ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሱዳን መከፋፈልና የአፍሪቃ ረሐብ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 2017ሱዳን፤ የሱዳን ተፎካካሪዎች ሱዳንን ለሁለት እየገመሷት ይሁን?
በጦርነት የምትተራመሰው ሱዳን ለመፈራረስ አንድ እርምጃ ወደፊት እየተራመደች ይመስላል። በአለፈው ሳምንት የሱዳን የሽግግር ሉአላዊ ምክርቤት ጦርን የሚፋለመው በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሐሚቲ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በሱዳን የትይዩ መንግስት ማቋቋሙን ከዳርፉር ይፋ አድርጓል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ይህን ያስታወቀው የዳርፉር ዞንን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ፤ እንዲሁም የሱዳን የደቡቡ ክፍል መቆጣጠሩን ተከትሎ ነው። ከሁለቱ ጀነራሎች ውጭ የሆኑ ግን ደግሞ እነሱም ነፍጥ አንግበው የሚታገሉ ሌሎች የታጣቂ ቡድኖችም በአለፈው መጋቢት ወር 2017 ዓ.ም የሱዳን ሕብረት በሚል መሰባሰባቸውንም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ይህን የትይዩ መንግስትን ለመመስረት እንዳስቻላቸው ይነገራል። እነዚህ ሃይሎች በመጋቢት ወር በተገናኙበት ወቅት በቅርቡ እነሱ በሚቆጣጠሩት አካባቢ «የሰላምና የአንድነት» ያሉትን መንግስት እንደሚያቋቁሙ አሳውቀው ነበር።
ሰሞኑ የተመሰረተው የትይዩ መንግስት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መሪ የሆኑት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ፕረዚደንት አድርጎ መንግስት መመስረቱን ይፋ አድርጓል። ይሁንና ከዚህ ቀደም እኛ በምንቆጣጠረው አካባቢ የሰላምና የአንድነት መንግስት እንመሰርታለን ያለውን በማጠፍ አሁን መላ ሱዳንን የሚያስተዳድር « ሰላማዊ የሽግግር መንግስት» ማቋቋሙን ነው ይፋ ያደረገው። በአሁኑ ሰዓት በሱዳን ሕጋዊ ዕውቅና የሚኖረው ይህ መንግስት መሆኑን በማከል።
በምህጻሩ «ታሲስ» እየተባለ የሚጠራው የሱዳን ሰላማዊ የሽግግር መንግስት ባሰራጨው መግለጫ አካታች የሆነ አዲስ መንግስትን ለማቋቋም፤ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አሰራርና አወቃቀር እንዲኖር ፣ ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ሆነው እንዲሰሩ፣ ያልተማከለ የሥልጣንና የአስተዳደር መርሆን መከተል፤ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሱዳን ሕብረት ለመንገንባት የሚሉ አላማዎችን አንግቦ ለተግባራዊነታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አሳውቋል።
ከአፍሪካ ሕብረትና ከተባበሩት መንግስታት የቀረበ ውግዘት
በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተመሰረተ የተባለው« ሰላማዊ የሽግግር መንግስት» ከሐገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተቃውሞና ውግዘት ደርሶበታል። ቀድሞ የተቃወመው የሱዳን ሰሜንና ሰሜን ምስራቁን ክፍል የተቆጣጠረው የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት መንግስት ነው። በጀነራል አብደልፋታሕ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን የሽግግር መንግስት ሉአላዊ ምክርቤት «ሕገወጥ» ሲል ድርጊቱን አውግዞታል። ፕረዚደንቱ ጀነራል ዓብዱል ፈታሕ አልቡርሃንና ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል እድሪስ በጋራ ተቋቋመ የተባለውን «ሰላማዊ የሽግግር መንግስት»ን « ሰውሰራሽ አሻንጉሊት» ብለው ከማንኳሰስ አልፈው ፤ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው ተቋም ነው» በማለት ድርጊቱን በጥብቅ ተቃውመውታል።
55 አባል ሃገራትን በአባልነት ያቀፈው የአፍሪካ ሕብረት በሱዳንኑ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መሪ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ለተቋቋመው «የትይዩ መንግስት» ዕውቅና እንደማይሰጥ ይፋ አድርጓል። መግለጫው አክሎም የአዲሱ የሽግግር መንግስት መቋቋም «በሃገሪቱ የተጀመረውን የሰላም ጥረትና በሐገሪቱ የወደፊት ህልውና አደገኛ መዘዝ የሚመዝ ነው» ሲል አስጠንቋል።
