ሸቀጥ የጫኑ 140 ተሽከርካሪዎች ሠመራ ደረቅ ወደብ መቆማቸውን አሽከርካሪዎቻቸው ገለጹ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 20 2017ሸቀጦች የጫኑ 140 ከባድ መኪኖች ለሁለት ወራት በአፋር ክልል በሚገኘው የሠመራ ደረቅ ወደብ ለመቆም መገደዳቸውን አሽከርካሪዎቻቸው ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። አሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደብ የጫኑትን ምግብ እና ሌሎች ሸቀጦች እንደጫኑ ሠመራ ደረቅ ወደብ ከገቡ ሁለት ወራት እንደተቆጠረ ገልጸዋል።
ለወትሮዉ በአራት እና አምስት ቀናት ይጠናቀቅ የነበረው የጉምሩክ የስራ ሂደት ተራዝሞ “ለወራት አቁሞናል” ሲሉ ቅሬታቸዉን ለዶቼቬለ አስረድተዋል። ከአሽከርካሪዎቹ አንዱ “ሠመራ ከገባን ሁለት ወር ከሦስት ቀናችን ነዉ” ሲሉ ተናግረዋል። “በቃ ምንም የሚጠየቅ ሰዉ የለም” የሚሉት የከባድ መኪና አሽከርካሪ ለመቆም ያስገደዳቸው ትዕዛዝ የመጣው “ከመንግስት ነዉ” መባላቸውን ገልጸዋል።
አሽከርካሪዎቹ በሠመራ ደረቅ ወደብ የሚሰሩ የጉምሩክ የሥራ ኃላፊዎች እና ትራንዚስተሮችን “ለምን ለወራት እንቆማለን?” ብለው ሲጠይቁ “ተገቢዉን ምላሽ” እንዳልተሰጣቸው እና አስመጭዎች እነርሱን ለማናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸዉን ይገልፃሉ።
ከአሽከርካሪዎቹ አንዱ “ጭራሽ የሚያናግርም ሰዉ የለም። አስመጪዉ አስጭኖን ያመጣን እራሱ ስንደዉልለት ስልክም አያነሳም” ሲሉ ተናግረዋል። ትራንዚስተሮቹ “ጠብቁ ነገ አዲስ ነገር ይኖራል” ብለዋቸው እንደነበር ያስረዱት አሽከርካሪ “የሆነ ጊዜ ስብሰባ ላይ ነን። ተሰብስበናል ይላሉ። አሁንም ምንም አዲስ ነገር የለም” ሲሉ አስረድተዋል።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሌላ አሽከርካሪ ትዕዛዙ የተላለፈው በገንዘብ ሚንስቴር መሆኑ እንደተናገራቸው ገልጸው “አስመጭዉ ስልክ አያነሳም። ሁሉ አያነሱም” ሲሉ ሰሚ እንዳጡ አስረድተዋል።
“ለወራት ከሥራ ዉጭ ተደርግን” ሲሉ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት የድንበር አቋራጭ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች “ቤተሰቦቻችንን ማስተዳደር አቅቶናል፤ የልጆቻቸን የትምህርት ቤት ክፍያ ላይ ተፅዕኖ ገጥሞናል” ይላሉ።
አንደኛው አሽከርካሪ “ሁለት ወር ሙሉ ስራ ሳትሰራ ቤት ኪራይ የሚከፈል የለ። ልጆች ትምህርትሊያቋርጡ ነዉ። ከባድ ነዉ። ማንም የሚረዳህ የለም” በማለት ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደት የገጠማቸውን ፈተና ገልጸዋል። “አሁን አስመጭዉ የአልጋ ብር ስጠን ስትለዉ አይሰጥህም። ባለ መኪናዉ መኪናዉ ቆሞ ሳይሰራ የሚያስብልህ ነገር የለም” ሲሉ አክለዋል።
ወደ ሀገር ዉስጥ የሚገቡ ምርቶችን ተገቢዉን የጉምሩክ ህግና ስርአት ተከትለዉ እንዲገብ የሚያደርጉት የጉምሩክ አስተላላፊ ትራንዚስተር ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ጀማል ሰይድ ምንም እንኳን እነኝህ ምርቶች መንግስት ከፍራንኮ ቫሉታ ጋር በተያያዘ ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ የታገዱ ቢሆንም 140 የጭነት መኪኖች የጫኗቸዉ ምግብ ነክ ሸቀጦች ግን ለብልሽት እየተዳረጉ ነዉ ይላሉ።
