲሲ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶችን መጎብኘታቸው ተገልጧል ። የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በሱዳን የፈጥኖ ደራሹን ኃይል በመደገፍ ትተቻለች። በበኩሏ ወቀሳውን ውድቅ አድርጋለች። የኢትዮጵያመንግሥትም የቅርብ ወዳጅ ናት ። አል ሲሲ በዚህ ሳምንት ጉብኝታቸው ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ፕሬዚደንት ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል-ናህያን ጋር አቡ ዳህቢ ውስጥ በወቅታዊ የቀጣናው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል ።
የብዙዎችን ትኩረት የሳበው የምሥራቅ አፍሪቃ ወቅታዊ ሁኔታ ወዴት ሊያመራ ይችላል? አብረን የምንመለከተው ይሆናል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