ውግዘቱ በአፍሪካ ሕብረት አላበቃም። የተባበሩት መንግስታትም የጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን የትይዩ መንግስት ምስረታን ተቃውሞታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ «አዲሱ የሽግግር መንግስት የሱዳን መከፋፈልን የሚያሰፋ፣ ጦርነት ለማስቆም የሚካሄደውን ውስብስብና እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን የሚያኮላሽ ነው» ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።
የፖለቲካው ትኩሳት ቱሩፋት
አማጋድ ጠይብ ፋሪድ በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የልማትና ምርምር ማዕከል ባልደረባ ናቸው። ከዚህ ቀደምም የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብደላ ሃምዶክ አማካሪ፤ በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። ፋሪድ ለዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ አገልግሎት በሰጡት አስተያየት «የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል የትይዩ መንግስት ማቋቋሙ እራሱን እንደ አንድ ትጥቅ መፍታት ያለበት ታጣቂ ሳይሆን እንደ አንድ የፖለቲካ ባለድርሻ አካል ሆኖ ወደ ዓለም አቀፋዊ ውይይት ለመግባት እየሞከረ ነው» ብለዋል። አክለውም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይልእየፈጠረው ያለው «የውሸት» ያሉት ትርክት የሱዳን አውዳሚ ጦርነትን ለመፍታት በሚደረጉ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ላይም የረዥም ጊዜ ጉዳትን የሚያስከትል ስብራት ሲሉ ገልጸውታል።
ፋሪድ እንደሚሉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል የሽግግር መንግስት መስርተናል መግለጫ ሆን ተብሎ የታቀደ እንደሆነም ያክላሉ። ምክንያቱም ይላሉ፤ ምክንያም በዩናይትድ ስቴትስ፣ ሳውዲዓረቢያ፤ ግብፅና ዩናይትድ ዓረብ ኤምረትስ አሸማጋይነት ሁለቱም ጀነራሎችን በቅርቡ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲያደርጉ የያዙትን እቅድ ተከትሎ የወጣ መግለጫ መሆኑን ይገልጻሉ። የውይይቱ ዓላማም በሱዳን እስከአሁን የቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያቆምና የሰብአዊ ረድኤት ተደራሽነትን ለማሻሻል ያለመ በመሆኑን በማከል።
የጦርነቱ የውጭ ተዋንያን
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር መንግስት ምክርቤት ፕረዚደንት የሚሚመሩት ጀነራል ዓብደልፋታሕ አልቡርሃንና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መሪ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሉን በቅርቡ ለማወያያት ተይዞ የነበረው ቀጠሩ መሰረዙን አሸማጋዮቹ አሳውቀዋል። ቀኑ ባይታወቅም አንዳን ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች እስከ የሚቀጥለው መስከረም ሊዘገይ እንደሚችል ገልጸዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በመጨረሻ ሰዓት በውይይቱ አጀንዳ ላይ « የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎችና የሱዳን የሽግግር ሉአላዊ ምክርቤት ሁለቱም በመጪው የሱዳን የሽግግር ሂደት ሚና ሊኖራቸው አይገባም» የሚል ሐሳብ እንዲካተት ጠይቃለች ሲል የዲፕሎማቲክ ምንጮችን እማኝ አድርጎ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
ፋሪድ አልጠይብ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ይህን ያደረገችበት ምክንያት ይገልጻሉ። የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሰነዱ ላይ በስተመጨረሻ ሰአት ይህ ሐሳብ እንዲካተት የሚል ሐሳብ ያቀረበችው ለፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች የምታደርገውን ድጋፍ ለመሸፋፈን ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ምክንያቱም «የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሱዳን ዴሞክራሲያዊ እና ስቪላዊ የመንግስት ሽግግር እንዲኖር እውነተኛ ፍላጎት ስለሌላት ነው» በማለት ምክንያታቸውን ገልጸዋል።
ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የተባበሩት መንግስታት የባለሙያዎች ቡድን፣ ዲፕሎማቶችና የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች፤ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ሰው አልባ የጦር ጀቶች (ድሮኖች) ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችና የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ በተደጋጋሚ ይወቅሳሉ። እነዚህን ወታደራዊ ድጋፎች የሰብአዊ ዕርዳታ በማስመሰል በቻድና ሊብያ በኩል ለፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች እንዲደርስ እንደምታደርግ በማከል። በመሆኑም ይህ የምታደርገው ቀጥታዊ የሆነ ወታደራዊ ድጋፍን ለመሸፋፈን እንደሆነ ነው ፋሪድ የሚገልጹት። ከዚህ የተነሳም የሚካሄዱ የሰላም ጥረቶች የተባበሩት ዓረብ ኤምሬስን ምቾት እንደማይሰጣት ያትታሉ ፋሪድ አልጠይብ።
እንደ ፋሪድ ሁሉ በርካታ ታዛቢዎችም በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሊቆም ያልቻለው በርካታ የውጭ ተዋናዮች ስላሉበት ነው። ከነዚህም ሌላኛዋ ካይሮ ናት። ካይሮ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክርቤት ፕረዚደንት ጀነራል አብደልፋታሕ አልቡርሃንን ትደግፋለች። በመሁኑም የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማሸማገል እየሞከሩ ባሉ ሐገራት የተካተተችው ግብፅ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በስተመጫረሻ «ሁለቱም ሃይሎች የሱዳን የሽግግር መንግስት ሂደት መውጣት አለባቸው» የሚል ሐሳብ በሰነዱ እንዲካተት ያቀረበችውን ምክረ ሐሳብ በግብፅ በኩል ውድቅ ተደርጓል። ይህ የግብፅ ተቃውሞ ውስብስቡ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት የበለጠ እንዲወሳሰብ አድርጎታል። በሱዳን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ያሉ የጦርነቱ ተዋናዮች በርካታ መሆናቸውን ደግሞ የተወሳሰበውን ችግር ይባስ እያወሳሰበው የሚሞት፣ የሚቆስል፣ የሚፈናቀል የሚሰደደውን ሕዝብ የትየለሌ እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሰብአዊ ቀውስ መባባስ
ይህ ከወደ ዳርፉር የተሰማው የትይዩ መንግስት ምስረታ ሐሳብ የመጣው በማዕከለዊና በደቡባዊ ሱዳን ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ነው። ይህ ደግሞ በዓለም ላይ ትልቁ የተባለለት የሰብአቂ ቀውስ ለመፍታትም ሆነ የተፋፋመውን ጦርነትን ለማስቆም የነበረውን ተስፋ የሚያቀጭጭ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተመልካች መስሪያቤት ሪፖርት እንደሚያመላክተው በሱዳን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2023 ወዲህ ከ150,000 በላይ ሰስቪሎች ተገድለዋል። ወደ 12 ሚልዮን የሚሆኑ ሱዳናውያንበጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ መንደራቸው ተፈናቅለዋል። ከነዚሁ 4.1 ሚልዮን የሚሆኑት ወደ ጎረቤት አገር ተሰደዋል። ይህ ጦርነቱ የመዘዘው መዘዝ በዓለማችን ከታዮ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውሶች ተርታ የሚመደብ መሆኑን ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስታወቀው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በአለፈው ዕረቡዕ ዕለት ባሰራጨው መግለጫ በተለያዩ ግጭት በተከሰተባቸው የሱዳን ክፍሎች