ቃለመጠይቅ ከአምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ጋር
ማክሰኞ፣ ግንቦት 25 2012ኢትዮጵያ በየሀገሩ የምትከፍታቸው ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ከትውልድ ሀገራቸው ለማገናኘት ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ይጠበቃል። ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ግን እዚህ ጀርመንም ሆነ በሌሎች የአውሮጳምና የዓለም ሃገራት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያ ከየኤምባሲዎቹ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በአመዛኙ መልካም የሚባል አልነበረም። በእነዚህ ጊዜያትም ኤምባሲዎቹ በሀገር ውስጥ ለሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችም ሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በውጪ የሚገኙ ወገኖችን ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ከርመዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ አንዳች ለውጥ መታየት ጀምሯል። ለወትሮው ፓስፖርት ማለትም የጉዞ ሰነድ ከማሳደስ፣ አንዳንዴም ከዜግነት ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ብቻ ወደኤምባሲው ሳይወዱ በግድ ይሄዱ የነበሩት ወገኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደኤምባሲዎቹ መመላለሳቸው ይታያል። በኤምባሲው በኩልም ለሀገራቸው የየበኩላቸውን ለማድረግ በያሉበት ሀገር የሚኖሩትን ወገኖቻቸውን በግልፅ ማስተባበር መጀመራቸውም ሌላው አዎንታዊ ለውጥ ነው። በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በርከት ያሉ አምባሳደሮችን ወደ ተለያዩ ሃገራት ልኳል። አሁን የሚታየው አዎንታዊ ግንኙነት የአምባሳደሮቹን ተልእኮና ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ይረዳ ይሆን? ዶቼ ቬለ በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት በጀርመን፣ ቼክ ሪፑብሊክ፣ ፖላንድ፣ ስሎቫክና ዩክሬን የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክብርት ወ/ሮ ሙሉ ሰሎሞንን በልዩ ዝግጅቱ እንግዳው አድርጓል። ሙሉ ቃለመጠይቁን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፣
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