“በፍራንኮ ቫሉታ ነዉ የቆመዉ። እስካሁን መፍትሄ አልተሰጠንም። ጅቡቲ ላይ አስቁመዉ ነበር። አገር ዉስጥ የገቡትንም አስቁመዋቸዋል። መፍትሄ ይመጣል ተብሏል። ገና ነዉ።እስካሁን ድረስ አልመጣልንም” የሚሉት አቶ ጀማል “ስንዴ አለ። ስንዴ ይነቅዛል። ብዙ ነገር የሚበላሽ አለ” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። “እስካሁን ድረስ መፍትሄ አልተሰጠንም። እየጠበቅን ነዉ” ሲሉ አክለዋል።
የፍራንኮ ቫሎታ መገታት፡ ገበያውን ለማረጋጋት ወይስ ትይዩ የውጪ ምንዛሪን ለመቆጣጠር?
በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሠመራ ቅርንጫፍ የንግድ ገቢ እቃ ቡድን አስተባባሪ አቶ አስራት የኢትዮጵያ መንግስት ፈቅዶት የነበረዉ ህጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የዉጭ ምንዛሬ የባንክ ቤት ፈቃድሳያስፈልግ ከዉጭ ሀገር እቃ ለማስገባት የተሰጠ ፈቃድ ፍራንኮ ቫሉታ ጊዜ ገደብ በማለፉ ነዉ እነኝህ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱት ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር “በሕግ ክልከላ ከተደረገባቸው ዕቃዎች፣ የነዳጅ አውቶሞቢሎች፣ ከጸጥታ እና ከደህንነት ዕቃዎች” ውጪ ያሉ ሸቀጦች ያለ ውጭ ምንዛሪ ፈቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ፈቅዶ ቆይቷል። ይሁንና የምግብ ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትን የፍራንኮ ቫሉታ አሰራር በገንዘብ ሚኒስቴር የሰረዘው ከአራት ወራት ገደማ በፊት ነው። ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ለሁሉም አስመጪዎች እና ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ መገለጹን አቶ አስራት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
“ከተሰጠዉ ቀን አንድ አምስት ቀን አሳልፈዉ የገቡትን እንዲገቡ ተደርጓል” የሚሉት አቶ አስራት “በጣም ዘግይተዉ የገቡ መኪኖች እንዳይገቡ ተብሎ በጉምሩክ ኮሚሽንም ዉሳኔ ተሰጠ” በማለት አስረድተዋል።
በሠመራ ደረቅ ወደብ የሚገኙ140 የሚደርሱ ተሳቢ መኪኖች የጫኑትን ጭነት በተመለከተ መፍትሄ የመስጠቱ ኃላፊነት ከጉምሩክ አቅም በላይ በመሆኑ ወደ ገንዘብ ሚንስቴር ተመርቷል የሚሉት አቶ አስራት በቀጣይ ከገንዘብ ሚንስቴር የሚመጣን መመሪያ እንተገብራለን ይላሉ።
“ገንዘብ ሚንስቴር ነዉ መቅረብ የሚችሉት። አሁን ጉምሩክ ጋር ጉዳዩ የለም። ዋናዉ ትዕዛዝ የሚሰጠዉ ገንዘብ ሚንስቴር ስለሆነ እኛ ማስፈፀም ብቻ ነዉ” ሲሉ ተናግረዋል። “በኛ በኩል ምንም አይነት የተሰጠን አቅጣጫ የለም። መንግስት ነዉ በደብዳቤ ያስቆመዉ። ስለዚህ እነሱ ልቀቁ ካሉን እኛ መልቀቅ ነዉ” ሲሉ አቶ አስራት ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል።
ኢሳያስ ገላው
እሸቴ በቀለ