ረሃብ ፣ በሽታና መፈናቀል በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሄዱን አንስቷል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን እንዲሁም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል በማለት ከሳለች ። በጄኔራል ቡርሃን የሚመራው ኃይል ደግሞ ከክሱ አላመለጠም፤ በሲቪሎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት በመሰንዘሩና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የማድረግ ግቡን በማክሸፉን ከሳለች።
በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ክፍል የሱዳን ተመራማሪ የሆኑት ሞሐመድ ኦስማን «በግጭቱ ምክንያት ሁለቱም ወገኖች ህዝቡ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያገኝ መፍቀድን ጨምሮ በቁጥጥራቸው ሥር ላለው ሕዝብ ዕርዳታ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው» ሲሉ ለዶይቼቨለ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ተናግረዋል ።
«በግጭቱ የተካፈሉ ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ጨምሮ በቁጥጥራቸው ሥር ላለው ሕዝብ እርዳታ እንዲያገኝ የማድረግ ግዴታ አለባቸው ። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በሚቆጣጠረው አካባቢ፤ በተመሳሳይ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው በአብዛኞቹ የዳርፉር አካባቢዎች ህዝቡ የሰብአዊ ዕርዳታ የሚያገኝበት መንገድ የመተባበር ግዴታ አለባቸው። አር ኤስ ኤፍ ማለትም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል የሱዳን ትይዩ መንግስት በመሰረተበትት ዳርፉር ላለው ለሰው ሕይወት እምብዛም አልተጨነቁም ፤ እንዲያም ሲል በተለያዩና በበርካታ አጋጣሚዎች እርዳታን ሲያሰናክሉ ወይም ሲዘርፉ ታይተዋል።»
ፋሪድ አልጠይብ በመጨረሻም አር ኤስ ኤፍ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ፍትሕ በማጓደል፣ ሕዝባዊ አገልግሎት ማስተጓጎል፣ በፆታዊ ጥቃት ፣ በጅምላ ጭፍጨፋ ፣ በዘረፋና መሠረተ ልማት ውድመት ላይ ተሰማርቷል በማለት ለዶይቸቨለ ተናግሯል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ የረሐብ ሁኔታ እየቀነሰ ቢመጣም በአፍሪካ ግን ረሐብ እየጨመረ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገው ሰነድ እንደተነበየው በዓለማችንየረሐብ አደጋእየቀነሰ ቢድም በአፍሪካ ግን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ያትታል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2030 በዓለማችን ከሚኖር የረሐብ ችግር 60 በመቶ የምትሸፍነው አፍሪካ መሆኗን ሰነዱ ይፋ አድርጓል።
በአምስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ድርጅቶች የተጠናቀረው ሪፖርት መሰረት በአፍሪካ አህጉር ከአምስት ሰዎች መካከል ከአንድ በላይ የሚሆኑት ማለትም 307 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በአለፈው በ2024 በአብዛኛው በቂ ምግብ እንደማይመገቡና ይህም ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ረሃብ በእጅጉ እንደሚበልጥ ያሳያል ።
በሪፖርቱ ላይ እንደገለፀው በ2024 ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ 8.2% የሚሆነው የረሐብ አለንጋ ሰለባ ነበር። ይህ አሃዝ ከዛ ዓመት በፊት በነበረው በ2023 በ0.3 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም የረሃብተኛው ቁጥር ትርጉም ባለው መልኩ አልቀነሰም። ሪፖርቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2030 በአፍሪካ ከፍተኛ የረሐብ አደጋ እንደሚኖር ገልጿል። በዓለማችን ከሚኖር የረሐብ አደጋ 60 በመቶ የምትሸፍነው አፍሪካ መሆኗን በማከል።
የዓለም አቀፉ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት አልቫሮ ላሪዮ ለዶይቼቨለ የእንግሊዝኛ አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ለምግብ እጥረትና ረሐብ ከፍተኛው ገፊ ምክንያት ግጭቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
«አደገኛ ለሆነ የምግብ እጥረት ወይም ከፍተኛ ለሆነ የምግብ እጥረት ገፊ ምክንያቱ ግጭት ሲሆን ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ደግሞ ከፍተና ቁችር ያላቸው ግጭቶችን አስተናግደናል።»
የምግብ ዋጋ ጭማሪ
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2023 የነበረውን በዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መናርና የሐገሮች አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መካከል የነበረው ክፍተት በተለይ የአፍሪካ ሀገራት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ለከፍተኛ የረሀብ ችግር አጋልጦአቸው እንደነበረ ሰነዱ ያስታውሳል።
የምርታማነት መጠን መቀነስ፤ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ መጨመርና በግጭት እንዲሁም በአየር መዛባት በተናጥል አልያም አንዱ በሌላኛው እየተደራረቡ የምግብ ዕህል ዋጋ እንዲንር ካደረጉ ምክንያቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
እንደ ሱዳንና ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ባሉ ሐገሮች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ሰዎች ወደከፋ ረሐብ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆነዋል ።የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ባለፈው ሰኞ በአዲስ አበባ በተካሄደውበምግብ አቅርቦትና ተግዳሮቱ ላይ የሚመክር የመሪዎች ስብሰባ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት « ረሐብን እንደ ጦርመሳሪያ መጠቀም ተገቢ አደለም» ብለዋል። ማን እና የትኛው ሐገር ረሐብን እንደጦር መሳሪያነት እየተጠቀመበት መሆኑን ባይገልጹም።
ከግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎች ባልተናነሰ መልኩ ደግሞ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ያለባቸው ብድር ለሕዝባቸው ምግብ ሸምተው እንዳያቀርቡ እንቅፋት እየሆነባቸው እንደሆነ ሪፖርቶች ያመላክታሉ። ሊርዮ እንደሚሉት ሐገራቱ የዕዳ ቅነሳ አልያም ስረዛ ስለማይደረግላቸው ከመንግታቸው ዓመታዊ ወጪ ከ10 እስከ 25 በመቶ ያለባቸውን ብድር ለመክፈል ያውላሉ። ይህም የምግብ እህል ገዝተው ሕዝባቸውን እንዳይመግቡ ከፍተኛ ጫና ሆኖባቸዋል ነው የሚሉት።
«ለአፍሪካ ሐገራት ፈታኝ ከሆኑባቸው ነገሮች አንዱ የብድር ጉዳይ ነው።ለብድር የሚከፍሉት ከፍተና መጠን ያለው ገንዘብ መኖሩ ነው። በየዓመቱ ከፍተኛ የወለድ መጠን ያለው ገንዘብ ለብድር መክፈያነት ያውላሉ። የዕዳ ቅነሳ አልያም ስረዛ ስለማይደረግላቸው ከመንግታቸው ዓመታዊ ወጪ ከ10 እስከ 25 በመቶ ያለባቸውን ብድር ለመክፈል ያውላሉ። ይህ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እንደሚጎዳ ግልፅ ነው። ስለዚህ ከእነዚህ አገሮች መካከል ብዙዎቹ ዕዳ ያለባቸውን ወይም የዕዳ ክፍያቸውን እንዴት መደገፍ እንደምንችል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ የምንፈልገውም ይህ ነው ። »
መንግሥታት ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል?
የምግብ ዋስትና ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች የአፍሪካ ሐገራት መሪዎች በምግብ ራስን ለመቻል ፖለቲካዊ ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው፤ ጠንካራና የሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ዕቅድ እንዲኖራቸውም ጥሪ አቅርበዋል ።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